Sunday 12 January 2014

ነጻነትን ለኃጢአት?

ከበለዐም መርገም አስማትና ምዋርት
ከባላቅም ምክር ቃየላዊ ክፋት
እስራኤል አምልጧል ከበዛው ተግዳሮት
ቀስቱ ተቀንጥሶ ወጥመድ ተሰብሮለት፡፡
           ተሽሯል እርግማን ኃይል አጥቷል አስማቱ
           የሠራዊት ጌታ ጣልቃ በመግባቱ
           በአህያ አንደበት የታላቁ ነቢይ ታግዶ እብደቱ፡፡



ግን ያ ብርቱ ህዝብ
ከግብጽ የተለየው የእግዚአብሔር ቅዱስ
ከፊተኛው ውጊያ ከተቃጣው ክፋት
ቢያመልጥም በአምላኩ የሰፋ ቸርነት …
ህሊናውን ሸጦ
ነጻነቱን ለኃጢአት ለዝሙት ሰውቶ
በፈቃዱ ሲሄድ ለጭን ዳሌ ሟሙቶ
ቅጥሩ ተነሳበት
ግርማውም ሸሸበት
እርግማን አስማቱ ያልረታው ያልፈታው
አመንዝራነቱ አድርቆ አረገፈው፡፡
          እጅ ስትዘረጋ
          ለ'ርሱም ስትገዛ
          ብትሔድ በሞት ጥላ
          ያድንሐል እርሱ ሆኖልህ ከለላ
ግና …
ለገዛ ምኞትህ
ስትኖር ለፈቃድህ
ቅጥሩ ካንተ ሸሽቷል
የጠላኸው ጠላት አዋርዶ ይወርስሐል
በበዛ መቅሰፍቱም በቀስት ያረግፍሐል፡፡

No comments:

Post a Comment