Wednesday, 15 April 2020

መሲሑ ሲደነግጥና ሲያጣጥር!

Please read in PDF
   ከኢየሩሳሌም ከተማ በቄድሮን ወንዝ ማዶ በደብረ ዘይት ግርጌ ባለው የአትክልት ስፍራ፣ ጌቴሴማኒ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ፣ ሐሙስ ማታ፣ “የናዝሬቱ ኢየሱስ … በተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ … የተገለጠው ሰው” (ሐዋ. 2፥22)፣ “ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር” (ማቴ. 26፥37)። ጌቴሴማኒ መልካሙና መሃሪው ጌታ ኢየሱስ ስቃዩን የጀመረበት ስፍራ ነው፤ ስለ ሰው ልጆች ኀጢአትና በደል፣ እርሱ የምድርና የሰማይ ሐዘንና ትካዜ በእርሱ ላይ ወረደ፤ በዚያም ሌሊት ብቻውን ተሳቀየ።
   


 ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ፣ “በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር፤ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ” (ሉቃ. 22፥44)፤ ማርቆስም፦ “እጅግ ያዝን ይጨነቅ ጀመር። ደግሞም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤” (ማር. 14፥33-34) ይላል፤ በዚያች ሌሊት ጌታ ኢየሱስ፣ እጅግ ከፍ ባለ ውጥረትና ጭንቀት እንዲሁም ድንጋጤ ውስጥ ነበር። መንፈሳዊ ስቃዩ እጅግ ጠንካራ ነበር። የወደቀውን ዓለም ኀጢአት ተሸክሞ ነበርና።


  ኀጢአትን የተሸከመ ብቻም አይደለም፤ በእግዚአብሔር አምላክ ዘንድ ስለ ኀጢአተኞች እንደ ፍጹም ኀጢአተኛ ተቈጥሮም ነበር፤ ስለዚህም አባቱ ፊቱን አዞረበት፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ኀጢአትን አያይምና፤ ከዚህም የተነሣ ጌታ ኢየሱስ በላብና በደም ተነከረ፤ በጭንቀትና በድንጋጤ ተከበበ፤ እንዲያውም ሉቃስ አያይዞ እንዲህ ይላል፣ “ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታ መልአክ ታየው” (22፥43)። የኀጢአት ድካም የወረሰው ዓለም ይበረታ ዘንድ፣ ሃያሉ ፍጹም ደከመ!


  የምድር በፀሐይ ብርሃን እጦት መጨለም ሳያንስ፣ በጌታ ኢየሱስ ሰማይም ፊቱን ዘወር አድርጐበት ነበር። “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።” (2ቆሮ. 5፥21) እንዲል፣ ስለ እኛ ፍጹም ኀጢአተኛና እንዲሁም፣ “በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ” (ገላ. 3፥13) በመስቀል ላይና በዚያን ምሽት ታየ።

 
የምድር በፀሐይ ብርሃን እጦት መጨለም ሳያንስ፣ በጌታ ኢየሱስ ሰማይም ፊቱን ዘወር አድርጐበት ነበር። “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።” (2ቆሮ. 5፥21) እንዲል፣ ስለ እኛ ፍጹም ኀጢአተኛና እንዲሁም፣ “በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ” (ገላ. 3፥13) በመስቀል ላይና በዚያን ምሽት ታየ።

    እንዲህ ባለ ኹኔታ ሳለ፣ ማንም ሊያየው አልወደደም፤ በተለይም ደግሞ በመስቀል ላይ በውርደት ስቅለት ሳለ የሚያጽናና አልነበረውም። እጅም መልካም የኾነው ፍጹሙ ሰው፣ በድንጋጤና በጭንቀት እንደ ተከበበ በመስቀል ላይ ይዋረድ ዘንድ ተሰቀለ፤ እንደ ክፉ ወንጀለኛ “በሞት ጣር” ተያዘ፤ (ሐዋ. 2፥24)። ፍርሃት የባሕርይ ገንዘባችን እስኪመስል ተጣብቶን ለነበርን ለእኛ፣ ፍርሃት የሌለበት እርሱ በፍርሃት ተጣጣረ። የእግዚአብሔርን ፍቅር በመግፋት አቻ የማይገኝልንን ክፉዎችን ያድን ዘንድ፣ እንደ ክፉ ወንጀለኛ ብቻውን በጌቴሴማኒ መከራን ተቀበለ።

   ያሳርፈን ዘንድ በፈቃዱ በምጥ ጣር ተያዘ፤ ድንጋጤና ጭንቀትን ገንዘቡ አደረገ፤ ያከብረን ዘንድ በውርደት ሞት በመስቀል ተሰቀለ፤ ደፍረን ወንጌልን እንመሰክርና ፍቅሩን ለኀጢአተኛው ዓለም እንናኘው ዘንድ እርሱ እያጣጣረ ፈራ፤ የማይሞተው ሕይወት እኛን ሙታንን ለማዳን ሞተ፤ ሞትን የሚውጠው እርሱ ኹለንተናው በደምና በላብ ተዋጠ፤ የሞቱ ሰዎችን ያስነሣና ሕይወትን የሰጠ እርሱ ሞተ፤ አምላክ ስለ ፈጠረው ሰው በፍርሃት አጣጣረ፤ ያድነውም ዘንድ እንደ ደካማ ሰው የሚያበረታው መልአክ መጣለት።

   “በነፍስ በሥጋ የሚፈርድ እርሱን ይሞት በቃ ወደ ሚፈረድበት አደባባይ አወጡት፤ ሊቃነ መላእክትን ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛ እርሱ በኃጥአን እጅ ተያዘ፤ ሕይወት እርሱ ሞተ።” (የኑሲሱ ጎርጎርዮስ ሃይማኖተ አበው ምዕ. 35 ክፍል 3 ቊጥር 34 ገጽ 122)

   እንዲህ ባለ መከራ አዳነን፤ እንዲህ ባለ ትድግና ነፍሳችንን በፍቅሩ ማረከ፤ የፈራውና ያጣጠረው ጌታ፣ የደነገጠውና የተጨነቀው መሲህ ሞትን ረትቶ ሕይወትን ሰጠን፤ ስለ ፍርሃቱ የሚያበረታታ መልአክ የመጣለት እርሱ፣ በማንም የማይገረሰስ የትንሣኤን ኃይል አለበሰን፤ በፊቱ በሞገስ እንገባ ዘንድ፣ በጲላጦስና በሄሮድስ ፊት ሞገስን አጣ፤ አቤቱ እንወድሃለን፤ እናከብርሃለን፤ ለዘለዓለምም እናመልክሃለን፤ አሜን።

1 comment: