Sunday, 26 April 2020

በሕማሙና በትንሣኤው ዙርያ የነበሩ ምስክሮች (ክፍል አምስት)


3. ትንሣኤውን በመመልከት ኹሉን ትቀድማለች፦ ባለፉት ጊዜያት ጌታ መንፈስ ቅዱስ እንዳስተማረን፣ በመግደሎሟ ሴት ኹለት ነጥቦችን አንስተን፤ ሰባት አጋንንት ያወጣላትና እንዲሁም የጌታ ኢየሱስን ሕይወትና ትምህርት ተመልክታ፣ ፍጹም የተከተለችው መኾኑን አንስተናል። ከዚሁ ቀጥለን የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ምስክሮች ስለ ኾነችው ሴት በጥቂቱ እንመለከታለን።


  “እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና።” (ሐዋ. 2፥24) ተብሎ እንደ ተነገረው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል ሙስናና መቃብርን አጥፍቶ ተነሥቶአል፤ ከሙታን መካከል መነሣቱ ደግሞ፣ የክርስትና ትምህርት መሠረትና ዋና ነው። በእርግጥ መግደላዊት ማርያምና ሌሎቹ ሴቶቹ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን መካከል የሚነሣ አልመሰላቸውም፤ ለዚህም ነው፣ ፍቅራቸውን ለመግለጽ ሲሉ፣ “ሊቀቡት ሽቱ መግዛታቸውና… እርስ በርሳቸውም፦ ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል?” (ማር. 16፥1፡ 3) እየተባባሉ በመነጋገር ወደ መቃብር የመጡት።

  ከቤታቸው ተነስተው ወደ መቃብሩ የሄዱበት ሰዓት ገና ጨለማ ነበር (ዮሐ. 20፥1)፤ መቃብሩ ዘንድ ሲደርሱ ምድር ገና መላቀቅዋ ወይም ወደ መንጋቱ ተቃርባ ነበር ወይም እዚያው እያሉም ፀሐይ የወጣች ይመስላል፤ (ማቴ. 28፥1፤ ማር. 16፥2)። በሕማሙና በትንሣኤው ሰዓት የብዙ ሴቶች ስም ቢጠቀስም፣ የማርያም መግደላዊት ስም በመጀመሪያ ይጠቀሳል፤ (ማቴ. 27፥56፤ ማር. 15፥40፤ ሉቃ. 24፥10፤ ዮሐ. 19፥25)፤ ምክንያቱም፦

1. ባዶውን መቃብር በመመልከት ቀዳሚ ነበረች፦ ኹሉም ወንጌላውያን ማርያም ከያዕቆብ እናትና ከሰሎሜ ጋር ቀድማ መድረሷን ይመሰክራሉ፤ (ማር. 16፥1፤ ማቴ. 28፥1፤ ሉቃ. 24፥1)። እኒህ ሴቶች ጌታ ኢየሱስ ከገሊላ ጀምሮ ሲከተሉት ነበር፤ በመከራውም ሰዓት አብረውት ነበሩ (ማር. 15፥40፤ ሉቃ. 23፥49)፤ ጌታችን ኢየሱስ በተቀበረ ጊዜም፣ ኹለቱ ወዳጆቹ የት እንደ ቀበሩት ተመልክተዋል፤ (ማር. 15፥47)። በእነዚህ ኹሉ ክንውኖች ውስጥ፣ ወደ መቃብሩ ከመጡ ሴቶች መካከል ማርያም መግደላዊት አስቀድማ መገኘቷን ስናስብ፣ ምን ያህል ለጌታ ፍቅር የተሰጠች መኾኑን እናስተውላለን።

   ከተጠቀሱት ሴቶች መካከል፣ የኢየሱስ እናት የቅድስት ማርያም አለመጠቀሱ ይደንቃል፤ ምናልባት በአንድነት ከወንጌላዊ ዮሐንስና ከሌሎች ደቀ መዛሙርት ኾና ይኾናል፤ በስቅለቱ ሰዓት፣ ከሞቱ በፊት ጌታ ኢየሱስ ለወንጌላዊው ዮሐንስ ሰጥቷት ነበርና፤ (ዮሐ. 19፥27)።

 ማርያም መግደላዊት መቃብሩን አስቀድሞ ተመልክታ ነበርና በመቃብሩ ስፍራ፣ ገና ጨለማ ቢኾንም እንኳ ለመገኘት አልተሳሳተችም። እናም፣ በመቃብሩ ስፍራ ድምጿን አሰምታ እያለቀሰች፣ ኢየሱስን “ትጠብቀው” ነበር፤ “ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር።” (ዮሐ. 20፥11)። መቃብሩ መከፈቱንና የመነሣቱን ዜና በተወሰነ ረገድ ብትሰማም፣ ነገር ግን እጅግ አዝና፣ ኢየሱስን ለማግኘት በብዙ መፈለጓን ያሳያል። ደክሞ ወደ መቃብር ቢወርድም፣ ወግና ባሕሏን ጥሳ ስለ ፍቅሩ ሽቱ ይዛ መገኘቷን አስተውሉ! እንደ አይሁድ ወግ አስከሬን ሽቱ አይቀባም፤ ነገር ግን ለፍቅሩ ይዘው መምጣታቸውን ስንሰማ እንደነቃለን! ፍቅር ለዘላለም ብርቱ ነው!

2. ትንሣኤውን በማየት ቀዳሚ ነበረች፦ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት የጌታን መቃብር ባዶነት አይተው ወደ ቤታቸውም ቢመለሱም፣ መግደላዊት ማርያም ግን ከዚያው ከመቃብሩ ስፍራ ንቅንቅ አላለችም ነበር፤ (ዮሐ. 20፥10-11)። ዙርያ ገባውን እያየች፤ መቃብሩንም ደጋግማ ጎንበስና ቀና እያለች በመመልከት እዚያው አከባቢ ነበረች፤ እንዲያውም በአከባቢው ያለ አትክልተኛ መስሏት፣ ኢየሱስን እንደ አትክልተኛ አውርታውም ነበር፤ ለማግኘት ያላት ፍላጎቷ ጥብቅ፤ ፍለጋዋም ብርቱ ነበር።

  እንዲህ በጥብቅ ስትፈልገው፣ ተወዳጁ መሲሕ ተገለጠላት፤ ከሙታን መካከል የተነሣው ጌታ ታያት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእርሷ ታየ! የትንሣኤው ቀዳሚ ምስክር ኾነች። “መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።” (ዮሐ. 20፥18)። የመጀመሪያዋም ምስክር ኾነች፤ (ማር. 16፥9)። ያየችውን መሰከረች፤ ክርስትና የመገለጥ ትምህርት ነው ስንል፣ ላመኑት ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ ተገልጧል ማለታችንም ነው!

3. ረቡኒ፦ ማርያም መግደላዊት ጌታ ለመጀመሪያ ጊዜ በመቃብሩ ስፍራ ሲገለጥላት፣ ያወቀችው “ማርያም” ብሎ በጠራት ጊዜ ነው። ጌታ ኢየሱስን በድምጹ አጥርታ ታውቀው ነበርና፤ በእርግጥ ኢየሱስን ልጆቹ በድምጹ ያውቁታል (ዮሐ. 10፥3-4)። እርሷን በስሟ በጠራት ጊዜ እርሷም፣ “ረቡኒ” አለችው፤ በአራማይክ ትርጉሙ መምህሬ ወይም አስተማሪዬ ማለት ነው። መጠሪያው በጸሎት ውስጥ አምላክን እንደ መጥራት ያለ ነው። ነገር ግን ማርያም በዚህ ጊዜ ኢየሱስን በዚህ ልክ ተረድታው ነበር ማለት አያስደፍርም።

  ኢየሱስን ግን ወዲያው አውቃዋለች፤ በድምጹ ለይታዋለች። ከኢየሱስ ጋር ብዙ ማሳለፍ ጥቅሙ ይህ ነው፣ እርሱን በትክክል ማወቅና መለየት፤ በእርግጥም እርሱ ዋናና የመጨረሻው መምህራችንና አስተማሪያችን ነው። ለሚወዱት ኢየሱስ እንዲህ በክብርና በብርሃን ይገለጣል።

4. ትንሣኤውን በመመስከር ቀዳሚ ነበረች፦ ለደቀ መዛሙርቱ አስቀድማ መጥታ፣ የጌታን ትንሣኤ ያበሠረችውም እርሷ ነበረች። ብዙ አጋንንት የነበረባት ሴት፣ እጅግ የተናቀችና የተተወችን ሴት ኢየሱስ ከመሬት አንሥቶ፣ የትንሣኤው ቀዳሚ ምስክር አደረጋት። የትንሣኤው ኀይል የተገለጠው እጅግ ኀጢአተኞች ለኾኑትና ለደካሞች ነው።  ዛሬም በምድራችን እግዚአብሔር ደካሞችን ጠርቶ፤ በጸጋው አጽንቶ፣ እውነተኛ የልጁ ምስክሮች አድርጎ እንዳቆማቸው ስናይ እጅግ እንደነቃለን!

  የጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ በብዙ ምስክር ያሸበረቀ እውነት ነው፤ ምስክሮቹ ደግሞ ሊታበሉና ሊስተባበሉ የማይችሉ ናቸው፤ ጌታችን ሆይ ትንሣኤህን እናምናለን፤ እንታመናለን፤ አሜን።

ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment