Friday, 24 April 2020

ቅንነት ጥሎ፤ ዘፈን አንጠልጥሎ!

Please read in PDF
    ተኩላው ወደ በጐች ጐረኖ መሰስ ብሎ ሲገባ፣ ዝም ማለት ወይም ባላየ ማለፍ “ተለመደ”፤ የእግዚአብሔርን ምሕረት አስታክኮ፣ ኀጢአትን “ምን አለበት?” እያሉ ማላመድ የለቀቅተኛ ነገረ መለኮታዊያንና በሰልን ባይ አማኝና አገልጋዮች መገለጫ ኾነ፤ ኀጢአትን መጠየፍ አጉል አክራሪነት ተባለ፤ ኀጢአተኝነትን መካድና መቃወም ተቃዋሚነትና ከሳሽነት ተብሎ ተፈረጀ፤ ግብረ ሰዶማዊው አገልጋይ ሲሰብክ፣ “መጀመሪያ ንስሐ ግባ!” ማለት ግብዝነትና ማካበድ ኾነ፤ በተቃራኒው ደግሞ ዘፋኝነት ከመዝሙርነት ሲጣባ መንፈሳዊ ግልጋሎት፣ ኢየሱስን የሚጋርድ ተግባር ትክክል፣ የተሰቀለውን ክርስቶስ የሚሸቅጥ ተግባርና ዐሳብን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለማድረግ ጥቅሶችን ማስጨነቅ ተወደደ፤ ተኩላውን ከመንጋው ማላመድ “ካውንስል” ተብሎ ተሞገሰ፤ ኢየሱስ ሳይኾን ቡድንና አገልጋይ ነኝ ባይ በሰው ልብ ገነነ፤ ለቀቅተኞች ቤተ ክርስቲያንን ንብ የማር ቀፎን እንደሚከብብ ከበቡአት። 


ቅዱስ ጳውሎስ፣ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ቅንነታቸውን እንዳይለወጥ በማስጠንቀቂያ ይናገራል፤ እንዲህ በማለት፣ “በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ።” (2ቆሮ. 11፥2-4)።

  ቅዱስ ጳውሎስ፣ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ጭንቀቱ የተገለጠ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ እስከ ክርስቶስ መምጫ ቀን ድረስ “እንከን አልባ ንጽሕት” ኾና እንድትቆይ ነው። ጽኑ መሻቱ፤ ብርቱ ፍላጎቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለክርስቶስ ፍጹም ታማኝ ኾና ትቆይ ዘንድ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ፍርሃት አለበት፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ በዚህ ቅድስናና ንጽሕናዋ፣ ከሐሰተኛ መምህራን የተነሣ እስከ መጨረሻ አትቆይም የሚል ፍርሃት። እንዲያውም በእንግዳ መንፈስና ልዩ ወንጌል ሌላ ኢየሱስ በመካከላቸው ሲሰበክ፣ ቆሮንቶሳውያውን ለዘብ ያለ መንፈስና ዐሳብ አሳይተዋል፤ ለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ “ትታገሡታላችሁ” በማለት ወቅሶአቸዋል።

   ሌላውን ኢየሱስ፣ በልዩ መንፈስና በልዩ ወንጌል የሚያስተምሩትና የሚሰብኩት የስህተት መምህራን፣ አገባባቸው ቀላልና ትኩረትን የማይስብ ነው፤ ይኸውም ሃሳብን ማበላሸት። ቆሮንቶሳዊነት የግሪካዊነት ተጽዕኖ አለበት፤ ግሪካዊነት ደግሞ እንግዳና ልዩ ነገር መስማት ያስደስተዋል፤ እናም ቆሮንቶሳውያን አስቀድሞ ካገኙት መንፈስ፣ ጳውሎስ ከሰበከላቸው ወንጌል የተለየ ወንጌል ሲመጣ፣ ታግሠው የመስማት ጠባይ ታይቶባቸዋል። እናም ይህን ቅዱስ ጳውሎስ “ለምን?” ይላቸዋል፤ ምክንያቱም እርሱ ለወንጌሉ ተቀናቃኝ ዐሳብ ፈጽሞ አይተኛምና።

  ቆሮንቶሳውያን፣ ለአንድ ወንድ እንደ ታጨች ድንግል ሴት ክርስቶስ እነርሱን ለአንዱ ሙሽራ ለክርስቶስ  ለይቶአቸዋል፤ እንደ ንጽሕት ድንግልም ለሐሰተኛ ትምህርት ያልተበረዘ ማንነት ያላቸው ናቸው፤ ነገር ግን ይህን ቅንታቸውንና ንጽሕናቸውን የሚያበላሽ ተግባር የሚሠሩና በመካከላቸው እየተሹለከለኩ ካገኙት መንፈስና ከተሰበከላቸው ወንጌል የተለየውን የሚሰብኩትን ተንኮለኛና አታላይ ሠራተኞችን ከመቃወም ይልቅ ዝም ማለታቸው አግባብ አልነበረም።

   አገልጋይ ነን ባዮቹ የሚጠቅሱት ወንጌል፣ የሚናገሩበት መንፈስ አላቸው፤ ነገር ግን እውነተኛውን ክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም፤ ምክንያቱም፦

1.      ትምህርታቸው ዐሳብን በማበላሸት ከቅንነት ያወርዳል፤ ቅንነት ቀጥተኝነት ነው፤ ለክርስቶስ ብቻ መኖር። ክርስቶስን ብቻ መከተል፤ የእርሱን ቃሎች ብቻ መስማት፤ ለእርሱ ቃሎች ብቻ መታዘዝ። የስህተት መምህራን ደግሞ ዘወትር ተግባራቸው፣ ከእግዚአብሔር ቃል በመቃረን ሰዎችን ወደ መንፈሳዊ በረዶነት መዶል፤ ከመንፈሳዊ ሙቀት ማብረድ ነው። መታጨት ለአንድ ወንድ ብቻ ነው! ሙሽራችን ኢየሱስ ብቻ ነው!
2.     ንጽሕናን ያስጥላሉ፦ ንጽሕና መለየትና ለአንድ ነገር ብቻ መኾንን ያሳያል። እኛም ቆሮንቶሳውያንም በደሙ ነጽተን ለክርስቶስ ሕይወት ትምህርት እንታዘዝ ዘንድ ለንጽሕና የተጠራን ነን፤ ሰይጣን ደግሞ ዘወትር ከዚህ ንጽዕና ሊያወርደን ተግቶ ይሠራል። ዐሳባችንን በማበላሸትም ሥራውን ይጀምራል፤ ዐሳቡ የተበላሸበት ዝንባሌው ይበላሻል፤ በሥራው ይረክሳል፤ ከንጽሕናው ይወድቃል። ሰይጣን የሚያደርገው በልዩ ወንጌልና በራሱ መንፈስ ነው። 

   አንድ ድርጊትም ኾነ ዐሳብ ለእግዚአብሔር ክብርን ካላመጣ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለቅድስና ካላነጸ፣ የተሰቀለውን ኢየሱስን በትክክል አጥርቶ ካላሳየ እርሱ ከሌላ ወንጌል፤ ከሌላ መንፈስ የተቀዳ ነው። እናም ከአዝማሪ ጋር እንዝፈን የሚሉን፣ በሥራቸው ለማን ክብርን ሊያመጡበት ይኾን? በሥራቸው ቤተ ክርስቲያን ለቅድስና ትታነጽበት ይኾንን? ደግሞስ በሥራቸው የተሰቀለው ኢየሱስ ለሰዎች ይሰበክበታልን? ይህን ማድረግ ካልቻለና ከሌለበት፣ የትኛውም ድርጊት፣ የትኛውም ትምህርት፣ የትኛውም ስብከት፣ የትኛውም ዝማሬ … ከልዩው መንፈስ ከልዩው ወንጌል እንጂ ከተሰቀለው ኢየሱስ፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ አይደለም! እናም ለቃየልና ለአቤል የኢየሱስ ቅዱስ ወንጌል እንጂ ዘፈን አልተባለም፤ ኢየሱስ ከኹሉም ይልቃል! አሜን።


1 comment: