Thursday 9 April 2020

የ“ዲያቆን” አሸናፊ መኮንን፣ አዲሱ ድርሳነ ማርያም (ክፍል ፪ እና የመጨረሻ)

Please read in PDF

የወንጌሉን ዓላማ በመሳት፣ በአሸናፊ የተተረጐሙ “ትርጓሜያት”


1. የሰርጉ ተቀዳሚ ዓላማ “የእመቤታችንን የድንግል ማርያምን የእምነት ጸሎት ለማብራራት ነው”[1] የሚለው፣ የዮሐንስ ወንጌል ተቃራኒ ዐሳብ ነው። “ዲያቆን” አሸናፊ፣ እመቤታችን የጸለየችው ጸሎት ተራ ጸሎት አይደለም ቢልም፣ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ኹለት ውስጥ ጸሎት መኖሩን አናነብም ወይም ወንጌላዊው ዮሐንስ፣ ቅድስት ማርያም ጸሎትን መጸለይዋን አልጻፈልንም። ይህን ለማለት አስግጎ ወይም ወደ ቃሉ በማሰገባት የተረጐመው ክፍል፣ “የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት፦ የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው።” የሚለውን አንቀጽ ነው፤ (2፥3)።[2] ጸሎት ነው ከማለት ባለፈ፣ አስደናቂ ልመና፣ የቃና ዘገሊላው ጸሎት፣ የድንግል ጸሎት እያለ ሲያሞጋግሰው እናስተውላለን። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ጸሎት ያለውን አንቀጽ፣ “እንደ ፈቃዱም የቀረበ፣ የጌታን ልብ ያወቀ ጸሎት” በማለትም ያሞካሸዋል።


    አዎን፤ የክፍሉ ፍካሬአዊ ትርጉም ይህን የሚል ነውን? ጸሎትስ አለውን? ብለን መጠየቅ ግድ ይለናል። ድንግል ማርያም በዚያ ስፍራ ቀድማ መገኘትዋ፣ ለሰርገኛው ቤተሰብ ቅርበትዋን ያሳያል። ቅድስት ማርያም፣ ለሰርጉ ቤተሰብና ለኢየሱስ ቅርብ ናት፤ አስቀድማ በዚያ ነበረችና፤ ይህ ቀረቤታዋ በጓዲያ የወይን ጠጅ ማለቁን እንድታውቅና እንድታይ አድርጐአታል፤ የወይን ጠጁን ማለቅና ለጌታ ያላትን ቀረቤታ ተገን በማድረግ፣ በቀጥታ ወደ ኢየሱስ መጥታ  ተናገረችው።

   ይህንም የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣ የዮሐንስ ወንጌልን በአንድምታ በተረጐሙት ትርጉማቸው፣ ፍንትው አድርገው ጸሎት አለመኾኑን በግልጥ በሚያመለክት ትርጉም ተርጉመውታል። ቅድስት ማርያም ለተናገረችው ንግግር[በትእዛዛዊ መንገድ]፣ ጌታ ኢየሱስ ሲመልስ እንዲህ አለ፣ “አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” ብሎአል። ይህንም ሲተረጉሙ፣

“… በአምላክነቱ አገብሮ ተአዝዞ (መገደድ፤ መታዘዝ) እንደሌለበት ለማጠየቅ። አንድም ውኀውን ጠጅ አድርጌ የማጠጣቸው በኔ ፈቃድ ነው እንጂ ባንቺ ትእዛዝ ነውን አላት።”[3]

  ከዚህ ትርጉም የቅድስት ማርያም ንግግር [ትእዛዝ አዘል] እንደ ነበር እንጂ፣ ፈጽሞ ጸሎት እንዳልነበር ማንም ሳይስተው ሊረዳው ይችላል። ድንግል ማርያም ያላትን “ልዩ” ትውውቅ(acquaints) ተገን አድርጋ፣[4] በቀጥታ ኢየሱስን ተናገረች፤ ይህ ደግሞ ፍጹም ስህተት እንደ ነበር፣ ጌታ ኢየሱስ በመለሰላት የተግሳጽ ንግግር ውስጥ እውነታውን እናስተውላለን። ይህ ተግሳጻዊ ንግግር፣ ጌታ የሚወዳቸውን ልጆቹን እንደሚገስጽበት ባለ ተግሳጽ፣ የገሰጸው ወይም የተቈጣው ቊጣ ነው።[5] በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ተግሳጽ በተመሳሳይ መንገድ ተጠቅሶ እንመለከታለን፤ (መሳ. 11፥12፤ 2ሳሙ. 16፥10፤ ዕዝ. 4፥3፤ ማቴ. 8፥29)።

   እንግዲህ ወደ ቃሉ በመተርጐም (በሰጊጎት) “ጸሎት” ተብሎ የተተረጎመውን ክፍል፣ ከመጽሐፉ ዐውድ ተነስተን እንዲህ ብለን መጠቅለል እችላለን፤

i. ኢየሱስ፣ ከአባቱ ፈቃድ በቀር የማንንም ፈቃድ አይፈጽምም ወይም ለአባቱ ፈቃድ ካልኾነ በቀር ለሌላ ለማንም አይታዘዝም። በዚህ ክፍል ድንግል ማርያምን መገሰጹ ወይም የአባቱን ፈቃድ ብቻ መስማቱ እናቱን አለማክበሩ ወይም አንዳንዶች እንደሚሉት መናቁን አያሳይም፤ ይህ ባሕርይው አይደለምና። ዳሩ ግን ይህን ያደረገው፣ ልክ ሌዊ በብሉይ ኪዳን እንዳደረገው ነው፤ እንዲህ ተብሎ ለሌዊ እንደ ተነገረ፦

    “ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፦ ቱሚምህና ኡሪምህ ለቅዱስህ ሰው ነው፥ በማሳህ ለፈተንኸው፥ በመሪባ ውኃም ለተከራከርኸው፤ ስለ አባቱና ስለ እናቱ፦ አላየሁም ላለ፥ ወንድሞቹንም ላላስተዋለ፥ ልጆቹንም ላላወቀ፤ ቃልህን አደረገ፥ ቃል ኪዳንህንም ጠበቁ።” (ዘዳግ. 33፥8-9)

    ሌዊ ለቅዱሱ አገልግሎት ሲል እናቱን፣ አባቱን አላየም፤ ወንድሞቹን አላስተዋለም፤ ልጆቹንም አላወቀም፤ ይህ ማለት ካዳቸው፤ ናቃቸው ማለቱ አይደለም፤ ነገር ግን ለሚበልጠው ፈቃድና አገልግሎት ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ አፈሰሰ እያለ እንጂ። እርሱ፤ ሴቶች ልጆቹም የሙሴን በረከት ተንከባካቢ፣ አስተማሪ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድና ኪዳን ለሕዝቡ ገላጭ፣ መሥዋዕት አቅራቢ፣ ስለ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት፣ ስለ እግዚአብሔር ደግሞ በሕዝቡ ፊት የሚቆም፣ በታቦቱ አጠገብ ለተቀመጠው መጽሐፍ ታማኝ አስተማሪና በእግዚአብሔር የተወደደ ነበር፤ (ዘሌ. 10፥11፤ ዘዳ. 31፥9-13)።[6]

ii. ለሥራዎቹ ደግሞ የማንም አማካሪና ትእዛዝ አያሻውም፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፋዊ የኾነ መሲሐዊ አገልግሎቱን ጀምሮአል፤ እንደ ሕጉ አንድ አይሁዳዊ አደባባያዊ አገልግሎትን የሚጀምረው፣ “ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ በመገናኛው ድንኳን ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡበትን” (ዘኊል. 4፥3) እንዲል፣ “ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር” ይለናል፤ (ሉቃ. 3፥23)። ስለዚህ መሲሐዊ አገልግሎቱ ከዘላለም የሥላሴ ዕቅድ ብቻ ነው፤ ከፍጡር የማንም እጅ፣ ፈቃድ፣ ዐሳብ፣ ትእዛዝ የለበትምና።

  ነገር ግን ድንግል ማርያም በንግግር ለመግባት ያሰበችው፣ በታላቁ የሥላሴ ዘላለማዊ ዕቅድ ውስጥ ነው፤ ጌታ ኢየሱስም ይህ እንዳይኾን ተከላከለ፤ በተግሳጽ ቃል መለሰ። ብዙ ሰዎች እንዲህ ሲባል ድንግል ማርያም፣ የተዋረደች፤ ዝቅ ያለች፣ ተቀባይነት ያጣች ይመስል ይከፋቸዋል ወይም መጽሐፉን ካጻፈው ከቅዱሱ መንፈስ በላቀ ሊቀኑላት ይቃጣቸዋል፤ ነገር ግን በዚህ ስፍራ ብቻ ሳይኾን፣ ድንግል ማርያም በሌላም ቦታ ደክማና ተሳስታ እንደ ነበረች እናስተውላለን።

    በአንድ ወቅት ከአረጋዊ ዮሴፍ ጋር በመኾን፣ “እናቱም፦ ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን”፣ ላለችው ንግግር ጌታ ኢየሱስ የመለሰላት ምላሽ፣ “ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” ብሎ፣ በቸለተኝነት የተነገረውን ንግግር አርሞአል፤ ይህን ለቅድስት ማርያምና ለአረጋዊው ዮሴፍ የተናገረውን ቅዱሱ መጽሐፍ፣ “እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም።” (ሉቃ. 2፥48-50) በማለት፣ ማርያምም ዮሴፍም ምን እንደ ተናገራቸው እንኳ እንዳላስተዋሉ ይናገራል። ስለዚህ ቅድስት ማርያምን ድካም አልባና ፍጽምት አድርጐ ማቅረብ የቅዱሳት መጻሕፍት ዐሳብ አይደለም።

   እርሱ እንደ ወደደ በራሱ ጊዜ የሚሠራ እንጂ፣ ሰው እንደ ወደደ ባዘዘው ጊዜ የሚሠራ አይደለም፤ ለዚህም፣ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም” በማለት መለሰላት። አሸናፊ፣ ይህን ክፍል እጅግ ጸያፍ በኾነ መንገድ ሲተረጉመው፣ “እመቤታችን ለዓለም በገለጠችውና ተአምራት ባደረገ ቊጥር  ሞቱ እየተፋጠነ ይመጣል።”[7] ብሎአል። በእውነት አሸናፊ መኮንን፣ “የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ፦ የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ …” የሚለው ቃል፣ ለኢየሱስ መፈጸሙን አላስተዋለምን? የቀባውና ቀብቶም ለዓለም የገለጠው መንፈስ ቅዱስ እንደ ኾነ አያውቅምን? በጥምቀቱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለዓለም እንደ ገለጠው አያውቅምን? (ሉቃ. 4፥17፤ 3፥22)።

  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጊዜውን ጉዳይ ያነሳው፣ ራሱ ከወሰነውና ከሚያውቀው፣ ደግሞም አባቱ ከወሰነው አንጻር እንጂ፣ ድንግል ማርያም፣ ኢየሱስን ለዓለም ከመግለጧና ካለ መግለጥዋ ጋር አንዳች የሚያዛምደው ነገር የለም። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ጊዜን በተመለከተ የተቀመጠው፣ ኢየሱስ ወይም አባቱ ብቻ ሊያውቁት በሚችል መልኩ ነው፤ ክፍሎቹንም ብናወጣቸው፦ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፥” (7፥6)፣ “… ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ …” (7፥30)፣ “ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም” (8፥20)፣ “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል” (12፥23)፣ “ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ …” (13፥1)፣ “አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤” (17፥1) የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጊዜው የተባለው፣ ቀጥታ ከሥጋ ሞቱ ጋርና እርሱ ብቻ የሚያውቀውም ጊዜ መኾኑን ማስተዋል ይገባል።

  የክርስቶስ ሞት ከድንግል ማርያም መፈጠር በፊት፣ በክበበ ሥላሴ የተወሰነና የታወቀ፤ ዕቅድ ነው። “ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ”፣ “በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ላይ ስሞቻቸው ሲጻፍ” ከሥላሴ በቀር ማንምና አንዳች የፍጡር ወገን አያውቅም፤ (ኤፌ. 1፥4፤ ራእ. 13፥8)፤ ምክንያቱም የክርስቶስ ሞትና የእኛ መዳን የታቀደውና የታሰበው፣ የሚታወቀውም በሥላሴ ዘንድ ብቻ ነውና። ጌታ ኢየሱስ የሚሞትበትንና ራሱን በገዛ ፈቃዱ የሚሰጥበትን ጊዜ ያውቅ ነበር፤ (ዮሐ. 10፥10፡ 17-18)። የሚሞተውም በአባቱ ፈቃድና በአባቱ በተወሰነው ጊዜ (12፥49) ብቻ ነው። ስለዚህ ክርስቶስ ኢየሱስ ከአባቱ በቀር ማንንም እንዳይሰማ ተናግሮአል፤ ከአባቱም በቀር የሚሰማውና የሚያውቀውም የለውም።

2. በኹለተኛ ደረጃ ወደ ቃሉ ከተተረጐሙ ዐሳቦች መካከል፣ “… ለመናቅ የሚሹትም ጊዜው ባይደርስም ስለ ልመናዋ ውኃውን ወይን ጠጅ ማድረጉን ማሰብ ያስፈልጋቸዋል። … እመቤታችን ለቃና ሰርገኞች የለመነችውን አንድ ቀን ለራሷ ለምና አታውቅም። … አባቶች ጸሎት ሲያሳርጉ፦ “በአማኑኤል ስሙ፣ በፈሰሰው ደሙ፣ በተወጋው ጎኑ፣ በእንተ ማርያም እሙ ምሬአችኋለሁ ይቅር ብያችኋለሁ ይበለን” ይላሉ።”[8]

  እንግዲህ ይህን ማብራራት የሚያሻው አይመስለኝም፤ በግልጥ ልክ እንደ ኢየሱስ ደምና እንደ ተወጋው ጐኑ[እንደ ተቀበለው መከራ]፣ እንደ አማኑኤል ስሙ እኩል ስለ ማርያም በማለትም የሚቀርበው ጸሎት እንደሚሰማ፣ የተባውንና የመነቸከውን ኑፋቄ ወደ ቃሉ አስገብቶ በመተርጎም ሊያቀርብልን ይዳዳዋል። ይህን ያህል መቀላወጥ ግን ለምን አስፈለገ ይኾን? እኛስ እግዚአብሔር በልጁ ጸሎታችንን እንዲሰማን፣ ከእርሱም በቀር በማንም እንዳይሰማን እናውቃለን።

የመጽሐፉን ዋና መልእክት ማድፋፋት

   የምዕራፉ ዋና መልእክት፣ “ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።” የሚለው ነው። ቅዱስ ዮሐንስ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጋቸውን ተአምራት፣ ምልክት በማለት ይጠራቸዋል፤ ተአምራቱ ምልክት ብቻ እንጂ ዋና ነገር አይደሉም፣ በመጨረሻ ውጤታቸውም ተአምራቶቹ የኢየሱስን ክብር እንዲያሳዩ ነው። ተአምራቶቹ ኹሉ የኢየሱስን ክብር ብቻ እንዲያሳዩ የተነገሩ ወይም የተከናወኑ ናቸው። ተአምራቱን ሲያደርግ፣ “ጌትነቱን ነው የገለጠው”።[9] ተአምራቶቹ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን አሰምተው፤ ጮኸው ተናገሩ።

   ከተአምራቱ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በእርሱ አመኑ፤ መሲሕ መኾኑን ማመን ጀመሩ፣ አስቀድሞ ናትናኤል ብቻ የሚያውቀውን መሲሕነቱን፣ አኹን ሌሎችም ደቀ መዛሙርት ማመን ጀመሩ፤ (1፥49)። በተአምራት የተለወጠውን ወይን የቀዱ፣ የጠጡ፣ መለወጡን ያዩ ስለ ማመናቸው አልተጻፈም፤ አላመኑምና። ተአምር ማየትም፣ የተአምሩ አካል ኾኖም የተአምራቱን በረከት መቋደስ፣ ውኃውን ቀድቶ በድንጋዮቹ ጋኖች መሙላትም፣ ሙሽራና ሙሽሪትም፣ ታዳሚዎቹም … ስለ ማመናቸው የተነገረ አንዳችም ሐረግ የለም፤ “ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።” የሚለው ሐረግ ግን የተአምራቱ ውጤትና የዮሐንስ ወንጌል ዓላማ ግብ ወይም መዳረሻ ወይም ፍጻሜ ኾኖ ተቀምጦአል፤ በእርግጥም የተአምራቱም፤ የወንጌሉም መጻፍ ዓላማ፣ “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ” የሚለው ታላቅ ቃል ነው፤ (20፥30)።

ለመጽሐፉ የተሰጠው ርእስ ዮሐ. 2ን አይገልጠውም!

  ለዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ኹለት የተሰጠው ርእስ፣ “ቃና ዘገሊላ” የሚል ነው። በአጭር ቃል ግን “ቃና ዘገሊላ” የሚለው ርዕስ ለምዕራፉ አይኾንም፤ ምክንያቱም፦
1. ምዕራፉን ብንከፋፍለው፣ ከምዕ. 2፥1-11 ኢየሱስ ውሃውን የወይን ጠጅ ስለ ማድረጉ የሚናገር ሲኾን፣ ከምዕ. 2፥12-25 ደግሞ ኢየሱስ ቤተ መቅደስን ስለ ማጥራቱ ወይም ነጋዴዎችን ገርፎ ስለ ማባረሩ የሚናገር ነው። እኒህን ኹለት ታላላቅ ተግባራት በአንድነት ጨፍልቀን፣ ቃና ዘገሊላ በሚል ርዕስ ብቻ እንደ ዋዛ ማለፍ፣ የኢየሱስን ዋነኛ ዓላማ አለማስተዋልና የምዕራፉን ዐሳብ ማድበስበስ ነውና።

  ቃና ዘገሊላ(የገሊላ ቃና) ቦታን ከማመልከት የዘለለ ምንም ዐሳብ በውስጡ የለውም፤ አንደኛው ተአምር ቃና ዘገሊላ ተፈጸመ ብንል እንኳ፣ ኢየሱስ የመቅደስ የማጥራት ሥራውን የሠራው በኢየሩሳሌም፤ ዘሩባቤል ባሠራው መቅደስ ውስጥ ነው። ስለዚህም “ቃና ዘገሊላ” የሚለው ርዕስ ምዕራፉን አይወክልም።

2. በቃና ዘገሊላ በሰርጉ ቤት በተከናወነው ተአምር በፍጻሜው እንዲህ ይላል፣ “ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።” (ቊ. 11)፣ ከቤተ መቅደሱ መጥራትም በኋላ በፍጻሜው እንዲህ ይላል፣ “ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ፤” (ቊ. 23)። እኒህን ኹለት ታላላቅ የክንውኖች ማሠሪያ ብርቱ ቃል እያለ፣ ጨርሶ ምዕራፉን የማይወክል ርእስ መስጠት፣ ኢየሱስን የመጋረድ ተግባር ነው።

“ዲያቆን” አሸናፊ እንዲህ አጥምሞ መተርጐምን ለምን ፈለገ?

እኒህንም በሚገባ መገመት እንችላለን፦
1. አሉታዊና ጸያፍ በኾነ ሥራው መነጋገሪያ መኾን የሚሻ ይመስላል። ይህን ያህል በመዝቀጥ ለኢየሱስና ለመሲሐዊ አገልግሎቱ የተሰጠውን ተአምርና ምልክት፣ ለፍጡር በመስጠትና ኢየሱስ ተግባሩን በእናቱ ረዳትነት እንደ ፈጸመው በማቅረብ፣ ለመሰማት ማሰብ የሐሰተኛ መምህራን ኹነኛ መገለጫና የሸቃጭነት ጠባያቸው ነው።

2. ሐድሶአውያንን ይኹን የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን[ከኹለቱ አንዱን] “ለድንግል ማርያም ክብርን መስጠት አይፈልጉም” በማለት፣ ራሱን የድንግል ማርያም ምዕመን ማድረግ የፈለገም ይመስላል። ይህንም ለማለት፣ “የለዘብተኞችን ንቅናቄ አራማጆችን ትምህርታቸውን መንቀፍ፣” ዓላማው እንደ ኾነም የመጽሐፉ ዓላማ አድርጐ አስቀምጦአል፤ ነገር ግን በሚሳከር ዐሳብ፣ እርሱ በቅድስት ማርያም ጉዳይ ለዘብተኛ አቋም ያላቸውን ለመንቀፍ ጻፍኩ ቢልም፣ መንቀፍ ግን የሰነፍ ሥራ ነው ይለናል፤[10] ተቃርኖ!

3. ድንግል ማርያምን በማወደስና በመቀደስ፣ ዳግም የኦርቶዶክስ ሲኖዶስን ልብ ማግኘትና መመለስን የሚሻም ይመስላል። ለዚህም ቀናውና የጠራው ወንጌል በአገሪቱ ላይ እንዳይሰፋ፤ ለኀጢአተኞች የምሥራቹ ወንጌል እንዳይደርስ በማጠልሸት፣ ይልቅ “ነባሩ ኑፋቄ” እንዲዘልቅና እንዳይፋቅ ከሚሠሩ መካከል አንዱ ኾኖ እንዲቈጠር፣ ከዚህ ውች ያለው ኹሉ ግን፣ በተለይ[ሐድሶውና የወንጌላውያን ኅብረት] ቅቡል እንዳይደሉ በማስመሰል በጽሑፎቹ ተግቶ የሚሠራው፤ በእርግጥም ራሱን “ወንጌል እንደ ተረዳ” ሰው እየቈጠረ፣ የወረደና ኢየሱስን የሚጋርድ ጽሑፍን ከሚጽፍ፣ በኹለት ልብም ከሚያነክስ፣ “ቄደር ተጠምቆ፤ ተናዝዞ በመመለስ[ለቄስ መናዘዝን ያምናልና][11]” ከእነ ምሕረተ አብ አሰፋ ጋር ቢሸቅጥ አይሻለውምን?። ጌታ ኢየሱስ ምሕረት ያደርግልህ፤ አሜን።

አጽንዖት

   መጽሐፉ ከዚህም በላይ፣ ከዮሐንስ ወንጌል ዓላማ ጋር የማይሄዱ ትርጉምና ዐሳቦችን የያዘ ነው፤ ነገር ግን በዙርያችን ያሉ ብዙዎች አኹንም የእርሱን ሥራ በአጋፋሪነት ይከተላሉና፣ “ከባለፈው ጊዜ በከፋ ኹኔታ”፤ የማያገናኘን የሕይወትና የትምህርት ልዩነት እንዳለን ለማሳየት ይህን ጻፍኹ። ቅድስት ማርያም፣ በወንጌላት እንደ ተነገረላት ያመነች ብጽዕት ናት፤ ከዚያ በዘለለ፣ በበዓለ ዓምሳ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ ከሚጠብቁ አማኞች መካከል እንደ አንዲቱ ትጠባበቅ የነበረች ናት፤ ከዚህ በዘለለ እኛ አናከብራትም፤ አናዋርዳትምም፤ (ሉቃ. 1፥45፤ ሐዋ. 1፥14)።

   ደግሜ ደጋግሜ መናገር የምፈልገው፣ የዮሐንስ ወንጌል ዋነኛ ዓላማ፣ “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ” (ዮሐ. 20፥30) የሚለው ደማቅ ዓላማ እንጂ ቅድስት ማርያምን ማክበርና ማግነን አለ መኾኑን መጮኽ ነው፤ በዮሐንስ ወንጌል የተከናወኑት ሰባቱም ተአምራትና ከተአምራቱ ጋር ተያይዘው የተሰጡት ትምህርቶች፣ የተደረጉት ውይይቶች ዋነኛ ዓላማቸው፤ ክርስቶስ ኢየሱስን ማግነን፣ የእግዚአብሔር ልጅነቱን፣ መሲሐዊ ክብሩን መግለጥ ነው። በዚህ ታላቅ ዓላማ ውስጥ የየትኛውም ፍጡር እጅ የለበትም፤ ምክንያቱም ከዘላለም የሥላሴ ዕቅድና ዐሳብ ብቻ ነበርና።

የዋቢ መጻሕፍት ጉዳይ

   “ዲያቆን” አሸናፊ መኮንን፣ አያሌ ታሪኮችን፣ የትርጉም ጽሑፎችን፣ ተረቶችን፣ ትውፊቶችን … አገኘኹ ብሎ ሲጽፍ፣ ከምን ምንጭ እንደ ወሰደ ፈጽሞ አይጠቅስም፤ ይህን ያህል ገጽ መጽሐፍ ሲጽፍ፣ ከሦስት መጻሕፍት በቀር የጠቀሰው አንዳችም ዋቢ የለውም፤ ከእነርሱም እንኳ በቀጥታ አልወሰደም። በምድራችን የታወቁ የስህተት መምህራን ደግሞ፣ ዋቢ ባለመጥቀስና ከሌሎች ጽሑፎች በቀጥታ ይኹን በተዘዋዋሪ በመቅዳት ወይም በመስረቅ (Plagiarizm) የታወቁ ናቸው። በዚህ ረገድ ደግሞ በመንፈሳዊ ጽሑፎች ያለዋቢ መጽሐፍ በመጽሐፍ፣ አሸናፊ መኮንን የሚተካከል በዘመናችን ያለ አይመስልም።

  ዋቢ መጻሕፍትን ጠቅሶ መጻፍ፣ የጽሑፍ ተቀዳሚና የታማኝ ጸሐፍት መገለጫ ነው፤ ሰዎች ከጻፉት መጽሐፍ ምንጭ በአግባቡ ጠቅሶ መውሰድ፣ ለሠሩትም ሥራ ዕውቅና መስጠት፤ የጽሑፍ ሥራቸውንም ማክበር ነው፤ ከዚህ በዘለለ ግን ከሰው መጽሐፍ ዐሳብ ወስዶ፣ የወሰዱበትን ስፍራ አለመጠቅስ፣ ከላይ እንደ ጠቀስኹት ጽሑፋዊ ስርቆት ነው። በአገራችን በእስርና በገንዘብ የሚያስቀጣ ወንጀልም ነው።

ማጠቃለያ

   የዮሐንስ ወንጌል ጠቅላላ ዐሳቡና ዓላማው፣ ሰዎች በጌታ ኢየሱስ እንዲያምኑና በእምነትም ጸንተው እንዲኖሩ ማድረግ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ በመሲሐዊ ክብሩ፣ በሰዎች ልብ እንዲገንንና እንዲመለክ ነው። ወንጌላዊው የተደረጉትን ተአምራትና ትምህርቶችን ኹሉ ጠቅልሎ፣ ለኢየሱስና ለመሲሑ ብቻ ይሰጣል፤ ከዚህ በዘለለ በወንጌሉ የትኛውንም ፍጡር አያገንንም። በሰዎች ልብ የገነኑትን እንኳ፣ ለኢየሱስ ሲያሳንሳቸውና የመሲሑን ጫማ ጠፍር ለመፍታት እንኳ የሚበቃ በጎነት የሌላቸው መኾኑን ከመንፈስ ቅዱስ ይመሰክራል፤ አዎ! መሲሑ ገናና ነው፤ ክብሩ አቻ የለውም፤ ሥጋ ለብሶ በምድር ላይ የተመላለሰውም፣ የአባቱን ፈቃድ ፍጹም በመፈጸም የሰዎች ልጆች ይታመኑበት፤ በስሙ ድነው በመጽናት ሕይወት ይኾንላቸው ዘንድ ነው። አሜን ኢየሱስ ሆይ፤ እንዲህ አምነንህ ፍጹም እንከተልሃለን፤ አሜን።

ተፈጸመ።

1. ገጽ 65
2. ገጽ 87
3. ወንጌል አንድምታ ገጽ 385፤ ወንጌል አንድምታው በሦስት ዓይነት መንገድ ይህን ክፍል ተርጉሞታል፤ ፩ኛው፣ አድርግ ብትዪኝ የማላደርግበት ምክንት የለኝም የሚል ትርጉም ይዞአል፤ ፪ተኛው ደግሞ፣ ውኀውን ወደ ወይን ለመለወጥ የመጣኹበት ዓላማዬ ነውና “ላላደርግልላቸው ከሰርግ ቤት ተጠርቼ መጥቻለሁን? የሚል ትርጉም ተሰጥቶ እናያለን፤ በሶስተኛ ደረጃ ግን ተግሳጻዊው ትርጉም በአንድነት ተቀምጦአል።
4. Mattew Henery; Commentary on the Whole Bible Volume V; Publisher: Grand Rapids, MI: Christian Classics Ethereal Library; p. 1252
5. ዝኒ ከማኹ ገጽ 1252
6. የብሉይ ኪዳን ማብራሪያ፤ ገጽ 198
7. ገጽ 180
8. ገጽ 81፤ 155፤ 159
9. ወንጌል አንድምታ፤ ገጽ 386
10. ገጽ 178
11. ገጽ 31

9 comments:

  1. በኢየሱስ ስም ምን አጊኝቶት ነው ጌታ ሆይ መጨረሻችንን አሳምረው

    ReplyDelete
  2. ኢየሱስ ይገስጸው

    ReplyDelete
  3. አሜን እንዲህ ኢየሱስን እንከተለዋለን

    ReplyDelete
  4. አቤኒ ተባረክ በብዙ

    የአሽናፊን መፃፍት ብዙዎችን አንብባቸዋለሁ.....አካላዊ ቃል የሚለውን አንብቤዋለሁ ....... ቀጥሎ ቃና ዘገሊላ ና ኒቆዲሞስ የሚባሉት መፃፎቹን አላነበብካቸውም ብዙ ጋደኞቸ ብዙ ትክክል ያልሆነ ነገር አለ አሉኝ...እኔም ለማንበብ ሳልነሳሳ ቀረው.....ምን ለማለት ነው ኒቆዲሞስ ብታዬው ጥሩ ነው....

    በቀረው ግን ፀጋ ይብዛልህ(አቃቤ አሚን አቤኒ)

    ReplyDelete
  5. አውቆ የሚያጠፋ ሰው አደገኛ ነው። እውነትም ወደኋላ እየተመለሰ ነው

    ReplyDelete
  6. አቡ ተባረክ በጣም ግሩም ስራ ነው

    ReplyDelete
  7. Geta Tsega yabzalih grum Israa new

    ReplyDelete
  8. አይ አቤኔዘር ተክሉ ማንነትህ ግልጥ ያለ እኮ ፕሮቴስታንት ነህ፡፡ ሪፖርቱን ያወጣው መናፍቅ ነው፡፡ እሱ ደግሞ ምንፍቅናውን እንደ አንተ በመለመላቸው ከሀዲዎች ቤተ ክርስቲያኗ መድረክ ላይ አለመስበካቸውን ነው፡፡ ኢየሱስን እንደምትሰብክ ዓለም ያውቃል፡፡ መናፍቅ ግን ለዘለዓለም አይቀበልም፡፡ እሱም እንደ ወገኖቹ አውሮፓውያን ለዘላለሙ ማሸለቡ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያ ግን ኢየሱስን ለዘለዓለም ትሰብካለች፡፡

    ReplyDelete
  9. እንኳንስ የማይደገም ፀጋ የተሰጣት መልካሚቱን ማርያምን ይቅርና በእግዚአብሔር ዙርያ ያሉ፣ የመንግስቱ ባለሟሎች መላዕክቱ፣ ቅዱሳኖቹ፣ ሳማዕታቱ… ሁሉ የሚደነቅ ሕይወት አላቸዉ። አንቱ ሽንጦን ገትረዉ በሚቆሙላቸዉ ምዕራባዊያን ዘንድ ነገረ ማርያም ቁምነገር ታጥቶበት ሲጣል ደንግልና እንደ ኋላ ቀርነት፣ ብልግና የዘመናዊነት መስፈርት ሆኖ አበላለጉ ሁሉ ረቀቀ። መምህር ሆይ በእዉኑ የቅዱሳኑን ህይወት ደጋግመን ብናጠናና ብናደናንቃቸዉ በፈለጎቻቸዉ አንሳብምን!? ደግሞስ በዚህ መንፈሳዊነት በተዳከመበት ዘመን፣ ከዚህ ረብ ከሌለዉ ንትርክ ይልቅ በገባን መጠን ዜጎችን ወደ መንግስቱ ማፍለስ አይቀድምም?!
    ዲያቆን አሸናፊ ለምን ብለዉ ሲኖዶሱን ለማማለል ይጥራሉ!? ወደ አዉደ ምህረት ተመልሰዉ ዘይት ለመነገድ እንደማይሉኝ እርግጠኛ ነኝ! ኦርቶኮክስ ዘንድ ቤተኛ መሆን በአረማውያን ለመገደል ካልሆነ ለስጋዊ ድሎትስ ወዲያ እርሶ በሚያደንቋቸዉ ዘንድ ይመስለኛል! እሰከሚገባኝ ድረስ ዲያቆኑ በብዙ ሰዉ ዘንድ እራስን እድምቆ ያለ ቁምነገር ከመድረክ ወደ መድረክ ከመዝለል ይልቅ፤ በጓዳቸዉ እራስን በማደብዝ ወንጌልን በብዙኻን ጓዳ ማዝለቅን የመረጡ ይመስላሉ!
    በአገልግሎቶ ብዙ ከተባረኩት ነኝ፤ ብስት ካለማወቅ ነዉና ይቅርታ ይደረግልኝ!

    ReplyDelete