Sunday, 5 January 2014

ድንግል ፈጣሪዋን ወለደች፡፡(ቅዱስ ቄርሎስ)

በእግዚአብሔር መንግስት ታሪክ እጅግ ልዩና ታላቅ የሆነ ምስጢር ነው፤የአካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ሥጋን ነስቶ የባህርያችን መመኪያ ሆኖ መገለጡ፡፡ነቢያት ለብዙ ሺህ አመታት የናፈቁት ፣ትንቢት ተንብየው ሱባዔ ቆጥረው ከሩቅ ያዩት ፣አባቶችና እናቶች በራዕይና በምሳሌ የተረዱት … እውነተኛው ጌታና አምላክ ፣ህጻንና ልዑል የእኛን ሥጋ ለብሶ እንዲህ  ተገለጠ፡፡
    ከነቢየ እግዚአብሔር ከሚልኪያስ ወዲህ የእግዚአብሔር ራዕይና ትንቢት እነሆ በግልጥ መገለጥ ከተወና ዝም ካለ፤ዘመኑም የዝምታ ዘመን ከተባለ እነሆ አራት መቶ አመታት አልፈዋል፡፡የምሳሌው አገልግሎት በሚገለገልበት በዚያ በጨለማ ዘመን ላይ የእግዚአብሔር ዝምታ ሲታከልበት ምን ያህል እጅጉን ይከፋ ይሆን? …የመከራው ዘመን ዕለቱ ዓመት …ዓመቱ ዘመን ይሆናል፤መከራ አሻጋሪው እግዚአብሔር ደግሞ ሲለየው መከራው ክብር አልባ ብቻ አለመሆኑ ሳይሆን ከሞት ይልቅ የሚከብድ ይሆናል፡፡“ሊነጋጋ ሲል አብዝቶ ይጨልማል ”እንዲሉ የብርሃንና የምህረት ዘመንን ጌታ ሊያመጣ ኋላው አብዝቶ ድቅድቅ፤አብዝቶ ዳፍንት ጨለማ ሆነ፡፡


       ብርሃን አብዝቶ የሚናፍቀው ጥልቁን ጨለማ ላየ ሰው ነው፡፡ጨለማን ያየ በጭላንጭል ብርሃን ተስፋው ይለመልማል፡፡በተፈጥሮ ዑደት ቀድሞ ብርሃን አይገለጥም፤ታላቁ መጽሐፍም አስቀድሞ “ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ”(ዘፍ.1÷2) ይለናል፡፡በዚህ ጥልቅ ጨለማ ላይ ጌታ እግዚአብሔር “ብርሃን ይሁን አለ ብርሃንም ሆነ።” ጌታ እግዚአብሔር ዛሬም የሚሰራው እንዲሁ ነው፤ክርስቶስንና ወንጌሉን የማያውቀው ጨለማ ልባችንና ማንነታችን ላይ ቀድሞ የክርስቶስ ወንጌል እንዲበራበት ይሻል፡፡(2ቆሮ.4÷6)፡፡በህይወት ጉዞም ከጨለማ ወደብርሃን እንጂ ከብርሃን ወደጨለማ መሄድ አያጓጓም፡፡ብዙ ጊዜ ትልቁን የህይወት ምዕራፍ የጨረሱ ሰዎች በትንሹ የህይወት ምዕራፍ ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ከትንሹ ወደትልቁ የሚሄዱ ክብር የሚበዛላቸው ሲሆኑ ከትልቁ ወደትንሹ የሚሄዱት ግን ዘመናቸውን በመቅበዝበዝ ይፈጃሉ፡፡ከኃጢአት ወደ እግዚአብሔር ጽድቅ ፊትን መመለስ ዕረፍት አለው፤ከበጎነት ወደክፋት መሄድ ይሁዳዊነት ብቻ ሳይሆን የዘላለምን ገሃነም መምረጥ ነው፡፡
    ጌታ እግዚአብሔር ለብዙ ሺህ አመታት በትንቢት ፣በህልምና በራዕይ የተናገረ ቢሆንም ለአራት መቶ አመታት ያህል ዝም ካለ በኋላ አሁን በልጁ ተገልጦ ሊናገረን ወደደ፡፡በሩቅ የሰማነው ሊቀርብ ፣ለዓይኖቻችን ድንቅ የሆነው ሊታይ፣ሰማያዊው ምድራዊ ሆኖ በትውልዱ ከእኛ እንደአንዱ ሊቆጠር ከብላቴናይቱ እናት ክንድ ላይ ታቅፎ ታየ፡፡ቅድስት እናታችን እመቤታችን የፈጠራትን እርሱን ፈጣሪዋ ክርስቶስን ወለደችው፡፡የማይቻለውን እርሱን በሁሉ ቻዩ ጌታ በእርሱ ቻለችው፡፡በጥንት ነቢያትን ኋላም ሐዋርያትን ፤መምህራንን፣ ዘማርያንን … የወለዱ እናቶች ተከብረዋል፤ተወደዋል፡፡በዘመን መካከል አምላክን በሥጋ የወለደች እናት ድንግል ማርያም ይህ ክብሯ ልዩና ታላቅ ነው፡፡
    ከእርሷም በፊት ሆነ ከእርሷም በኋላ በዚህ ክብርና ሞገስ በፈጣሪ ፊት ተገልጦ የታየ፤ተወዶ የቀረበም የለም፡፡እግዚአብሔር በክብሩ ድንግል ማርያምን አከበራት፡፡እመቤታችንን ክብሯ ትልቅ ነው የምንለው በአንድ ልዩና ግልጽ ምክንያት ነው፤እርሱም “እርሷ ፈጣሪዋን በመውለዷ ነው”፡፡የሌሎች ቅዱሳን ጸጋ የሚደገምና በሌሎችም የተገለገለ ነው፡፡የድንግል ማርያም ግን በእርሷ ብቻ እንጂ በሌሎች ያልተደገመ ጸጋ ነው፡፡በጸሎቷም እንዲህ አለች፦“ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው።”(ሉቃ.1÷49)፡፡በዘመን የእግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው፤እኛን ለማዳን ግን በእርሷ ያደረገው ድንቅና ግሩም ነው!!!
     ድንግል የሚሸከማትን ተሸከመችው፤ የምትታዘዝለትን አዘዘችው፤ የፈጠራትን ወለደችው፤ የምትሰግድለትን ታቀፈችው፤ የምትፈራውን በፊቱ ተንጓደደች፤ የምትዘምርለትንና በገናን የምትደረድርለትን ኢየሱስ ብላ በስሙ ጠራችው ፤ አባትዋና አስገኚዋ በፍቅር ታዘዛት፤ በሠራዒነቱ የሚመግባትን ጡት አጠባችው ፤የምታመልከውን በአንቀልባ አዘለችው ፤ ትሁት ባርያ እናት ሆና ፈጣሪዋን ወለደችው፡፡
   ድንግል ፈጣሪዋን በመውለዷ ፤ከተወለደውም ህጻን የተነሳ ለእኛ ፍጹም መቅረብ ፣ወደእግዚአብሔር አደባባይ ወደምህረቱ እልፍኝ መግቢያ በር አገኘን፡፡የወለደችው ህጻን መሰላል ሆኖ መላዕክት በእርሱ ስለእርሱ ሲወጡና ሲወርዱ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ…” እያሉ ሲያመሰግኑ ሰማንም፤ አየንም፡፡እውነተኛም መሰላል ሆኖ ሰውን ከእግዚአብሔር፣ ሰውን ከመላዕክት፣ አህዛብን ከህዝብ … ጋር ሲያስታርቅ (የዕርቅን ውጥን ሲያደርግ) አየን፡፡ነገሩ ድንቅ ነው! ድንግል ፈጣሪዋን ወልዳዋለች… በመወለዱም የራቁ ቀርበዋል፤የተራራቁም ለዝማሬና ለእልልታ በእርቁ ሰነድ በክርስቶስ ኢየሱስ ሊስማሙ ቀርበዋል፡፡
      እንኪያስ ይህን ምስጢር እናድንቅ፤አምልኮም ክብርም ሁሉ ለሚጠቀለልለት ህጻንና ልዑሉን ጌታ “መመለክ፣መወደድ ይገባሃል” ብለን እንዘምርለት እንሰግድለትም ዘንድ ይገባናል፡፡ምህረቱ ይቆየን፡፡አሜን፡፡









1 comment:

  1. ke segawa seegama alwesedem segaw ke semay newu pls read john 13

    ReplyDelete