Friday 17 January 2014

ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፡፡(ማቴ.3÷8)

Read in PDF

የስሙ ትርጓሜ “እግዚአብሔር ፀጋ ነው” ማለት ነው፤የተወለደው “በጌታ ትዕዛዝ ህግጋት ሁሉ ያለነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ከነበሩት” ከቅድስት ኤልሳቤጥና ከካህኑ ዘካርያስ ነው፡፡(ሉቃ.1÷6)፡፡ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ኃጢአትን ያልሰሩ ጻድቃን አልነበሩም ነገር ግን የእግዚአብሔርን ህግና ሥርዓት በማክበር ታማኞችና እጅግም ቅኖች ነበሩ፡፡የእግዚአብሔር ቅዱሳን ህይወታቸውን በንስሐ ያጠሩ ብቻ ሳይሆኑ ፤ንስሐቸውም ፍሬ የሚያፈራና የሚታይ ህይወት የሚነበብበት ነው፡፡ኤልሳቤጥና ዘካርያስ ህይወታቸው በእግዚአብሔር ፊት ያለነቀፋ የሆነውን ያህል በሰውም ፊት ነውር ያልነበረባቸው ነበሩ፡፡
     በሌላ ንግግር ኤልሳቤጥና ዘካርያስ ስም ብቻ ያልነበራቸውና ያልከበዳቸው አማኞች ነበሩ፡፡ለታመኑለት ጌታ የሚታመንና በፍሬ የሚታይ ህይወት ነበራቸው፡፡ዛሬ ክርስትናችንን ከሚያስነቅፉብን ነገሮች ዋነኛውና ትልቁ “ክርስቲያን የሚለው ስም አለን ነገር ግን ስሙ በእኛ የማይሰራ ሙትመሆኑ ነው፡፡(ራዕ.3÷1)፡፡ክርስቲያን ተብሎ የሚጠራው ጥቂት የማይባለው ማህበረሰብ የነጠላ ያህል በነውር ካጌጠ ፣የላንቃ ያህል በዝሙት ከተቆነጀ፣በጉበኝነት ከተሞሸረ፣አለልክ በማግበስበስና በስግብግብነት ከተካነ …  ዘመን ቆጥሮብናል፡፡
     እኒህ ደጋግ ቅዱሳን ግን ለእግዚአብሔር የለዩት ቅዱስ ህይወታቸው ያለፍሬ የቀረ አይደለም፡፡ እነርሱ ቢያረጁም በዘመናት በሸመገለው ጌታ እየተጽናኑ በፊቱ ያለነቀፋ ኖሩ፡፡በሰው ፊት ቅድስና በሚመስል ሽንገላ መኖር ይቻል ይሆናል፤ጨለማ እንኳ በፊቱ በተገለጠ ጌታ ዘንድ ግን ለመዘበት ካልሆነ በቀር ፈጽሞ አይቻልም፡፡የሰው ጽድቅ ያረክሳል፤የእግዚአብሔር ጽድቅ ግን የረከሱትንና ተስፋቸው የሞተባቸውን ያለመልማል፡፡እኒህ ቅዱሳን በማግኘትና በሙሌት እግዚአብሔርን ያመለኩ አይደሉም፤በማጣትና በመካንነት ውስጥ ሆነው እስከሽበት ሽምግልና የታመኑ ናቸው እንጂ፡፡እግዚአብሔርን በማግኘት የሚያመልኩ ብዙ ናቸው፡፡በማጣትም የሚያመልኩ ግን የጨከኑና ፍቅሩን ያዩ ብቻ ናቸው፡፡
     ስለዚህም በዘመን መጨረሻ ፣ቀን ሲመሻሽ ፣ተስፋ ሊጠፋ ሲስለመለም፣እርጅና በደጅ ሳለ ጌታ እግዚአብሔር “መልዕክተኛና መንገድ አስተካካይ”(ሚል.3÷1)፤ “የአዋጅ ነጋሪ ቃል”(ኢሳ.40÷3) የተባለውን ዮሐንስን ልጅ አድርጎ ሰጣቸው፡፡እግዚአብሔር ስለቃሉ እንጂ ስለበጎነታችን ታማኝ የሆነ አይደለም፡፡አባታችን ስለሆነ ከሁሉ አያጎድልብንም፤ በአባትነቱ ልግስና እግዚአብሔር ዮሐንስን ለካህኑ ቤተሰብ ሰጠ፡፡
       ዮሐንስ ሙሉ ዘመኑን ያሳለፈው በምድረ በዳ፤ህይወቱንም በብህትውና ለእግዚአብሔር ነው፡፡በዚያ በምድረ በዳ ሳለ ሁሉንም ነገር ከእግዚአብሔር ፤በእግዚአብሔር ተምሯል፡፡ከምድረ በዳ ሲወጣ ቀጥታ የጀመረው “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ”(ማቴ.3÷2)የሚለውን ስብከቱን ነው፡፡ከሰው መማርና ዕወቀት መጨበጥ አስፈላጊ ቢሆንም ግና “ከእገሌ ሥነ መለኮት ኮሌጅ ወይም ከእገሌ መምህር ካልተመረቀ ወይም ካላስመሰከረ ለሚሉ ለዛሬዎቹ የቤተ ክርስቲያን አመራሮችና የበላይ አካላት ከባድና ብርቱ ተግሳጽ ነው፡፡እግዚአብሔር በየትኛውም ዘመን በሰው ብልሐት አልተገለገለም፡፡ለአዕምሮ ከሚናገሩ ሊቃውንትና መምህራን ይልቅ ለነፍስና ለመንፈስ የሚናገሩ ያልተማሩቱ ይበልጣሉ፡፡ሊቃውንትና መምህራን የተባሉት ከዘመኑ የፖለቲካ አየር ጋር እየነፈሱ እንደአይሁድ ሊቃውንት ህጻኑን ለማስገደል ከሄሮድስ ጋር ይመክራሉ(ማቴ.2÷5) እውነተኞቹና ያልተማሩቱ እረኞች ግን የትንቢቱን ቃል ፍጻሜ በአይኖቻቸው አይተው እግዚአብሔርን ያከብራሉ፡፡(ሉቃ.2÷20)
       እንደአይሁድ ለክፋትና ለአድመኝነት ፣ሰው ለመግደልና ለመስደብ የሚጠቀስና የሚገለጥ “የእግዚእብሔር ቃል ሚስጢር” ዛሬ ከምን ጊዜውም ይልቅ በዝቷል፡፡እግዚአብሔር ግን በእንዲህ ያሉ መምህራንና ሊቃውንት አይከብርም፤አይገለገልም፡፡ዮሐንስ ዝም ቢል ህይወቱ የሚናገር ቅዱስ አገልጋይ ነው፡፡በብዙ ጌጥ የተጌጠና በልስላሴው ያማረ ቀሚስ የለውም ልብሱ የግመል ጠጉር ነው፡፡ከአፉ የሚወጣው ቃል ግን የነፍስን ዕርቃን ይሸፍናል፡፡የእርሱ ኑሮ በምድረ በዳ ቢሆንም ብዙዎችን ወደእግዚአብሔር በረትና ቤት አፍልሷል፡፡እንደእናትና አባቱ በጉድለቱ አላንጎራጎረም፤ በህይወቱ አምላኩን አከበረ እንጂ፡፡የቃሉም ስብከት ከምድረ በዳ የተሰማ ነው፡፡“ንስሐ ግቡ”፡፡
        ሰው ንስሐ የሚታወሰው ኃጢአተኝነቱን በሚገባ ከተረዳ ነው፡፡ዮሐንስ ከኃጢአት ጋር አልተደራደረም ስለዚህም ጨክኖ ተናገረ፡፡ንስሐ የሐዲስ ኪዳን ማዕከላዊ መልዕክት ነው፤የቀደሙት ነቢያት፣ጌታ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የሰበኩት ዋና ርዕስም ንስሐ ነው፡፡የቀረበችው የእግዚአብሔር መንግስት ለሰው ልጆች ልትሠጥ የተበሰረችው በንስሐ ነው፡፡እውነተኛም ንስሐ የመንፈስ ቅዱስን ፍሬ ከማፍራትና ከማሳየት ጋር የተያያዘ ነው፡ዮሐንስ በልከኛ ህይወቱ ሳይፈራ ይህን ተናገረ፡፡እውነተኛ አገልጋይ “ጎመን በጤና” ብሎ ካለው ነገር ጋር ተመሳስሎ ከኃጢአት ጋር ተመቻምቾ የሚኖር አይደለም፡፡ሰዎች ከኃጢአት ህይወት እንዲወጡ ጨክኖ ኃጢአተኝነትን እየገለጠ የሚናገር፣ የሚመክር፣ የሚገስጽ እንጂ፡፡
     ብዙ ጊዜ ዘፋኝነትን የሚደግፉና ዘፋኞችን ለአገልግሎት የሚጋብዙ አንዳንድ “አገልጋይና አብያተ ክርስቲያናትን” አያለሁ፡፡ምናለ የዮሐንስ አንገት የተቆረጠው በዘፋኝ መዘዝ እንደሆነ ቢያስተወሉ? … በዓላትን ታኮ ብዙ ጊዜ ዘፋኞች የሞት ድግስ ለህዝቡ ይደግሳሉ፡፡አንድ ብርቱ ለጌታ አገልግሎት የጨከነና “እናንተ የክፋት አገልጋዮች ይህን ህዝብ አታስቱ ይበቃችኋል” ብሎ ጮኾ የሚናገር ግን ዛሬ እንደዔሊ ዘመን ብርቅ ሆኖብናል፡፡(1ሳሙ.3÷1) 
    አዎ! ዮሐንስ “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” ዛሬም ይለናል፡፡አንዳንዶች በተለያየ አጋጣሚ ኃጢትን አይሰሩምና ንስሐ ማለት ኃጢአትን አለመስራት ማለት አይደለም፡፡ንስሐ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ለማፍራት በደሙ ጉልበት ዕለት ዕለት በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን በመተው የምንመለሰው መመለስ ነው፡፡ “የአብርሐም ዘር ነኝ፣ የቅዱሳን ወገን ነኝ፣ የጥንት እምነት ተከታይ ነኝ፣ ቀደምት ነን … ” ማለቱ አይረባንም ፤እግዚአብሔር ከናቅናቸውና ድንጋይ ናቸው ካልናቸው ወገኖች መካከል ልዩና ታላቅ የራሱን ህዝብ ሊያስነሳ ይቻለዋልና እኛ ለራሳችን ለንስሐ ሚገባ ፍሬ ይታይብን፡፡አልያ ግን ፍርድ በደጅ፤ምሳር ሊቆርጥ በዛፍ ሥር አለና ፈጥነን በንስሐ እንመለስ፡፡
መልካም በዓል ይሁንላችሁ፡፡
ጸጋ ከሁላችን ይሁን፡፡አሜን፡፡ 

2 comments: