Sunday 17 May 2020

የኅዳር በሽታ፤ ኮሮና፤ ዝሙት!

50 ሚሊየን በላይ ሕዝብ የቀጠፈው፣ ዓለም ዓቀፉ ብሪትሽ ፍሉ፣ በአገራችን ሲከሰት "የኅዳር በሽታ" መባሉንና የመጣበት ምክንያትም "ዘማዊ በምድሪቱ ስለ በዛ ነው" ተብሎ ይታመን እንደ ነበር ስንቶች ሰምተን ይኾን? [በእርግጥ በአገራችን አንድ ጥፋት ሲከሰት፣ ወዲያው ከመቅሰፍትና ከመዓት ጋር ማያያዙ የተለመደ ቢሆንም፣ በዚያ ዘመን ዝሙት የተስፋፋ መኾኑን በሚገባ ያሳብቃል] እግዚአብሔር ግን ምሕረቱ ብዙም፤ ለዘላለምም ነው!

አንዳንድ የአውሮፓ አገራትም፣ በኮቪድ 19 - ኮሮና ምክንያት ዜጎቻቸውን፣ "በአንድ ሚስት አልያ ፍቅረኛ ተወሰኑ!" እያሉ ሲማጸኑ እየሰማናቸው ነው። ከዚህ በዘለለ በኮሮና ምክንያት የሴቶችና የሕፃናት ትንኮሳ፣ ፍቺ እጅግ ማሻቀቡን በተደጋጋሚ ሰምተናል።

  ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ በኢትዮጵያ ትምህርት የተጀመረበት ምክንያት፣ ዝሙትን ለመከላከል እንደ ኾነ ስንቶቻችን እናውቃለን? ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያነቡና ከዝሙት እንዲጠበቁ ለማበረታታት ታስቦ ይኾንን?! አላውቅም፤ ከኾነ ግን ታላቅ ማስተዋል ይመስላል።

ሃይማኖተኞች በበዙባት ምድር፣ በተደጋጋሚ ከዝሙት ጋር ስማችን መነሳቱ፣ ኢየሱስ በናዝሬት ሰዎች አለማመን የተደነቀውን ያህል ያስደንቃል። የዓለሙ ትልቁ ድረ መረብ ጎግል(Google) በአለም ላይ አያሌ የዝሙት ፊልም ተመልካች ሰዎች ከያዙ አገራት መካከል፣ እኛን መመደቡ የማንዘነጋው የቅርብ ትዝታ ነው። እኛ ግን አኹንም በግብዝነታችን አለን!

ዝሙት የትውልድ ነቀርሳ ነው፤ የአምልኮውን መቅደስ የሚያሳድፍ እቡይ ነው፤አዋርዳ የጣለቻቸው ብዙ ናቸው፤ የገደለቻቸውም ስፍር ቊጥር የላቸውም።” (ምሳሌ 726) እንዲል፣ ዝሙት ብዙ ቤቶችን፣ ትዳሮችን፣ ጥብቅ ባልንጀርነትን፣ የተወደዱ ሕብረቶችን፣ ታላላቅ ጉባኤያትን ...  መነቃቅሮ አፈራርሶአል።

ስለ ዝሙት ከምልክት ባለፈ፣ ያፈጠጠ እውነት በመካከላችን አለ፤ በአንዳንድ ስፍራዎች አብያተ ክርስቲያናት ጭምር የመፍትሔ አካላት ከመኾን ይልቅ፣ የችግሩ አካላት ኾነው ተመልክተናል። እንዴት ልብ ይሠብራል?! ወርቁ እንዴት ደበሰ ይኾን?!

ሰው ዓመጻውን አሟጥጦ እየፈጸመ ይመስላል። እናም እባካችን[] ከዝሙት እንሽሽ፤ ዳሩ ኮሮናን ፈርተን አይኹን፤ በሕይወት እንኖር ዘንድ፣ ንስሐ ገብተን እግዚአብሔርን በመፍራት እንመለስ። “... ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ የሚመራህ መሆኑን ሳትገነዘብ፣ የቸርነቱን፣ የቻይነቱን የትዕግሥቱን ባለጠግነት ትንቃለህ?” (ሮሜ 24) የበዛ ምሕረቱን አንናቅ፤ ዘመን ለንስሐ ዕድሜ ለመንፈሳዊ ፍስሐ ተሰጥቶናልና፤ እንመለስ።

ከኀጢአት ኹሉ የሚያድነው የእግዚአብሔር ጸጋ ባለ መጥፋት ኢየሱስን ለምትወዱና እግዚአብሔርን ለምትፈሩ ኹሉ ይብዛላችሁ፤ አሜን።

No comments:

Post a Comment