Thursday 9 April 2020

የ“ዲያቆን” አሸናፊ መኮንን፣ አዲሱ ድርሳነ ማርያም (ክፍል ፩)

Please read in PDF
መግቢያ

  “ዲያቆን” አሸናፊ መኮንን፣ የዮሐንስ ወንጌልን እያንዳንዱን ምዕራፍ በመተርጐም፣ የዮሐንስ ወንጌልን ምዕራፍ ኹለትን፣ ኹለተኛ መጽሐፍ በማድረግ አቅርቦታል፤ ለምዕራፍ ኹለቱ መጽሐፍ፣ የሰጠው ርእስ “ቃና ዘገሊላ” የሚል ሲኾን፣ መጽሐፉ 252 ገጻት፣ አሥራ አምስት ክፍሎች[ምዕራፍ ሳይኾን] አሉት። መጽሐፉ የተጻፈው የዮሐንስ ወንጌልን ማዕከል በማድረግና “የለዘብተኞችን ንቅናቄ አራማጆችን ትምህርታቸውን እየነቀፈ” መተርጐምና ትችትን ማቅረብ እንደ ኾነ ጠቅሶአል፤ በተጨማሪም መጽሐፉ ራሱ የተወለደው፣ ከዮሐንስ ወንጌል ጥልቅ ምስጢር እንደ ኾነም ጭምር በድፍረት በመናገር።1


   የዚህ አጭር ጽሑፍ ዋነኛ ዓላማ፣ በአሸናፊ መኮንን የተጻፈው መጽሐፍ፣ የዮሐንስ ወንጌልን ማዕከል አለማድረጉንና ፈጽሞ እንግዳ፤ የጌታ ኢየሱስን ክብር በሚጋርድ መልኩ፣ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህን ክፍል በተመለከተ ከሠራችው ስህተት፣ በባሰ መንገድ የተጻፈ መኾኑን አጋልጦ ማሳየትና የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ ዐሳብ፤ የዮሐንስ ወንጌልና ቅዱሳት መጻሕፍትን ማዕከል በማድረግ ትክክለኛውን ትርጉም ማቅረብ ነው።

ጥቂት ስለ “ዲያቆን” አሸናፊ መኮንን የትርጉም ሥራ መግቢያ

    የመጽሐፉ ትርጉም መግቢያ የሚጀምረው[2] በጐጃም አገር እንደ ተፈጸመ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ጻድቅና ፍቅር የመኾኑን ባሕርይ ከሚቃረን ተረት ነው። ተረቱ፣ እግዚአብሔር ሰባት ልጆች ካሏት እናት ይልቅ፣ አንድ ልጅ ባላት መጨከኑንና ይህችው አንድ ልጅ የሞተባት እናት፣ ሰባት ካላት አንዱን እንኳ ሳይገድል ቀርቶ፣ የእርሷን አንድ ልጅ በመግደሉ፣ “የሴት ልጅ ፍርድ የማታውቅ” በማለት በኢየሱስ ስትበሳጭ ሳለ፣ በአቅራቢያዋ ያለው የማርያም ቤተ ክርስቲያን ተቃጥሎ፣ ሰዎች እሳቱን ለማጥፋት በብዙ ቢጥሩም፣ ነገር ግን ባለመቻላቸው ቤተ ክርስቲያኑ ነዶ በማለቁ ምክንያት፣ እርሱም በእርሷ ሲቀልድ፣ እንግዲህ እናትህ ተቃጥላ አራለችና፣ “አንተም መከራህን ቅመሰው” በሚል ዋዘኛ ተረት ይጀምራል።

   በኢየሱስ የጽድቅ ሥራ ውስጥ ኀጢአተኞችን ሲወድ፣ ከኀጢአትና ከኀጢአተኝነት ጋር የተዛመደበትን አንዲት ዘለላ መስመር አናገኝም። ጭከናው፣ “የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት በሚንቁትና በልበ ደንዳናነት ንስሐ ከመግባት በጠነከሩት ላይ ነው፤ (ሮሜ 2፥4-5)። ንስሐ ሊገቡ ባልወደዱት ላይ ሲጨክን፣ ፈታሒ በጽድቅ ነው፤ ንስሐ ሊገቡ ወደው ፍቅሩን ለተጠለሉ ደግሞ፣ እርሱ እጅግ የተትረፈረፈ ምሕረትና ይቅርታ አለው እንጂ፣ ሰባት ልጀች ካሏት ይልቅ አንድ ያላትን በመግደሉ ጭከናው፣ የአንዲቱን ትቶ ከሰባቱ አንዱን በመግደል ምሕረቱን አይገልጥም። ይህን ባለማድረጉም በሕንጻ መቃጠል አንጀቱ የሚያርር፣ አምላክና አባት የለንም፤ እንዲህ የሚያስቡና የጨዋ ተረቶችን ለትርጓሜ ከመጠቀም ዓይናቸውን የማያሹ፣ ኹለቱም የጠራ ጨዋዎች ብቻ መኾናቸውን ነው።

የ“ዲያቆን” አሸናፊ፣ የዮሐንስ ወንጌል ዓላማ

    “ዲያቆን” አሸናፊ፣ የዮሐንስ ወንጌልን ዓላማን፣ እንዲህ በማለት ያስቀምጠዋል፤
1.“የእመቤታችን የድንግል ማርያምን የእምነት ጸሎት ለማብራራት”፣[3]
2. “የለዘብተኞችን ንቅናቄ አራማጆችን ትምህርታቸውን መንቀፍ፣ እመቤታችን ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ መሆኗን” ለማብራራት፣[4]
3. “ስለ ክብሩ ለመናገርና”
4. “የደቀ መዛሙርቱን ማመን ለመግለጽ ነው” [5]ይላል።

    እኒህ ዓላማ ተብለው የቀረቡት የግል ዐሳቦች፣ በደራሲው ኾን ተብለው የተዘጋጁ ብልሃታዊ ተረቶች እንጂ፣ ከወንጌልም ይኹን ከታሪክ አንዳችም ማስረጃ ማቅረብ የሚቻልባቸው አይደሉም። በተለይም በአንደኛና በኹለተኛ ደረጃ የተጠቀሱት ዓላማዎች፣ በወንጌሉ ውስጥ አሉ ወይስ ወደ ወንጌሉ እንዲገቡ (እንዲሰግጉ) የተደረጉ ባዕድ ዐሳቦች ናቸው? የሚለውን በጥንቃቄ መመርመርና አስረግጦ መልስ መስጠት ይሻል።

ትክክለኛው የዮሐንስ ወንጌል ዓላማ

1. ራሱ ቅዱስ ዮሐንስ፣ የወንጌሉን ዓላማ ፍንትው አድርጐ ያስቀምጥልናል፤ “ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።” (ዮሐ. 20፥30-31) በማለት፣ የወንጌሉን መጻፍ ዋና ዓላማ ይነግረናል፤ ይህ የወንጌሉ ዋና ዓላማ ለኹሉም የወንጌሉ ምዕራፎች የማይለወጥና ወጥ ነው፣[6]

  የወንጌል አንድምታውም፣ “ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ እንደሆነ እናንተ ታምኑ ዘንድ ከተአምራቱ ይህ ተጽፏል። ስሙ ሕይወት መድኃኒት እንደሆነ አምናችሁ የዘለዓለም ድኅነትን ታገኙ ዘንድ።” [7] ሲል፣ ማኅበረ ቅዱሳን እንኳ ከዚህ እውነት ሳይዛነፍ፣ “የመጽሐፉ ዋና ዓላማ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ኾነ[ኢየሱስ የተባለው ክርስቶስ እንደሆነ] እናምን ዘንድ አምነንም በስሙ ሕይወት ይሆንልን[እናገኝ] ዘንድ ነው።” [8] በማለት ቁልጭ አድርጐ ያስቀምጣል።[9]

  በዮሐንስ ወንጌል የተጠቀሱት ሰባቱም ተአምራት ወይም ምልክቶች ይህን እውነት በትክክል ያሳያሉ። ኹሉም ወንጌላት ትኩረታቸውና ሊያሳዩት የሚፈልጉት ዋና ነገር፣ የክርስቶስን ሕይወትና ትምህርት ለማመንና ለሕይወት ይኾነን ዘንድ ነው። ለዚህም ነው፣ በወቅቱ የተከናወኑትን ተግባራት ኹሉ ከመዘገብ ይልቅ፣ ዋና ትኩረታቸውን ምን እንደ ተፈጸመና ለምን እንደ ተፈጸሙ ከማብራራቱ ላይ ያደረጉት። ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ፣ ረጃጅም ውይይቶችና ንግግሮችን፣ የተመረጡ ተአምራትን ሲጽፍልን ዋና ዓላማው ክርስቶስ ኢየሱስን እጅግ በማጕላት ሌላውን ኹሉ ማደብዘዝና ማሳነስም ነው።

  ለዚህ አንድ ጕልህ ማሳያ ምሳሌ ብንጠቅስ፣ “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል” (ዮሐ. 3፥30)፤ “ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው፦ ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ አሉ። በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።” (ዮሐ. 10፥41-42) የሚለውን ብንወስድ፤ ወንጌላዊው ዮሐንስ፣ መጥምቁ ዮሐንስ አንዳችም ተአምር አለማድረጉን ይነግረናል፤ እልፍ አእላፍ ተከታይ ያለው፤ በነገሥታት ዘንድ የተፈራውና የታወቀው መጥምቁ ዮሐንስ፣ አንዳችም ተአምር አላደረገም፤ ምክንያቱም ኢየሱስን እንዲጋርድ አይገባም፤ ብርቱው አገልጋይ እጅግ ሊያንስ፤ ሊዋረድ ይገባዋልና፤ ኢየሱስ ብቻ ሊልቅና ሊገንን ይገባዋልና።

   እንግዲህ፣ ጠቅላላው የዮሐንስ ወንጌል ዓላማ፣ በእነዚህ ኹለት ታላላቅ ዓላማዎች የተቀነበበ ነው። በአንደኛው ዓላማ ሥር ኹለት ታላላቅ ዓላማዎች አሉ፤ እኒህም “ማመንና ሕይወት” የሚሉ ናቸው። “እንድታምኑ” በሚለው ዐሳብ ውስጥ፣ “ማመን እንድትጀምሩና በእምነት ጸንታችሁ እንድትኖሩም በማለት የሚያሳስብ” ሲኾን፣ “በስሙ ሕይወት ይኾንላችሁ ዘንድ” የሚለው ደግሞ፣ “በስሙ በመታመን ከአብና ከወልድ ጋር ባለው ኅብረታዊ ሕይወትነት እንድትኖሩ” የሚል ነው፤ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” እንዲል፤ (ዮሐ. 17፥3)።

2. የወንጌሉ ኹለተኛ ዓላማ ብለን ብንወስድ፣ በወንጌሉ መጻፍ የተጋለጡ አንዳንድ ኑፋቄያት አሉ፤ ምክንያቱም ወንጌሉ ለግሪክ ማለትም ለኤፌሶን እንደ መጻፉ መጠን፣ ኖስቲሳውያን(Gnostism)፣ ጌታ ኢየሱስን “ሰው ብቻ”(mere man) ነው ብለው ያስተምሩ የነበሩ ኢቦናውያንና(Ebionites) ኩሪንቱስ(Corinthus) [10] ኑፋቄአቸው በአደባባይ ተጋልጦአል። አኹንም ግን አጽንተን የምንናገረው፣ የወንጌሉ ዋና ዓላማ ሰዎች እንዲያምኑና አምነውም በስሙ ሕይወት ይኾንላቸውም ዘንድ ወይም በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ ነው። እግረ መንገድ ግን እኒህን ኑፋቄያትም ደፍጥጦአቸዋል፤ ቅዱሱ ወንጌል።

ይቀጥላል …
1. ገጽ 21 እና 22
2. ገጽ 16
3.  ገጽ 65
4.  ገጽ 21
5.  ገጽ 66-7
6. የመጽሐፍ ቅዱስ መደበኛ ትርጉም፤ ገጽ 1585፤ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፤ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ 1992 ዓ.ም፤ ባናዊ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 223፤ ምሉዕ ሕይወት መጽሐፍ ቅዱስ፤ ገጽ 1596፤ Merrill C. Tenney; THE EXSPOSITOR’S BIBLE COMMENTARY; 1981; Vol. 9; Printed in USA; A Zondervan Publication; pp. 10-1
7. ወንጌል አንድምታ፤ 1997 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 471
8. ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ፤ ትምህርተ ክርስትና፤ 1979 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 93
9. ቤተ ክርስቲያንህን ዕወቅ፤ 1992 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ብራና ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 77
10. Mattew Henery; Commentary on the Whole Bible Volume V; Publisher: Grand Rapids, MI: Christian Classics Ethereal Library; p. 847

11 comments:

  1. አቡ ግሩም ምልከታ ነው እንዲህ መች መስሎን

    ReplyDelete
  2. አቤ ተመችቶኛል እይታህ ይበል ነው

    ReplyDelete
  3. ብዙ ሰዎች አሁንም ጽሑፎቹን ያነባሉና ትኩረት ሰጥተው እንዲያዩት ጥሩ ጥቆማ ይሆናል።

    ReplyDelete
  4. Yehone neger ale silent man semagn Geta gaze slew laka

    ReplyDelete
  5. አረ ጉድ ነው።በጣሞ ያሳፍራል እንዲ ከጻፈ

    ReplyDelete
  6. ተባረክ ተወዳጁ:: አቢየ ኒቆዲሞስ በሚለው መጽሐፉ ላይ ደግሞ ስለ ዳግም ልደት የጻፈው ነገር ትክክል አይመስለኝም:: ከሰሞኑ ከደረሱኝ የቴሌግራም መልዕክቶች መካከል አንዱ... የእሱ ተማሪ ነኝ / መንፈሳዊ አባቴ / የምትል ልጅ በዉሃ ጥምቀት ስርአት ነው ሰው ዳግመኛ የሚወለደው ብላኝ የበለጠ ሃሳቡን እንድረዳው የእሱን መጽሐፍ ኒቆዲሞስን ነው የጋበዘችኝ:: እኔ ክፍለ ሃገር ስለሆነ ያለሁት መጽሐፉን አግኝቼ ለማንበብ አልቻልኩም:: እየው እና በዚህኛውም መጽሐፍ ላይ (ኒቆዲሞስ) ሂስህን መስጠት ቀጥል::

    ReplyDelete
  7. በጣም አፈርኩለት

    ReplyDelete
  8. Wey ashenaffi endih hone bemecheresha.Geta yirdaw

    ReplyDelete
  9. “አንተም መከራህን ቅመሰው” በሚል ዋዘኛ ተረት ይጀምራል። በተራችን ወዘባች

    ReplyDelete
  10. እንዲ የዘቀጠ ሰው ነው እንዴ ምን ሆኖ ነው ግን ያሳዝናል

    ReplyDelete
  11. አይ ሰው ትንሽ ነገር ሲገኝ ሆይ ሆይ ማለት ብቻ ህፀጽም የለበት ሁሉ አስተማሪ ነው ነገር ግን ቢገኝበት እንኳን እንፀልይ ይባላል እንጂ ባንዴ ሆያ ሆዬ ውይ ሰው የበላበትን ወጭት ሰባሪ እግዚኦ እኔስ ብዙ ተምሬበታለሁ የአገልግሎት ዘመንህን ይባርከው መምህሬ በፀጋ ላይ ፀጋ ይጨምርልህ መምህሬ፡፡ የዚህ ምድር ጉድ እንደሆን አይልቅም አደራ በጠፈጣሪ ስም ቀጥል እንዳታቆም አደራ አደራ አደራ፡፡

    ReplyDelete