Monday 6 April 2020

ኒቆዲሞስ - የሰው ጽድቅ ሽማግሌ - የኢየሱስ ሕፃን

Please read in PDF
  በዓቢይ ጾም ውስጥ ስያሜ ከተሰጣቸው ሳምንታት፣ ያለንበት ሳምንት ኒቆዲሞስ ተብሎ ይጠራል። ታሪኩ የሚገኘው በዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 3፥1-21 ባለው ክፍል ውስጥ ነው። ኒቆዲሞስ በትውልዱ አይሁዳዊ ቢኾንም፣ ስሙ ግን የግሪክ ስም ነው። አይሁዳዊ ኾኖ፣ የግሪክ ስም መያዙ በራሱ ያስደንቃል፤ አሕዛብን አጥብቀው ከሚንቁና ከሚጠሉ ፈሪሳውያን መካከል መገኘቱና አለቃቸው መኾኑ ደግሞ፣ እጅግ አስደማሚ ነው። በክፉዎች መካከል፣ ከክፉዎች መካከል የተገኘ ደገኛና የሰላም ሰው ነበር። ይህ ብዙ ጊዜ ሲኾን አይታይም።


  ኒቆዲሞስ፣ በዚያ ዘመን ቍጥራቸው ሰባ ከነበረውና ከታወቁ የአይሁድ ሸንጎ ወይም ስመ ጥር ዳኞች[ሲንሃድሪየም] መካከል አንዱ ነው፤ በዚህም እጅግ ከፍ ያለው የዚያን ዘመን ቁንጮ ሥልጣን፣ በእጁ ነበር ማለት ነው፤ በሌላ ንግግር አንዱን የአይሁድ የጸሎትና የቅዱሳት መጻሕፍት ማንበቢያ ምኩራብ፣ አለቃና መሪ ሳይኾን አይቀርም። ምናልባት ዮሐንስ ወንጌላዊ በዚያ ዘመን ይኖሩ ከነበሩ አይሁድ መካከል፣ የትክክለኛ አይሁድ ሕይወትን በተመለከተ በምሳሌነት ያቀረበው እንደ ኾነ ማስተዋል ይቻላል።

  በአይሁድ ዘንድ ኒቆዲሞስ፣ በጽድቅም በሥልጣንም ጫፍ ላይ ነበሩ ተብለው ከሚታመኑ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ኒቆዲሞስ ስመ ማዕረጉ ብዙ ነበር፤ የእስራኤል መምህር (ቊ. 10)፣ የአይሁድ አለቃ (ቊ. 1)፣ ከታወቁ ካህናት መካከል አንዱ (7፥50) ነበር። ያለበትና የያዘው ሥልጣን ማንኛውም አይሁዳዊ ሊደርስበት የሚመኘውና እንዲኾንለት በብርቱ የሚተጋለት ስፍራ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ሕጉን ያጠናው ከታወቁ ራቢዎች መካከል፣ ከገማልያል እንደ ነበር አንረሳውም፤ (ሐዋ. 22፥3)። ኒቆዲሞስ በጊዜው የያዘው ማዕረግና ሥልጣን  ከእነገማልያል እንደ አንዱ የሚቈጠር ነበር።

  በሰው እይታ ወይም የጽድቅ ሚዛን የመጨረሻና ብቁ የተባለው፣ በጌታ ኢየሱስ ዘንድ፣ ምንምና ፍሬ አልባ፣ ጨርሶውኑ ባዶ እንደ ኾነ ለማሳየት ኒቆዲሞስ ኹነኛ፤ ልከኛም ምሳሌ ነው። ክፍሉ የሚጀምረው ኒቆዲሞስ፣ በአይሁድ ዘንድ ቁንጮና ብቁ ተደርጐ መቈጠሩን፤ ነገር ግን በኢየሱስ ዘንድ የኹሉ ነገር ጀማሪና ጨርሶውኑ እንዳልተወለደ ሕፃን መኾኑን በማሳየት ነው። በዚያ ዘመን ለነበሩት አይሁድ ትልቅ ምሳሌ ቢኾንም፣ ለኢየሱስ ግን ገና መንፈሳዊ ነገር ያልጀመረ ፍጹም ሥጋ ብቻ ነበር።

  በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ብቁ እንደ ኾኑ የሚያስቡ ሰዎች፣ እንደ ገና “ሀ” ብለው ወይም “፩” ብለው መጀመር እንዳለባቸው ለማስተማር፣ ጌታ ኢየሱስ ኒቆዲሞስን ሲጠቀምበት እናያለን። ኒቆዲሞስ በሰው ዘንድ የሚታይ ሙሉውን ሃይማኖታዊነት በመፈጸም ግንባር ቀደም ነው፤ በሰው ዘንድ ሃይማኖታዊ የነበረው ተግባር ግን፣ አንድን ሰው እንደ ሕጉ ያለ ምስክር ወይም ምክንያት ከመግደል የሚያደርስ ነበር፤ ራሱ ኒቆዲሞስ እንደ ተናገረው፣ “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” (7፥51) እንዳለው። የጊዜው እጅግ የሃይማኖት ቀናተኞች ኢየሱስ የገደሉትና ድኾችን ፈጽመው የተጠየፉት በሰው ዘንድ ሲታይ የላቀ ሃይማኖተኞችና ጻድቃን ነበሩ።

   የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስን ሳያዉቁ፣ የፈለገውን ያህል ሕጉን ቢፈጽሙ፣ የሃይማኖትን ሥርዓት ቢፈጽሙ፣ ለመልካም ነገሮች ኹሉ ምንም ያህል ታማኝ ቢኾኑ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ አንዳች ተቀባይነት የለውም። ሕግጋትንና የሃይማኖት ተግባራትን በመፈጸም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይቻልም። የጽድቅም የበጐነትም የመልካም ነገርም ኹሉ ማዕከል ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው። የጽድቅም፤ የበጐነትም፣ የመልካምነትም ኹሉ ምንጭ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን ለመቀበል ያዘጋጀው የጽድቅ መንገድ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ያለ ክርስቶስ የትኛውም መልካምነትና ሃይማኖታዊ ተግባር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አያደርስም።

  ኒቆዲሞስ፣ በሰው ዘንድ ከሚታይ ሃይማኖታዊ መልካምነት ወይም ምግባራዊ ደግነት ባሻገር፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን”፣ የሚል ጠንካራ ምስክርነትም ነበረው፤ ነገር ግን እንዲህም ቢመሰክር እንኳ፣ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት በቂና አስተማማኝ አልነበረም። ምስክርነቱ ትክክል ነው፤ ነገር ግን ፍጹም አላመነበትምና ከኢየሱስ ጋር አያኖረውም፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አያስገባውም።

  ለምናምነው መኖር ከማወቅ ያልፋል፤ ብዙዎች ያውቃሉ፣ ነገር ግን ላወቁት እውነት አይኖሩም፤ ብዙዎች ኢየሱስ ጌታ እንደ ኾነ ያምናሉ፣ በጌትነቱ ጥላ ሥር ግን ኹለንተናቸውን ማሳለፍና ማስገዛት አይፈልጉም። ጌታ ኢየሱስ ኒቆዲሞስን፣ እንደ ሕፃን ዳግመኛ መወለድ አለብህ ሲለው፣ የያዘውን ሃይማኖታዊ ትምክህትና ሰዋዊ ጽድቅ እርግፍ አድርጐ መተው እንዳለበትም ጭምር እያስተማረው ነበር። ኢየሱስን በማመን መዳንና ማረፍ ዳግም ልደት ወይም ከሰማይ መወለድ ነው።

  የወደቀ ዓለም ለተባለው የሰው ልጅ፣ ብቸኛ የመዳን ተስፋ፣ የመዳን መንገድ፣ የድኅነት ምክንያት … ከሰማይ መወለድ ወይም ዳግመኛ መወለድ ነው፤ እርሱም ክርስቶስ የእግዚአብሔር እንደ ኾነ በማመን የሚገኝ ፍጹም ዘላለማዊ ደስታ ነው። በሰው ጽድቅ በመታጀል አትታበዩ፤ አትገበዙ፤ አትጃጃሉ፤ ይልቅስ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስን በማመን ዳግመኛ ተወለዱ፤ ሕፃናትም በመኾን የእግዚአብሔርን መንግሥት ውረሱ፤ ከሰማይም ወይም ከላይ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጆች ኹኑ!

ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፤ አሜን።

1 comment: