Friday 17 April 2020

“ለይሁዳ ወልዱ ወውሉደ ወልዱ ይደምሰስ!” ለምን አንልም?

Please read in PDF
   በሰሙነ ሕማማት ከምናስተውለው አስደናቂ ነገር አንዱ፣ ይሁዳን የሚረግሙ ሰዎችና አብያተ ክርስቲያናት የመብዛታቸው ጉዳይ ነው። ለክርስቶስ ተላልፎ መሰጠት ይሁዳን ተቀዳሚ ተጠያቂ በማድረግ፣ ይሁዳንና ዘር ማንዘሩን የሚራገሙና የሚኰንኑ፣ የአምልኮ አካላቸውም አድርገው፣ የይሁዳን ኀጢአት ዘክረው፣ በብዙ የሚወቅሱ አያሌ “ክርስቲያኖች” አሉ። ክፋትን መጠየፍ አንድ ነገር ቢኾንም፣ ከእውነት ብዙ መራቅ ግን ግብዝነትን ያጐላል።



   የክርስቶስን ሞት ስናስብ የምናስተውላቸው እውነቶች፦

1. ክርስቶስ በፈቃዱ ሞቶአል፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። … ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ። … እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም” (ዮሐ. 10፥11፡ 15፡ 18) በማለቱ፣ በፈቃዱ ሊሞት እንደ ኾነ አስተማረ። ቅዱሳን ሐዋርያትም ጌታችን ኢየሱስ ራሱን በፈቃዱ አሳልፎ መስጠቱንና ለውርደት ሞት መታዘዙን በግልጥ ጽፈዋል፤ (ፊልጵ. 2፥8፤ ዕብ. 5፥8፤ 1ጴጥ. 2፥23)።

2. ክርስቶስ ሞቱን ያውቀው ነበር፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴሴማኒ በአትክልቱ ቦታ፣ በይሁዳ መሪነት ሊይዙት፣ ጭፍሮችንና ከካህናት አለቆች ከፈሪሳውያንም ሎሌዎች ጋር ኾኖ በችቦና በፋና በጋሻ ጦርም ሲመጡ፣ ኹሉን ያውቅ ነበር፤ በመጡ ጊዜም፣ “ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና፦ ማንን ትፈልጋላችሁ? አላቸው” (ዮሐ. 18፥4) ይላል። እርሱ ምን እንደሚያገኘው፤ ወደ አባቱ መሄጃውን ሰዓትም ያውቅ ነበር፤ (ዮሐ. 13፥1)፤ ማን አሳልፎ እንደሚሰጠውም ያውቅ ነበር፤ (ዮሐ. 13፥11)።

3. የክርስቶስ ሞት ዓለም ሳይፈጠር በክበበ ሥላሴ የታወቀና የተወሰነ ነው፦ “ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በጉ ታርዶአል” (ራእ. 13፥8)፤ የመጣበት ዓላማውም ለመሞት ነው (ዮሐ. 3፥13-15፤ 12፥27)፤ ነቢያት ተስማምተው በአንድ ቃል፣ “እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤” ብለው እንደ ተናገሩት፤ (ኢሳ. 53፥10)።

4. ይሁዳ፣ ጲላጦስ፣ ሄሮድስና አይሁድ የእግዚአብሔርን ዕቅድ ፈጻሚዎች ነበሩ፦ እግዚአብሔር ዕቅዱንና ዐሳቡን በወደደበት መንገድ ሲፈጽም ከልካይ የለበትም፤ እግዚአብሔር በዮሴፍ በኩል የተስፋውን ዘር ከረሃብ ለመታደግ ሲያስብ፣ ዮሴፍን በክብር ወደ ግብጽ ከማውረድ ይልቅ፣ በወንድሞቹ ጭካኔና ቅንአት አማካይነት ወደ ግብጽ እንዲወርድ አደረገው፤ (ዘፍ. 45፥5፡ 7-8፤ 50፥20፤ መዝ. 105፥17)። እስራኤል ኅጢአትን በማድረግ እጅግ በተቀማጠለችበትና ባመጸችበት ወራት፣ እግዚአብሔር ጣኦት አምላኪውን ናቡከደነጾር፣ እስራኤልን ለመቅጣት ባሪያዬ ብሎ ጠራው፤ (ኤር. 27፥6)፤ ከኃጢአታቸው በተመለሱና በምሕረቱ ባሰባቸው ጊዜ፣ አኹንም ጣኦት አምላኪ በኾነው የአሶሩ ቂሮስ አማካይነት ወደ ምድራቸው እንዲመለሱ አደረገ፤ (ዕዝ. 1፥1)

   በተመሳሳይ መንገድ ሉዓላዊው ጌታ እግዚአብሔር፣ የይሁዳን ስግብግብነት፣ የጲላጦስን ቀጣፊነት፣ የሄሮድስን ስድነት፣ የካህናትን ክብርና ሥልጣን አምላኪነት፣ የአይሁድን መቃኞነት ለሥራውና ለፈቃዱ መፈጸሚያ ተጠቀመበት፤ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ “እግዚአብሔር በጥንት ውሳኔውና በቀደመው ዕውቀቱ ይህን ሰው አሳልፎ በእጃችሁ ሰጣችሁ፤ እናንተም በክፉ ሰዎች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት” ብሎ እንደ ተናገረው (ሐዋ. 2፥23)። ከዚህም ባሻገር፣ “እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው።” (ሐዋ. 3፥18)።

  አዎን፤ ሞቱ ቀድሞ የተወሰነ ነው፤ “በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ።” (ሐዋ. 4፥28-29) እንዲል።

   ይህ ማለት፣ ይሁዳና በክርስቶስ ሞት የተባበሩት ኹሉ ልክ ናቸው፤ አላጠፉም፤ አይጠየቁም ማለት አይደለም፤ እግዚአብሔር ፈቃዱንና ዐሳቡን በዚህ መንገድ መፈጸሙ፣ የሳቱትን ኹሉ ከተጠያቂነት የሚያድን አይደለም። ለምሳሌ የይሁዳን ብናነሳ፣ ይሁዳ ሌባ፣ ከልክ ያለፈም ገንዘብ ወዳድ ነበር (ዮሐ. 12፥6)፤ አንድ ቀን ትልቅ ገንዘብ የሚያገኝበት ዕድል ስላመለጠው ሳያስቆጨው አይቀርም፤ (ማቴ. 26፥9-16)። እናም ገንዘብን በማግኘት ክርስቶስን አሳልፎ ሊሰጥ በልቡ ዐሳብን አስገብቶ ነበር፤ (ዮሐ. 13፥2)።

  ሰይጣን ይህን የይሁዳን መንገድ ተከትሎ በመምጣት፣ ወደ እርሱ ልብ ገብቶአል፤ የይሁዳን ፍላጎት ሰይጣን አደላለደለው፤ እንዲረካበትም አመቻቸለት። በይሁዳ ልብ ሰይጣን ከገባ በኋላ፣ የይሁዳ ውሳኔዎች ተከታትለው ተፈጽመዋል። በፍጻሜው ግን፣ “በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፥ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ፦ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ።” (ማቴ. 27፥3-4) በማለቱ፣ ለሠራው ሥራው ኹሉ ተጠያቂ መኾኑን አመለከተ፤ በራሱም ፈረደ።

   የይሁዳ አሟሟቱም ከዔሳው ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ዔሳው፣ አንድ ቀን በመራቡ ምክንያት፣ ለሆዱ መብል ሲል ብኩርናውን አቃለላት፤ እናም ለሆዱ መብል ለምስር ወጥ ሲል፣ ብኩርናውን ሸጣት። ትልቁ ኀጢአቱ ለምድራዊ መብል ሲል፣ ሰማያዊውን ብኩርና አቃልሎ መሸጡ ነው፤ (ዘፍ. 25፥34፤ ዕብ. 12፥16)። ከሸጠም በኋላ ንስሐ ከመግባት ይልቅ፣ ወንድሙን ለመግደል አቄመ (ዘፍ. 27፥41)፤ ይሁዳም በተመሳሳይ መንገድ ወደ ሞት ለሚነዳ ሃዘን ራሱን አሳልፎ ሰጠ እንጂ፣ ልቡን ወደ ንስሐ አላቀናም። ራሱን ሊያጠፋ ቸኮለ፣ ጥፋተኝነቱ ወደ ጸጸት እንጂ ምሕረቱ ብዙ ወደ ኾነው ጌታ መመለሱን አይነግረንም፤ (ሐዋ. 1፥18)። ባልተወለደ ይሻለው ነበር የተባለውም ለዚህ ነው፤ (ማቴ. 26፥24)።

   ዛሬ ግን ይሁዳ ሲረገምና በብዙ ሲኰነን እንሰማለን፤ ወንድማቸውን ባለመውደድ፣ በሰው ልጅ መካከል ልዩነት በማድረግ፣ በሐሰት ክስና ምስክርነት የታወቁ፣ ልዩነትን በወንድማማች መካከል በመዝራት የሚተጉ … ደርሰው ይሁዳን ሲወቅሱ እናያለን፤ ነገር ግን ይሁዳን ከመውቀስና ከመክሰስ፣ ለራሳችን ፈጥነን ንስሐ ብንገባና እግዚአብሔር በክፉዎች እንኳ ዐሳቡንና ዕቅዱን እንዴት እንደሚፈጽም ልናደንቅ ይገባናል። ይህ የእግዚአብሔር አደራረግ ፈጥነን ንስሐ እንድንገባ እንጂ፣ ከዘላለም ያቀደውንና ያሰበውን ለመፈጸም የሄደበትን መንገድ መኰነን የሚገባ አይደለም።

   የምንከሰው የለንም፤ እኛም በዚያ ዘመን ኖረን ቢኾን ወይም ኢየሱስ አኹን ባለንበት ዘመን መጥቶ ቢኾን ከመስቀል የምንመለስ አይደለንም፤ ክፋታችን ስል፣ ዓመጻችን ጽኑ ነውና፤ እንዲያውም በዚያ ዘመን የጌታ ልብ ያልያዙቱ እንዲህ ማድረጋቸው አይደንቅም፤ ዛሬ የጌታን ልብ ይዘናል የምንል እንዲህ መራርነታችን መብዛቱ እጅግ ይደንቃል! ደግሞስ እኛ መርገም የተወገደልን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የጸደቅን፣ ክብርና በረከት የበዛልን ሌላውን እንረግም ዘንድ ይገባናልን? በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ሌላውን ትረግም ዘንድ የሚገባት አይደለም፤ “የሚረግሙአችሁን መርቁ” ብሎአልና (ማቴ. 5፥44)፤ እርሱም እንኳ ለሰቀሉት ምሕረትን እንደ ለመነ አንዘንጋ፤ (ሉቃ. 23፥43)። አዎን፤ በፈቃዱ የሞተልንን ጌታ ከማምለክና ከመወደስ በቀር ሌላ ሥራ የለንም፤ አሜን ኢየሱስ ሆይ! እንወድስሃለን፤ አሜን። 

3 comments:

  1. Yihudan degefkew demo

    ReplyDelete
  2. የዩዳ ጠበቃ ነኝ አልክሳ

    ReplyDelete
  3. ብዙ ተሀዲሶና ፕሮቴስታንት አንተን ጨምሮ ኦርቶዶክሳዊነትን በጅምላ እንደምትፈርጁት ሊሆን ይችላል፡፡ ተንኳስሽ የሆነ አካሄድና ማላገጥ ለዚህ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል ባምንም በኦርቶዶክሳዊነት እይታ ግን በምንም መስፈርት ትክክል ሊሆን አይችልም፤ መደረግ አለበት ብዬ አላምንም፡፡ ወደዚህ ድርጊት ገፊ የሆኑ ድርጊቶች ግን ከላይ ከጠቀስኳቸው አካላት በየቀኑ የምንሰማቸው ነገሮች ሊያጋልጥ የሚችል እንደሆነ እገምታለሁኝ፡፡ ትርፉ ሁሉም ኃጢአት መሆኑ ነው፡፡

    ReplyDelete