Wednesday 22 April 2020

ተነሥቶአል!

Please read in PDF
ይህ ታላቅ ምስክር የተሰጠው ለታላቁ መሲህ ለክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ ሞት ብርቱ ሥጋ ለባሽን ኹሉ አሸንፎ ገዝቶአል፤ በጦር ሜዳ ጀግኖች የነበሩትን አርበድብዶ፣ “በውኑ ሞት እንደዚህ መራራ ነውን?” (1ሳሙ. 15፥32) በማስባል፣ በፊቱ አንበርክኮአል። ሞት ያልገዛው ብርቱ፣ ያልሻረው ኃያል፣ ያልጠቀለለው ጎበዝ፣ ያልዋጠው አለቃ፣ ያልሰበረው ጠንካራ … በምድር ላይ ከቶ አልነበረም። ሞት ወደቀውን ዓለም ተከትሎ፣ በሰው ልጆች ኹሉ ነግሦ ኖሮአል፤ “በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል” ወደ ሥጋ ለባሹ ዓለም ሰተት ብሎ ገባ፤ (ሮሜ 5፥17) እንዲል።




ኀጢአት በሞት በኩል ዓለምን ገዛ፤ አንበረከከ፤ ሰይጣን፣ የሞትን መውጊያ፣ የሲኦልን ድል መንሣት በኀጢአት ኀይል አማካይነት በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ቀረቀረ፤ ኀጢአትና በደል ለገዛው ዓለም፣ ሞት ገዢ ንጉሥ ኾኖ ገነነ፤ ላቀ። የሰው ማስፈራሪያውና መፍሪያው ሞት ኾነ። የሞት ፍርሃት ያላንበረከከው፤ ሙስና[መፍረስና መበስበስ] መቃብር ያልገዛው ማን አለ? ምድር ውጣ ያላስቀረችው ብርቱና ኀያል አንዳችም በምድር አልነበረም።

ጌታ ኢየሱስ ግን አንዳችም በደል ሳይኖርበት፣ ከቅድስት ድንግል ተወልዶ፣ ወደዚህ ምድር መጣ፤ የሰውን ልጅም ለማዳንም በፈቃዱ ሥጋን ነሥቶ፤ ከእኛ እንደ አንዱ ኾኖ የአባቱን ፈቃድ እየፈጸመ ተገለጠ፤ “የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።” (ዮሐ. 5፥30)፣ “እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና” (ዮሐ. 8፥29) በማለት፣ የአባቱን ድምጽ ብቻ ሰምቶ በመታዘዝ፣ የሰውን ልጅ ቤዛነት ፍጹም በኾነ መንገድ ፈጸመ፤ አንዳች በደል ሳይገኝበት (ዮሐ. 8፥46፤ 1ጴጥ. 2፥22) መዳናችንን ጠነቀቀ። ምንም እንኳ አንዳች በደል ባይገኝበትም፣ ክርስቶስ ኢየሱስ የሞተውና ከምድር የተወገደው እጅግ ከፍ ባለ ውርደት ነበር።

በግርፋት ይለቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ተገርፎም ተሰቀለ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ተናገረው፣ “እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም እስኪቈጠር” (53፥4) ድረስ፣ በተሰቀለ ጊዜ፣ “የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ሰድቡት” (ማቴ. 27፥39)። የኾነበት ኹሉ በእግዚአብሔር እንደ ተቀሰፈና እንደ ተጣለ ሰው እንጂ፣ በእግዚአብሔር እንደ ተወደደ ቅዱስ ሰው አልነበረም። “በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ … እስራኤልን እንዲቤዥ ተስፋ” (ሉቃ. 24፥19፡ 21) የተጣለበት ቢኾንም፣ በፍጻሜው ግን እጅግ የውርደትና (ፊል. 2፥8)፣ የተረገመ ሰው በሚሞትበት መንገድ ሞተ፤ (ገላ. 3፥13)።

 በደል ያልተገኘበት ይህ ቅዱስ ጌታ በፈቃዱ ሞተ፤ በደልና ኀጢአት የለበትምና ሞትን አልፈራውም፤ በፈቃዱ ሞተ እንጂ። ሞት በደል ያለባቸውን የአዳምን ልጆች አስጨንቆ ሲገድል ኖረ፤ ኢየሱስ ግን ለሞት በፈቃዱ ታዘዘ፤ እርሱ ነፍሱን በፈቃዱ አኖረ፤ ስለዚህም በፈቃዱ ማንሣትም ይቻለዋል፤ (ዮሐ. 10፥11፡ 17)። ስለዚህም ሞት በእርሱ ላይ አንዳችም ሥልጣን የለውም።

በታሪክ ያልተሰማ ታላቀወ እውነት፤ ክርስቶስ ከሙታን መካከል እንደ ተናገረው በሦስተኛው ቀን ተነሥቶአል፤ የመላእክቱ ብሥራት ይህ ነበር፤ “አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ።” (ማር. 16፥6)። እርሱ ተነሥቶአል፤ የመቃብሩ ሥፍራም ባዶ ነው፤ የኹሉም ሃይማኖት መሥራቾች መቃብር በምድር አለ፤ የክርስትናው ፈርጥና በኩር ግን ከሙታን መካከል ተነሥቶ በመቃብር የለም።

  ያለ ክርስቶስ ኢየሱስ መነሣት ክርስትና ከንቱ ነው፤ የእርሱ መነሣት ግን የክርስትና ዋናና ማዕከል ነው። እርሱ ባይነሣ ክርስትናም ክርስቲያኖችም የሉም። ስለ መዳንም የምንሰብከው ስብከት ከንቱና ደካማ ነው፤ “ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ።” (1ቆሮ. 15፥17) እንዲል። የመዳናችን የመጨረሻውና ፍጹሙ ማስረጃ፣ የእርሱ ከሙታን መካከል መነሣት ነው። እርሱ ሲነሣ አለመሞታችን ተረጋገጠ፤ እርሱ ከሙታን መካከል ሲነሣ፣ መዳናችን ተረጋገጠ፤ እርሱ ከሙታን መካከል ሲነሣ፣ ሲኦል ድል መንሣቱ ተሻረ፤ ሞት መውጊያው ተሰበረ፤ ገሃነም ደጁ ፈራረሰ፤ የኀጢአት ኃይሉ በረሰ፤ አሜን።

አሜን፤ ክርስቶስ ከሙታን መካከል ተነሥቶአል፤ የመጨረሻውም ጠላታችን ተሽሮአል፤ በእርሱ ለምናምን ኹላችን እነሆ የምሥራች! ክርስቶስ ኢየሱስ ከሙታን መካከል ተነሥቶአል! አሜን። 

No comments:

Post a Comment