Tuesday 21 January 2014

የኢየሱስ ደም - ክፍል ስድስት

    Read in PDF:
    6- ደሙ ከኃጢአታችን ሁሉ ያነጻናል፡፡

“የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።” (1ዮሐ.1÷7)

“… እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።” (1ዮሐ.2÷2)

“… እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ።” (ራዕ.7÷14)

“በአንድ ልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአታችን መዳንን የሰጠን ፤የሁሉ ህይወት ወደእርሱ የሚሸሹትን የሚረዳ ወደእርሱ ለሚጮኹ ሰዎች ተስፋቸው፡፡” (የቅዱስ ባስልዮስ ቅዳሴ)

“ጥበብ ግን መድኃኒታችን ነው በሥጋው መሥዋዕትነት ያዳነን በደሙም ፈሳሽነት የተወዳጀን ለመንግስቱም የመረጠን...”(የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ)
       ጌታ በመዋዕለ ሥጋዌው ከአይሁድ የገጠመው ዋናውና ትልቁ ተቃውሞ ኃጢአትን ይቅር ስለማለቱ ነው፡፡(ማር.2÷6)በእርግጥም ኃጢአትን ይቅር ማለት የሚቻለው አምላካዊነት ባህርይ ያለው አካል ብቻ ነው፡፡አይሁድ በዚህ ምክንያት ኢየሱስን እስከሞት ጠሉት፡፡ክርስቶስ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው በግልጥ አሳይቷል፡፡ይህ ግን ለአይሁድ እግዚአብሔርን እንደመናቅ ያለ ታላቅ ስድብ ነበር፡፡ለዚህም ነው ሉቃስ በወንጌሉ “ … ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአት ሊያስተሰርይ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ብሎ … ” በማለት በግልጥ የፃፈልን፡፡(ሉቃ.5÷24)

       ይህም ክርስቶስ እርሱ ኢየሱስ ያህዌ የሆነው ፤ ኃጢአትን ይቅር ማለት የሚቻለው እንደሆነ አይሁድ እንዲያውቁ ለመፈወስ ያለውን አምላካዊ ኃይል ፤ኃጢአትንም ይቅር ለማለት እንደሚቻለውና እንዲያውቁትም ነው ብሎ ሉቃስ የጻፈልን፡፡በነገረ ድህነት አስተምህሮ ቤዛነት ከኃጢአት ስርየት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ከእርሱ በቀር ኃጢአትን ይቅር የሚል እንደሌለ ሁሉ ቤዛም ያለክርስቶስ ኢየሱስ የለም፡፡የአብ ናፍቆት ይህን እንድናውቅም ነው፡፡
        ቅዱሱን የመንግስት ወንጌል ከሥጋ ሐሳብ በመራቅ በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት የናኙት ቅዱሳን ሐዋርያት መከራን የተቀበሉበት ዋናው ርዕስ "ክርስቶስ በሆነ  በኢየሱስ እመኑና ተጠመቁ ፤ኃጢአታችሁም ይሰረይላችኋል" ማለታቸው ነው፡፡በእርግጥም የኃጢአት ሥርየት በክርስቶስ ኢየሱስ በደሙ ቤዛነት ላመኑትና ለተቀበሉት ብቻ ነው፡፡(ሉቃ.24÷47፤ሐዋ.5÷42፤10÷43)፡፡የእውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን የመከራ ምንጭና የስደቷ መነሻ፤ የየትኛውም አማኝ የነቀፌታውና የመገፋቱ ዋና ርዕስ የደሙን ቤዛነት ጮኾ በመናገሩ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ያ ሲሆን ብቻም ነው ሰማያዊ ክብርና ደስታ የሚኖረው፡፡(ማቴ.5÷11)

       በኃጢአት ምክንያት በሰው ልጆች ላይ የነበረው የእግዚአብሔር ቁጣ በክርስቶስ መስዋዕትነት በርዶዐል፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለሰው ልጆች ኃጢአት ሲል ታርዶአልና፡፡ከጥንት ኃጢአትን ማስተስረይ የተቻለው አልነበረም፡፡ስለዚህም የዓለሙን ኃጢአት ያስተሰርይና ያስወግድ ዘንድ  ንፁሑ፤ነውር የሌለበት የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ መጣ፡፡
      ከጌታ መምጣት በፊት የነበሩት የብሉይ ካህናትና ሊቃነ ካህናት ምሳሌውን አገለገሉ፡፡እርሱ ግን ዋና ሆኖ ብቻውን ሁለተኛውንና አዲሱን ሊመሰርት አሮጌውንና የፊተኛውን ሻረ፡፡ (ዕብ.9÷10)እርሱ ካቀረበው መስዋዕት የተነሳ ዕርቅና መንጻትን አጊኝተን ከአባቱና ከባህርይ ህይወቱ ጋር ለመታረቅ በቃን፡፡1ዮሐ.1÷7 ላይ “ከኃጢአት ሁሉ” የሚለው ቃል የእግዚአብሔርን ምህረትና የክርስቶስን ደም የሚበልጥ ምንም ኃጢአት እንደሌለ ያሳየናል፡፡አምነን ከመጣን ደሙ ከየትኛውም ኃጢአት ያነጻናልና፡፡
     ውኃ የሚያጠራና የሚያነጻ ሆኖ ሳለ አለመመረጡ ፤ደም ግን የሚያቆሽሽ (ያውም የሥጋን የነፍስንና የመንፈስን ዕድፈት)ለማጥራት መመረጡ በእውነት የእግዚአብሔር ሐሳብ ድንቅና ልዩ ነው!!! በእርግጥ ደሙን ያፈሰሰልን ሊቀ ካህናት የሚራራልንና አምነን በመጣን ጊዜ በኃጢአታችን የማይፈርድብን ነው፡፡ስለኃጠአታችን ማስተስረያ ደሙን አፍስሶልናልና ወደጸጋው ዙፋን በእምነት ስንቀርብ በሚያስፈልገን በማናቸውም ጊዜ ከኃጢአት ይቅርታ ጋር የሚረዳንን ጸጋ በምህረቱ ይሰጠናል፡፡ (ዕብ.4÷16-17)
      “ከእንግዲህ ስለኃጢአት የሚቀርብ መስዋዕት አይኖርም” (ዕብ.10÷18) ዘላለማዊውንና  አንዱን መስዋዕት ክርስቶስ በቀራንዮ ካቀረበባት ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ሌላ ፤ፈጽሞ ሌላ መስዋዕትና ኪዳን የለም፡፡ደሙ እንጂ የየትኛውም ፍጡር ሥራና መልካምነትም ኃጢአትን ማንጻትና ማሥተስረይ አይችልም፡፡እግዚአብሔር ስለኃጢአት ያፈሰሰውና ያቀረበው፤ደስም ተሰኝቶ የተቀበለው መስዋዕት የክርስቶስን ደም ብቻ ነው፡፡ድንቅና ውብ ነው!! ቅድስናና የኃጢአት ስርየት በደሙ ብቻ ነው!!! (ዕብ.10÷10) ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ፡፡
              “ሰው በመሆኑ ሊቀ ካህናት ሆነ፤በገዛ ሥጋው መስዋዕት እርሱ ነው፡፡
              በአምላክነቱ መስዋዕትን ለእርሱ ያቀርባል እንደጌትነቱ ሥልጣንም
              ኃጢአትን የሚያስተሰረይ እርሱ ነው፡፡እንደዚህ ከሆነ ገዥ ፈጣሪ
              ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ነው፡፡”(ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ)
   የትኛውም ልንናገረው ያልደፈርነው ፣የሚያሸማቅቀን፣ሰዎች ሁሉ አይተው የሚጠቋቆሙበት፣ በድፍረት በእውቀት በግድፈት በስህተት፣ከቁጥር የበዛም ይሁን አንዲቱን ፣ከባድ ነው ያልነውም ሆነ “የቀለለው” ሁሉንም ኃጢአትና ዓመጻ የክርስቶስ ደም ሊያነጻ ብቁና ብቻውን ይቅር ለማለት የሚቻለው ነው፡፡የሚያነጻም ብቻ አይደለም የወንድሞች ከሳሽ ቢከሰን እንኳ የሚሟገትልንና እግዚአብሔርን እንድናመልከው ከሞተ ሥራ ህሊናችንን የሚያነጻና በቅድስናም የሚያተጋ ውድ ደሙ ነው፡፡(ዕብ.9÷12)

ይቀጥላል …


No comments:

Post a Comment