Monday, 30 December 2013

የኢየሱስ ደም - ክፍል አራት


Please read in PDF
                                                                             
የኢየሱስ ደም አገልግሎት

                     “ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻ”(1ዮሐ.1፥9)

                     “በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን የሚታይ”(ዕብ.9፥24)

                    “በቅዱስ ደሙ ኃጢአታችንን የሻረ”(ትምህርተ ኅቡዐት)

                   “መዓዛው የጣፈጠ ንጹህ መስዋዕት”(ቅዱስ ቄርሎስ)

      ፊተኛው የደም አገልግሎት ኃጢአትን ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ፣ ከማንጻት ይልቅ እያዳፈነ የኃጢአት ፍህም በየማለዳው አዲስ እየሆነ ምድርን በእድፈትና በርኩሰት ስላካለለ ኢየሱስ ከዕድፈትና ከርኩሰት፣ ከፊት መጨማደድም ንጹህ የሆነች (ኤፌ.5፥27) ቤተ  ክርስቲያንን ያዘጋጅና ይሞሽር ዘንድ ወደደ፡፡ ስለዚህም በገዛ ደሙ የዋጃትንና ያነጻትን ቤተ ክርስቲያን እርሱ በገዛ ፈቃዱ መሠረተልን፤ (ሐዋ.20፥28)፡፡

     ቤተ ክርስቲያን የደሙን አገልግሎት ፍጹም ታምናለች፡፡ የደመቀችበት፣ ያጌጠችበት ለሙሽራው ኢየሱስ የተሞሸረችበትና ሙሽሪት ሆና የቀረበችበት የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፡፡ የደሙን አገልግሎት የማታምን ቤተ ክርስቲያንና የማያምን አማኝ ፈጽሞ ክርስቶሳዊ ክርስቲያን መሆን አይችልም፡፡ የኢየሱስ የደሙ አገልግሎት ዛሬም ያላቋረጠ፤ የደሙን መስዋዕት አቅራቢው ሊቀ ካህን ክርስቶስ ኢየሱስም የማይለወጥና የዘላለም ክህነት ያለው ነው፤ (ዕብ.7፥24)፡፡
        አስተውሉ!!! የታረደው በግ ዛሬም በዙፋኑ ሕያው ሆኖ አለ፤ በእግዚአብሔር አሁን ውስጥ ሆኖም በዙፋኑ የሚታየው እንደታረደ ሆኖ ነው፡፡ በዳግም ምጽአቱ የሚመጣው እንኳ የታረደበትን ችንካር እያሳየ ነው፤ (ራእ.5፥9 ፤ ማቴ.24፥30 ፤ ራእ.1፥7)፡፡ በጉ ሊታረድ ግድ የሆነው ምንም ኃጢአት የሌለበት ሆኖ ለኃጢአተኛው አዳም ሊሞት በሥላሴ ዘንድ ምክሩ ስለፀና ነው፡፡ የሞተውንና የወደቀውን ሊያነሳ የማይሞተው ሞቶ፤ እንደታረደም ሆኖ ታየ፡፡
        የታረደው በግ ደም ዋና አገልግሎት፦
1.   ደሙ አዲሱን ኪዳንና ሕያውን መንገድ መርቆ የከፈተ ነው፡፡
      ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለደም አልተመረቀም፡፡ ጌታ ደካማዋንና ሙት የነበረችዋን የኩነኔ አገልግሎት መንገዷን መርቆ የከፈተውና ሊቀ ካህኑ ወደቅድስቱ ሊገባ ድፍረት የሆነው በእግዚብሔር ፊት የሚያቀርበውና በእጁ የያዘው ደም ነው፡፡ ያለደም ወደቅድስት ፈጽሞ መግባት አይቻልም፡፡
    በአንድ ሐገር የሚሰሩ ታላላቅ የመንገድ ሥራዎች የምረቃ ሥርዐታቸው የሚከናወነው በሐገሪቱ ዋና ባዕለሥልጣን(መሪ) ነው፡፡ ዋናው ባዕለሥልጣን የምረቃዋን ሪባን ገመድ ቆርጦ በመንገዱ ከተራመደበት በኋላ ሌሎች እርሱን ተከትለው ይጓዛሉ፡፡ ከዚያ ቀንም ጀምሮ መንገዱ ለሁሉም አካላት ክፍት ይሆናል፡፡
    ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በር ሆኖ በደሙ መርቆ የከፈተልን አዲስና ህያው መንገድ እርሱ የምሕረቱ ዓመት አዲስ ኪዳን ነው፡፡ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት … ”አለን፤ (ዕብ.10፥19)፡፡ ምንም እንኳ ኃጢአተኞችና በደለኞች ብንሆን በልጁ በኩል የምንገባው ወደዘላለም ክብሩ፤ የምንወርሰውም የዘላለም ሕይወትን ነው፤ (ቆላ.2፥13 ዮሐ.3፥15)፡፡ ሕይወታችን የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት በዚያን ጊዜ እኛም ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር እንገለጣለን፤ (ቆላ.3÷41ተሰ.4÷17)፡፡
       “ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእኛ አይደለም … ”(ኤፌ.2፥8)፡፡ ያለእርሱ ጸጋና ያለእርሱ መንገድነት ወደአብ መድረስ አይቻልም፤ (ዮሐ.14፥6)፡፡ ቅዱሳን ሁሉ የሄዱበት መንገድ እርሱ መርቆ በከፈተው ቅዱስና ሕያው መንገድ ነው፡፡ ወደአብ የሚያደርሰው ይህ መንገድ የማያሳስት መንገድ ነው፡፡
    በደሙ ተመርቆ ከተከፈተውም መንገድ በቀር ሌላ ወደሕይወትና ወደእረፍት የሚያደርስ መንገድ ፈጽሞ የለም፡፡ ደሙ የከፈተልን መንገድ የሕይወትና የልምላሜ መንገድ ነው፡፡ ክርስትና የሚለው አዲስ መንገድ ላይ መጓዝ የጀመርነው ክርስቶስ መርቆ ከከፈተው በኋላ ነው፡፡ አዲሱም ኪዳን ላያረጅ ፍጹም የታተመበት ኅትመት ህያውና ለዘላለም ትኩስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፡፡
2.   ደሙ ቤዛችን ነው፡፡

     “በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን
      እርሱም የበደላችን ስርየት።”(ኤፌ.1፥7)

በኋለኛው ዘመን የምክርህን አበጋዝ መድኀኒት ቤዛ የሚሆን ልጅህን ሰደድህልን፡፡
(የሐዋርያት ቅዳሴ)
   
"ስለፍጥረትህ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በእግዚአብሔር ቸርነት በሥጋ ሞተ"
(ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ምዕ.70 .1 ቁጥር 10)

      “ከአዳም ጀምሮ እስከዛሬ ከተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ማንም ማን ሊያድነን አልቻለም፤ ከእግዚአብሔር ቃል በቀር በሰው ቢሆን አለኝታችን ከንቱ እንዳይሆን የባህርይ አምላክ እርሱ ሰው ኾነ እንጂ፡፡ ከሰው ወገን የሚሾም ሊቀ ካህናት ሁሉ በመጽሐፍ እንደተነገረ ስለሰው ይሾማል፤ ስለዚህም ጌታ ከወዲያ ዓለም ወደዚህ ዓለም መጥቶ ከሰው ወገን ተወለደ እግዚአብሔር ቃል ሰው ሆነ፤ አምላክ በመሆኑ ያድነን ዘንድ ሰው በመሆኑም ለእኛ ቤዛ ሆኖ ይሞትልን ዘንድ፤ (ሃይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ ምዕ.58 .49-50)፡፡
        “ቤዛየሚለውን ቃልአዳኝ፣ መድኃኒት፡፡ ዋቢ፣ ሃላፊ፣ መድህን፡፡ በካሳ መልክ ወይም እንደምትክ፣ እንደመለወጫ፣ እንደመያዣ የሚቀርብ…” ብሎ ይፈታዋል፤ (ኣማርኛ መዝገበ ቃላት፡፡ 2001 .ም፤ አዲስ አበባ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ ቤት፡፡ ገጽ.243)፡፡ በሌላ ትርጉም ደግሞየተያዘን ወይም የተወሰደን ነገር ለማስመለስ የሚከፈል ዋጋ፣ ካሳ፣ ለውጥ … ” ነው ይለናል፤ (የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር(2002)፤ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9 እትም፣ አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡)
        በሞቱ ለሚያምንበት ሁሉ ቤዛ ሆኖ በእግረ አጋንንት፤ በሞት ይገዛ የነበረውን አዳምንና ዘሩን በሞቱ ካሳ ክሶ፤ ደሙን አፍስሶ በመከራና በሐዘኑ ሁሉ ምትክ ሆኖ ወደቀደመና ህያው ክብሩ የመለሰው ሥጋ የለበሰው ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታ ነፍሱን በቤዛነቱ ላመኑበት ለብዙዎች ራሱን የሰጠ ነው፤ (ማር.10፥45 1ጢሞ.2፥5)፡፡
    ኢትዮጲያውያን ገበሬዎች በልዩ የሥነ መለኰት የእምነት እውቀታቸውቤዛነት አምላክነት   ያሻዋልይላሉ፡፡ ክርስቶስን ቤዛችን ነው የምንለው የእኛ ምትክ ሆኖ ከታላቅ የፍቅሩ ባዕለጠግነቱ የተነሳ እኛን ተገብቶ፤ ዕዳችንን ሁሉ ከፍሎ በመቤዥ በደሙ ነጻ ስላወጣን ነው፡፡ ቤዛነት የክርስቶስ ብቻ ነው፤ ከፍጡር ወገን ቤዛ መሆን የሚቻለው ማንም የለም፡፡ ዋጋ የሚከፍል አካል እርሱ ቀድሞ ከዕዳ ነጻ መሆን መቻል አለበት፤ ከክርስቶስም በቀር ከአዳም በደልና ዕድፈት ነጻ ሆኖ ዕዳችንን ከፍሎ መድኃኒትና ቤዛ የሆነን የለም፡፡ እርሱ በንጹህ ደሙ ለበደለኛው የሰው ዘር ሁሉ ዋጋ የሆነና በዋጋውም ገዝቶን የዋጀን ነው፡፡ቤዛነት አምላክነት ያሻዋልየሚባለው ከአምላክ በቀር ፍጹምና ንጹህ ቤዛ ፈጽሞ ስለሌለ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው የማይበድል አይደለምና፤ በተጨማሪምጻድቅ አንድስ እንኳ የለም(2ዜና.6፥36   ሮሜ.3፥11)በማለት ቃሉ ስለደመደመ ንጹህና ፍጹም ቤዛ መሆን የሚቻለው ከብርሐን የተገኘው ብርሐን፣ ከእውነተኛው አምላክ የተገኘው እውነተኛው አምላክ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ፍጹም ሥጋን የነሳውና ዘመዳችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እርሱ አምላክ የሆነ ሰው፤ ሰው የሆነ አምላክ ነውና፡፡   
    ክርስቶስ የመጣበት ዋና ዓላማውነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥእንደሆነ ተገልጧል፤ (ማቴ.20፥28 ማር.10፥45) አዎ! ከአምላክ በቀር ሰው ስለራሱ ነፍስ  ቤዛ መሆን(መስጠት) አይችልም፤ (ማቴ.16፥26)፡፡ ቤዛነት ምትክ ሆኖ ከእስራት ነጻ ለማውጣት የሚከፈል ዋጋ ከሆነ፤ ኢየሱስ ብዙዎች ስለሆንነው ስለሁላችን ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ከኃጢአትና ከዘላለም ሞት ነጻ ሊያወጣን ሕይወቱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ አምላክ ለፍጡር እንጂ ፍጡር ለፍጡር ቤዛ መሆን ከቶ አይቻለውም፡፡ ኃጢአት ላረከሰው የሰው ልጅ ኃጢአትና ዕድፍ ፈጽሞ የሌለበት የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ያስፈለገው ለዚህ ነው፡፡
         ስለዚህ የኃጢአት ክስ ያለበት የትኛውም አዳማዊ ፍጡር መዳን የሚችለው በአንዱ ቤዛ በተሰቀለው መድኃኒት ማመን ሲቻለው ብቻ ነው፡፡ እስከዛሬ ለበደለ ባርያ የሞተ ጌታ ወይም አንድ የስስት ልጁን የሰጠ ጌታ አልሰማንም፡፡ ጌታ አብ ግን ልጁን እስኪሰጠን በእንዲሁ ፍቅር ወደደን፤ (ዮሐ.3፥16) ወልድም ገና ደካሞች ሳለን ቤዛ ሆኖ በሞቱ ሊታረቀንና ሊያስታርቀን ወደእኛ መጣ፤ (ሮሜ.5፥6)እኛ ወደእርሱ የሚያቀርብ ምንም ነገር ስለሌለንና የሕይወት በራችንን በራሳችን ላይ ስለዘጋን እርሱ ወደእኛ የተዘጋውን በር ከፍቶ መጥቶ ተቤዠን፡፡ ፍቅሩ ከኅሊና መረዳት ከማስተዋል ይረቃል!!! ተመርቆ የተከፈተውን ሕያውና አዲስ መንገድ የሚያስተዋውቀውና የሞቱን ነገር በልባችን የሚስለውም መንፈስ ቅዱስ ድንቅና ፍቅር ነው፡፡ አዎ! ኢየሱስ መስዋዕት ሆኖ ባፈሰሰልን ደሙ ቤዛችን ሆነልን፡፡ ከእርሱ በቀርም ማንም፤ ምንም ቤዛ የለንም፡፡
            በቤዛችን እንዲህ ተወደናልና ደስ ይበለን፡፡ አሜን፡፡
                             ይቀጥላል

1 comment: