Friday 3 January 2014

ጸሎት - ሰባራ በግህን አትለፈኝ!!!

ሁለንተናህ ቅዱስ ዘወትር የምትናፈቅ ፤ማለዳህ ጽድቅ ሠርክህም ምህረት የሆንከው ጌታዬ! ሰባራው በግህ እኔን የተሸከምከኝ ውዱ እረኛዬ ሆይ አመሰግንሐለሁ፡፡ጠባቂዬ! በሚያልፍና በማይጠቅመው ሸክላ ማንነቴ ተመክቼ ያንተን እረኝነትና መጋቢነት ንቄ ብሔድ እንኳ ከፊቴ ቀድመህ የማርፍበትን ለምለም መስክ የምረካበትንም የዕረፍት ውኃን አዘጋጅተህልኛልና አመሰግንሐለሁ፡፡
   
መልካሙ እረኛዬ ኢየሱስ ሆይ! እኔ ሰባራህ በግህ ነኝ፡፡በቤትህ በፀጋህ እንዳደጉትና እንደጐለመሱት የማልበረታ ታናሽና ኃጢአተኛ ብላቴናህ ነኝ፡፡ሰው እንደማትንቅ ፣ሰባራ በግ እኔን ልጅህን አይተህ እንደማታልፍየጤሜዎስ ልጅ በርጠሜዎስን ፣ቀራጩ ሌዊን ፣ሰባት አጋንንት የወጡላት የመግደሎሟን ሴት ማርያምን ፣መዳን የሆነለት ዘኬዎስን፣ሰው የሌለው የቤተ ሳይዳ መጻጉዕን፣ባለንዳድዋንና ደካማዋን የኬፋን አማት ፣አለማመኑን የረዳህለትን ሽባእኔን አመንዝራና አመጸኛ ባርያህንም ስትሰበስብ አይኔ አይታሀለችና ነፍሴ ትመካብሐለች፡፡

     በእነርሱ ስብራትና ድካም ላይ ጌታ የሆንከው ጌታዬ በእኔም ስብራትና ድካም ላይ ሥልጣን እንዳለህ አምናለሁና በምስጋና እባርክሀለሁ፡፡ተሰብሬ ከመንገድ የቀረሁ በግ ልጅህን ትተኸኝ እንዳታልፈኝ ቀራንዮ ለእኔ ለውድ ልጅህ ስትል ባፈሰስከው ደምህ እማጸንሐለሁ፡፡እረኛዬ ያገኘኝ ሁሉ ሰብሮኛል፤ ደካማነቴን አይቶ እንደመንገድ ዳር ጭቃ ተላላፊ ሁሉ ረግጦኛልና ሁሉን ቻዩ ጌታ አሁን ብርታትህ ትደግፈኝ፡፡
     ጌታዬ ሰባራን በግ ማን ይወደዋል? እረኛ እንኳ ቶሎ ቶሎ ስለማይሄድለትና ሁሌ አዝሎና አቅፎ መሔድ ስለሚታክተው ከአንድ ስፍራ ያኖረዋል፡፡እረኛዬ ኢየሱስ! ሁሌ በመተላለፍ፣ዘወትር በኃጢአት ፣ዕለት ዕለት በነውር መያዜን የሚያውቁ ሁሉ ተጠየፉኝ ፣አይተውኝም ፊታቸውን ከእኔ ዘወር አደረጉ፡፡ጌታዬ! በቤትህ እንዳሉት ስላልበረታሁ በገረገራ ቅጠል ለብሼ ያለሁትን ያዩኝ ሁሉ በርኩሰቴ ተጠቋቆሙብኝ፡፡መድኃኒቴ! ህይወቴና ኑሮዬ ተከናውኖ ባይሰምርልኝ ፣ሁሌ የምትጠግነኝና የምትፈውሰኝእኔን መሸከም እኔን ማዘል የማትሰለቸኝ አንድ አንተ ብቻ ነህና ዘወትር አይኖቼን ወዳንተ አቀናለሁ፡፡
      ጌታዬ! ሰባራ ብሆንም እግሮቼን እየጎተትኩ እከተልሐለሁ፡፡ባትፈውሰኝም ተስፋዬና ጌታዬን ለዘለዓለም አልተውህም፡፡መልካም የበጎች እረኛ እኔ ነኝያልክ ጌታዬ ሆይ! ዳግመኛ ለኔ ባፈሰስከው ደምህ እማጸንሐለሁ፡፡ሰባራ በግህን አትተወኝ፡፡ጌታዬ! መሐላዬና ኪዳኔ አንተን ባንተው ጸጋ ማየት ነውና እባክህን እርዳኝ፡፡ሰው ሁሉ የናቀው በግህን አንተ በሰማያዊ አባትህ ፊት አክብረኝ፡፡በበረት ያሉህን ዘጠና ዘጠኙን በጎች ትተህ እኔን ፍለጋ ከሰማየ ሰማያት የመጣህ ወዳጅና አምላኬ ሆይ የሚሰብረኝ ጠላቴ ብዙ ነውና በአለሙ ጫካ ውስጥ ባዛኝ በግህን አትተወኝ፡፡  
      አቤቱ! አውሬውን ተኩላ አልፈራም፤ የሚሰብረኝ የሰው ተኩላ ነውና አንተ ከእርሱ አድነኝ፡፡ጌታዬ! የሰው ተኩላ ሰባራ ቀን አይቶ የማያልፍ ፣በደከምሁም ጊዜ ራርቶ የማይረዳ ጨካኝ ነውና ጠባቂዬ ከዚህ ክፉ አውሬ አድነኝ፡፡አቤቱ! ይህ ትውልድም በዚህ ክፉ አውሬ መንፈስ ተተብትቧልና ድረስለት፡፡የአምልኮ መልክ ይዞ ውስጡ ግን የስድብ ዝናም የሚያጎርፍ፣ተመሳስሎ መተራረድና መተላለቅ የሆነለት፣እየተሳሳቁ ጉድጓድ መማማስ እንደነውር የማይቆጠርበት ፣አንዱ አንዱን ሲያጠፋውም ሐይ ባይ የጠፋበት የተኩላ ዘመን ሆኗልና  አቤቱ አንተ ለትውልዱ ናለት፡፡
       አቤቱ! ወጣትነታችን በዝሙት ነውር ረክሶብናል፣ጉብዝናችንም በሴሰኝነት አድፏል ፣ሽምግልናችንም በተላላነትና በምሬት አልቋልና ዘመናችንን አድስልን፡፡ሁሉን ቻዩ ጌታ የውስጡ መንፈሳችንን ፈውስልን፡፡ይቻልሐልና መምሰልን ሳይሆን ባንተ ላንተ መሆንን ስጠን፡፡በግ ሆኖ እንደተኩላ ከመኖርም አድነን፡፡
    መድኃኒቴ! ያገኘኝ ተኩላ እንዳይሰብረኝ ለሰባራው በግህ ቅጥር ሁንልኝ፤ የዝሙት አሜኬላ ወግቶ እናዳያደማኝ ለደካማው በግህ ኃይልህን አስታጥቀኝ፤ አለማዊነትና ክፉ ምኞት እንዳያስጎመዠኝ በለምለም መስክህ በዕረፍት ውኃህ አሳድረኝ፤ መድኃኒቴ! ያዕቆብበጭኑ ምክንያት እያነከሰእግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች”(ዘፍ.32÷30)ብሎ ላንተ በደስታ እንደዘመረልህ እኔም እየዳህኩ ፣እየተናፏቀቅሁ እያነከስኩም … (መዳህ፣ መንፏቀቅና እያነከሱም መከተል የሚቻለው ባንተ ነውና)  ተከትዬህ በደስታ እንድዘምርልህ ባርያህን በጸጋ ለመንፈሳዊ አካለ መጠን አድርሰኝ፡፡የእኔ ጌታ ሁሉ እንደፈቃድህ ይሁን፡፡በተወደደው በክርስቶስ ኢየሱስ ስምህ፡፡አሜን፡፡



1 comment:

  1. ወንድሜ ሆይ! ቃለ ሕይወት ያሰማልን እያልኩ - የማንኛውን ጽሑፍህ(በተለይ ደግሞ-"ጸሎት" በሚለው) ምንጭ ብትጠቅስልን በታላቅ ትሕትና እጠይቃለሁኝ::

    ReplyDelete