Sunday 3 May 2020

የሐሰት መምህራን የማይነኳቸው ርእሶች (ክፍል ፩)

Please read in PDF
   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ቅዱሳን ደቀ መዛሙርት፣ ከእነርሱ መሄድ በኋላ ሐሰተኛ መምህራን ሊመጡ እንዳላቸው በግልጥ ተናግረዋል።  የሐሰት መምህራን ሁል ጊዜ የእውነተኛ ደቀ መዛሙርት አለመኖርን ይመኛሉ ወይም የእውነተኛ ደቀ መዛሙርትን ቸለተኝነት እንደ መግቢያ በር ይጠቀሙበታል።  ስለዚህም ሁልጊዜ ባለመታከት አንገታቸውን ከማስገግ አያርፉም።  አሳቻ ቦታ ቆመው ምቹ ጊዜ እንዲመጣላቸው ተግተው ይጠብቃሉ።



  ከሌላው ጊዜ በተለየ፣ የሐሰት መምህራን ሐሰትን ወደ ሰው አእምሮ ወይም ወደ ጉባኤ ለማስገባት የሚተጉትን ትጋት ያህል፣ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት እውነትን ለመመስከርና በአደባባይ ለማወጅ ያላቸው ቅንነትና ድፍረት፣ በቊጥርም ጭምር እጅግ አናሣ ነው።  የሐሰት መምህራን የእውነተኛ ደቀ መዛሙርትን አለመኖር የሚጠብቁ ደግሞም የሚተጉ ብቻ አይደሉም፤ ጣፋጭና ሰውን ደስ የሚያሰኝ ትምህርትም በማዘጋጀት የሚተካከላቸው የለም።  እንግዲህ ታላቁን የጥፋት መንገድ ሲያዘጋጁና ሲያደላድሉ የስህተት መምህራን ፈጽሞ የማይናገሩአቸው፣ የሚያስተምሩአቸው፣ የማይሰብኳቸው የማይተጉላቸው አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አሉ።

  በድፍረት እንዲህ ብለን መናገር አንችላለን፤ ከዚህ በታች ስለምናነሳቸው ስለእያንዳንቸው ርዕሶች ወይም ትምህርቶች የሐሰት መምህራን ፈጽሞ አያስተምሩም ወይም ጨርሶውኑ ትምህርቶቹን አያውቁአቸውም ወይም እነዚህን ርዕሶች በተመለከቱ ያላቸው ትምህርትና ተአምኖ ጐደሎ ወይም ኢ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው።
እኒህም፦

1. ኀጢአት፦ የሐሰት መምህራን ስለ ኀጢአት ፈጽሞ አያስተምሩም፤ ቢያስተምሩም ኀጢአትን የሚረዱበት መንገድ እጅግ የተሳሳተ ነው።  ኀጢአትን በተመለከተ በሐሰት መምህራን ዘንድ እኒህ ቃላት እጅግ የተሳሳተ ትርጉም አላቸው።

·        ጸጋ፦ የእግዚአብሔር ጸጋ ከኀጢአት የዳንበት አምላካዊ የባለጠግነት ችሮታ ነው።  ኹላችን በክርስቶስ ኢየሱስ ያመንን፣ ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ሲሰቀል የኀጢአታችን ዕዳ ተከፍሎአል፤ ከሙታን መካከል ሲነሣ ደግሞ ጸድቀናል፤ መጽደቃችንም በመንፈስ ቅዱስ ታትሞ ተረጋግጦአል።

  በክርስቶስ ኢየሱስ መዳናችን ግን ኀጢአት ለመሥራት ፈጽሞ አርነት አይሰጥም።  ስለ ዳንን ኀጢአትን ወይም የኑሮ ዘይቤ እንድናደርግ አይፈቅድልንም።  በጸጋ የጸደቀ ሰው ወይም “አማኝ” ኀጢአት ቢሠራ፣ “ንስሐ ግባና በኢየሱስ ደም ታጥበህ ንጻ፤ ጥራ!” እንለዋለን እንጂ፣ “ችግር የለውም” ብለን አናቃልለውም ወይም የእግዚአብሔርን ጸጋ አናጣጥልም።  “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤” እንዲል።

  ስለዚህም ጸጋ የዳንንበት ብቻ አይደለም፤ ወደፊትም ከኀጢአት የምንጠበቅበት ብርታትና አቅማችን፣ ጉልበታችንም ነው እንጂ።  ጸጋው ከኀጢአት ይጠብቃል፤ ያሸሻል፤ ያርቃል፤ እንድንሰደድ ያደርጋል።  ብዙዎች የሐሰት መምህራን በጸጋ ሽፋን ኀጢአትን ሲያበረታቱ እናያለን።  አልያም አያሌ አማኞች፣ በጸጋ ሽፋን ለኀጢአት አርነት ሲሸነፉ እናስተውላለን፤ ለዚሀም ነው የአዲስ ኪዳን ምንባባት እንዲህ ያለውን ዐሳብ፣ በብርቱ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ የሚያስጠነቅቁት።

 በሕግ የኀጢአት ባሮችና የተረገምን የነበርን ኹላችን፣ በክርስቶስ ጽድቅ ከኀጢአት ባርነት ወጥተን አርነትን አጊኘተናል።  አርነታችንም ኹለንተናዊ ነው።  ኹለንተናዊ ስለ ኾነም፣ በሥጋ፣ በነፍስ ወይም በመንፈስ ካገኘነው አርነት ባሻገር፣ በዘላለም ጉዳያችንና በሰማያዊ ስፍራ በመቀመጥ፣ ሥፍራዊ ለውጥ ጭምር ማድረጋችንን የሚያሳይ ሕያው አርነት ነው።  ይህን ዘላለማዊ እውነት ግን ላልተፈለገ የኀጢአት ተግባር ተርጉመው ሲጠቀሙ እንመለከታለን።  

   በብዙ ኀጢአታችን ላይ የተትረፈረፈ ጸጋ የፈሰሰልን፣ ዳግመኛ እጅግ ብዙ ኀጢአት እንድንሠራ አይደለም፤ “እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? አይደለም።” (ሮሜ 8፥1)።  አዎን አይደለም፤ ኀጢአትን የኑሮ ዘይቤአችን አድርገን የማንሠራው፣ ስለ ዳንን ነው፤ ከዳንን ዘንዳ የትላንት የኀጢአት ኑሮአችንን ፈጽመን የምንጠላው እንጂ አንዳች የሚወደድ እንደ ሌለው ማስተዋል ይገባል።  መዳን ለኀጢአት አንዳችም አርነት አይሰጥም፤ “ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ።” (ገላ. 5፥13)።

ብዙዎች በጸጋ መዳናቸውን፣ በኀጢአት መውደቃቸውን ለመፈጸሚያ ሲጠቅሱት እንመለከታለን፤ ነገር ግን እንዲያው ከጸጋው የተነሣያገኘነው ዐርነት፣ ኀጢአትን ለመሥራት ፈቃድን የሚሰጥ አይደለም፤ ይልቁን ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ፍጹም በመሰጠት የምንኖርበትን ሕይወት የምንለማመድበት እንጂ።  ጸጋ እንደ እግዚአብሔር ቃል ተጣምሞ ከተተረጐመበት ውጭ፣ ከተተረጐመ ፍጻሜው ከኀጢአት አዘቅት ውስጥ እንደሚዘፍቀን መታወቅ አለበት፤ ከዳንን፤ ላዳነን ጌታ ብቻ ልንታዘዝና ልንኖርለት ተጠርተናል፤ ጸጋ ይብዛላችሁ፤ አሜን።

ይቀጥላል …  

1 comment: