Friday 17 April 2020

የሃይማኖት መሪዎች በኢየሱስ ላይ ለምን ተነሣሱ?

Please read in PDF
   በሰሙነ ሕማማት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሥጋ ሞቱ ይዘከራል፤ ስለ ሞቱ የተነገሩ ክፍሎች በብዛት ይነበባሉ፤ ይፈከራሉ፤ ይታተታሉ። በእነዚህ ጊዜያት አብዛኛውም የክርስቲያን ማኅበረ ሰብ “የፍለጋውን ዱካ” ወደ መንፈሳዊ ነገሮች ሲያደርግም ይታያል። መጠጥና ጭፈራ ቤቶች፣ የቁማር፣ የጫት መቃሚያና ሺሻ፣ ጋንጃ መማጊያ ቤቶች ከወትሮው ጊዜ በተለየ፣ ሰዎች ጐራ አይሉባቸውም[ኮቪድ 19 ኮሮና ጭርሱን ጠረቀመልን - እሰይ - ኡፈይ]። በሰሙነ ሕማማት የዘፈን ኮንሰርቶች፣ የመጠጥ ድግሶች ጨርሶ አይታሰቡም፤ ይህ ግን ከሳምንት ያላለፈ ጥንቃቄና መጠበቅ መኾኑን ስናስተውል፣ ነገሩ መንፈሳዊ ሳይኾን የግብዛዊነት ጠባይ መኾኑን እንረዳለን።





  ዳሩ ግን የሰሙነ ሕማማት መንፈሳዊነቱ ከፋሲካ ማግስት ገና ቀኑ ሳይዋገድ፣ በጭፈራ፣ አለልክ በመብላት፤ በመጠጣትና እንዲህ ከሚመስሉ ተግባራት ከመዋጥ አይዘልም፤ ከሕማማቱ ማግስት ትንሣኤውን በማሰላሰል፣ ነገረ መስቀሉን በማውጣትና በማውረድ፣ የጌታ ኢየሱስን ለአባቱ መታዘዝና ደስ የማሰኘቱን ነገር የሚያጉተመትሙ ቅዱሳን ቊጥራቸው ከማነሱም በዘለለ፣ የሚገኙትም የቅሬታ ያህል በፍለጋ ነው፤ የአብዛኛው ሰው ትኵረቱ፣ ከምድራዊ ነገር እልፍ አይልምና። ጌታ እግዚአብሔር ምሕረት ያድርግልን፤ አሜን።

  በበዓላት ዋዜማና በቀናቸው፣ ከኢየሱስ ይልቅ ብዙውን ጊዜ፣ ሃይማኖታዊ ተግባራትና ሃይማኖታዊ መሪዎች ገንነው ይታያሉ። ጌታ በነበረበትም ዘመን የኾነው እውነት እንዲህ ነው፤ የሃይማኖት መሪዎች ከኢየሱስ ይልቅ ራሳቸውን የተሻሉ አድርገው በማቅረብና ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅ ብለው፣ ኢየሱስን አሳልፈው ለሞት በመስጠት ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛሉ። ጲላጦስ ኢየሱስን በተደጋጋሚ መርምሮት፣ “እነሆም፥ በፊታችሁ መርምሬ ከምትከሱበት ነገር አንድ በደል ስንኳ በዚህ ሰው አላገኘሁበትም።” ቢልም (ሉቃ. 23፥14)፣ ሚስቱም፣ “ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ” (ማቴ. 27፥19) ጥብቅ መልእክት ብትልክበትም፣ ጲላጦስ ግን የመጨረሻውን ሥልጣን ተጠቅሞ ፍትሐዊ ፍርድ ከመፍረድ ይልቅ፣ ሕዝቡንና የሃይማኖት መሪዎችን በመፍራት ምክንያት አድሎአዊ ፍርድ ፈረደ።

   የሃይማኖት ሰዎች ለምን ኢየሱስን ለማጥፋት፣ ለመግደል ከልብ ተነሳሱ? ብለን ወንጌላትን ብንጠይቅ እንዲህ ይሉናል፤

1. ሥልጣናቸውን እንዳያጡ፦ ጲላጦስ፣ የሃይማኖት አለቆች ለፋሲካ በዓላቸው መፈሰኪያ ይኾን ዘንድ፣ አንድ እስረኛ ለመፍታት ልማድ በነበረበት ወቅት፣ “በጣም የታወቀውን፤ በዓመጽም ነፍስ ከገደሉት ከዓመጸኞች ጋር የታሰረውን” (ማቴ. 27፥16፤ ማር. 15፥7) በርባንን ከማሰር ይልቅ፣ “በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ” የነበረውን ኢየሱስን ለመግደል በአብሮነት ተስማማ ወይም ራሱን ንጹሕ በማስመሰል እጁን ታጥቦ ለፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጠው።

  ጲላጦስ ብዙ ምክንያት አቅርቦ ኢየሱስን ለመፍታት ቢሞክርም፣ “የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ” (27፥20)። የካህናት አለቆች ሕዝቡን ያባበሉበትን ማባበል፣ የጲላጦስ ውሳኔ ማለፍ ወይም ማሸነፍ አልቻለም። ለካህናት አለቆች ኢየሱስ ብርቱ ማሰናከያ ኾኖባቸዋል፤ ለሕዝቡ ባሳየው ርኅራኄና ፍጹም አገልጋይነት፣ ሥልጣናቸው ከፍተኛ ጥያቄ ተነሥቶበት ነበር። በዚህም ምክንያት ሥልጣናቸው በብዙ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ያበሳጫቸው የካህናት አለቆች፣ ኢየሱስን ገፍተው ለመጣል የትኛውንም ወራዳ መንገድ ለመከተል ጨክነዋል። ዛሬስ ሰውን በመግደልና በማዋረድ መኖርና ሥልጣናቸውን ማደላደል የሚሹ ስንት አሉ?

2. ክብርና ተቀባይነት ማጣታቸው፦ ከአንዲት ከናዝሬት መንደር የተነሣው መሲህ፣ ለብዙዎች የመነጋገሪ ርእስ ኾነ፤ ከእነርሱ መምህራን ሳይማር፣ አያሌ ሕዝብ ተከተለው። ሥርዓታቸውን እየሻረ፣ ወጋቸውን እየተወ፣ ልማዳቸውን እያቃለለ፣ የሃይማኖት መሪዎችን “ግብዞች” በሚል ብርቱ ቃል እየወቀሰ … መምጣቱና በተቃራኒው ደግሞ፣ ከተናቁት ጋር መዋሉ፣ ከተዋረዱት ጋር መቆሙ፣ ከኀጢአተኞች ጋር መብላቱ፣ ከለምጻሞች ጋር መቈጠሩ፣ በሰንበት መፈወሱ … ፊት ለፊት የትምህርቶቻቸውን ሐሰተኝነትና ለእግዚአብሔር ክብር አለማድላቱን ሲናገር፣ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን እያጡ መምጣታቸውን አወቁ። የሕዝቡም ጌታ ኢየሱስን መከተል፣ የሃይማኖት መሪዎችን አላስደሰተም፤ ይልቅ ብርቱ ስጋት ኾነባቸው እንጂ፤ (ማር. 11፥12፡ 18፤ ሉቃ. 20፥19)።

   ራሳቸውን በእግዚአብሔር ቦታ እንጂ እንደ ሕዝብ አገልጋዮች አልቈጠሩምና፤ ፈሪሳዊነታቸውን፣ አገልጋይ ካህናት መኾናቸውን፣ በሕዝቡ ዘንድ እንደ ሰው ሥርዓት መታወቃቸውን … እጅግ አልቀው ተመለከቱት። ከእግዚአብሔር አገልጋይነት በሰው ፊት ጌቶችና ታላላቅ፣ አለቆች ኾነው መታየትን መረጡ። እናም ለገዛ ክብራቸው ብለው ኢየሱስን ለሞት አሳልፈው ሰጡት፤ በመጨረሻም “በዓመፀኞች እጅ ሰቅለው ገደሉት።” (ሐዋ. 2፥23)። ለራስ ለመክበር ሌላውን ማዋረድና የሌላውን ክብር ማጠልሸት እንኳን መንፈሳዊ፣ አመክንዮአዊ አይደለም፡፡

3. እጅግ በክፉ ቀኑበት፦ በጲላጦስ ፊት፣ “የካህናት አለቆች ብዙ ያሳጡት ነበር” (ማር. 15፥3)፤ ብዙ ጊዜ ሊይዙትና ሊግድሉት ቢፈልጉም፣ ነገር ግን ሕዝቡን በመፍራት ብቻ አሳቻ ቀንን ጠበቁለት (ማቴ. 21፥46፤ ማር. 11፥18 14፥1)፣ “የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፥ ኢየሱስንም በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ” (ማቴ. 26፥3-4)፤ ለምክራቸው ማጽኛ ይኾን ዘንድም፣ “የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጐውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፥” (ቊ. 59)።

  የኢየሱስ በሕዝቡ ኹሉ ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት የካህናት አለቆችን እጅግ አበሳጭቶአቸዋል፤ የእነርሱ ሥልጣንና ክብር ከሕዝቡ ልብ እንዳይወጣ በመስጋት፣ ኢየሱስን ከሕዝቡ ልብ በመግደል ለማውጣት ጨከኑ፤ ቅንአት መራራ ናት፤ የኀጢአት ምርጫ አታቀርብም፤ የመልካም ስም ካባ ለብሳ፣ የአጋንንትን ሥራ ታሠራለች፤ ልክ የካህናት አለቆች በፋሲካ አስታክከው፣ ኢየሱስን በቅንአት ከመንገዳቸው ለማስወደግ እንደ ተቻኮሉት። ክፋትን በመልካም ስም ሸሸጎ መሥራት፣ ኤልዛቤል የሄደችበት ፍጹም አጋንንታዊ መንገድ ነው፤ ጾም አጹማ፣ ምስክር አስቈጥራ ንጹሑን ናቡቴ እንዳስገደለችው ማለት ነው፤ (1ነገ. 20)። በዛሬው ዘመንም ይህ መንገድ ቀላልና ምክንያታዊ ይመስላል፤ ኀጢአት ሙሉ ስምና መልኩን ቀይሮም ወደ አብያተ ክርስቲያናት አስግጎ የገባም ይመስላል።

   አዎን፤ በተሰጠን ነገር ለእግዚአብሔር መዋረድና ፍጹም መሰጠት ካልቻልን፣ ስጦታውን አግንነን ሰጪውን ከማዋረድ እንደማንመለስ ያሳየናል። ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ታላቁን አደራና ሥልጣን፣ ለገዛ ጥቅምና ሥልጣናቸው አዋሉት፤ በመጨረሻ ግን ብርቱ ወቀሳና ነቀፌታ ደረሰባቸው። የተሰጠንን ለእግዚአብሔር ካልሠዋነው፣ በፍጻሜው የተቀበልነው ያው ነገር ጠልፎ ይጥለናል፤ በፍጻሜውም ከእግዚአብሔር ፈቃድና ዐሳብ ፈጽሞ ይለየናል። ጌታ ኢየሱስ መልካሙን የእግዚአብሔር ዐሳብና ፈቃድ በትክክል እናስተውል ዘንድ በመንፈሱ ዓይኖቻችንን ያብራ፤ አሜን።

2 comments: