Thursday, 30 January 2014

ቃሉ “የማይሰራ አይብላ” አይልም!!! (ክፍል - 1)


Please read in PDF :- kalu Yemaysera aybila aylim(part 1)

       እግዚአብሔር ሠራተኛ ነው፤ ይሠራል፡፡እግዚአብሔር አገልጋይ ነው፤ ያገለግላል፡፡በፍጥረት መጀመርያ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ የተገለጠው ሠራተኛና ሠሪ ሆኖ ነው፡፡ፍጥረትን በዝምታ፣በቃሉና በድርጊት ፈጥሯል፡፡ሠራተኛ ነውና ሲሰራ አይተነዋል፡፡የሠራውንም ለዓይኖቻችን ድንቅ ሆኖ አይተነዋል፡፡በአስገኚነቱና በፈጣሪነቱ የሚታወቀው ቀዳማዊ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ “ሁሉ በእርሱ የሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ ያልሆነ”(ዮሐ.1÷3) ፣ብርቱና አስገኚ ጌታ ነው፡፡ሁሉ በእርሱ የሆነው ጌታ እግዚአብሔር ወልድ አዛዥ የሌለበት ሠራተኛ ነው፡፡
       እግዚአብሔር እርሱን እንድንመስልበት ከሰጠን ጠባዩ አንዱ ሥራ ነው፤እርሱ ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ በሠራዒነቱ እንደሚንከባከብ ሁሉ የመጀመርያው ሰው አዳምንም ምንም ባልጎደለባት የተድላይቱ ምድር “ … ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው።”(ዘፍ.2÷15)ይለናል፡፡ የመጀመርያው ሰው ሁሉንም በጸጋ ያገኘውና የተሠጠው ቢሆንም ሥራ ፈት እንዳይሆን የማስተዳደርና የመንከባከብ የሥልጣን ሥራ በዚያ ሥራ ወዝና ድካም በማይጠይቅበት በገነቱ የጸጋ ዘመን ተሰጠው፡፡



    ሥራ ከእርግማን በኋላ አድካሚና የማያረካ ሆነ እንጂ ከእርግማን በፊትም የነበረ ነው፡፡መላዕክት እንኳ ስራ አላቸው፡፡ሥራቸውም ምስጋና ፤ምስጋናውም ዕረፍታቸው ነው፡፡(ራዕ.4÷8)በምስጋናው ያርፋሉ እንጂ ከምስጋናው አያርፉም፡፡በአጽዋማት ወቅት ብዙ ጉባኤያትና የጸሎት መርሐ ግብሮች በየአብያተ ክርስቲያናቱ ይደረጋሉ፡፡ከአጽዋማት በኋላ ግን ብዙ አውደ ምህረቶች ይቀዘቅዛሉ፤ዕረፍት ወደሚመስሉ የኃጢአት “መስኮች” ብዙ አማኞች ይሰማራሉ፡፡በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት የምናገለግለው መንፈሳዊ አገልግሎታችን አገልግሎትም ዕረፍትም ካልሆነን ንስሐ በመግባት ዳግም ልንመረምረው ይገባናል፡፡
       ሁሉን ቻዩ አዳኙ ኢየሱስ ሥጋ ለብሶ በሰው ልጆች መካከል በተመላለሰበት ወራቱ ለወላጅ እናቱና ለዘመዶቹ “ይታዘዝላቸው እንደነበር” ተነግሯል፡፡(ሉቃ.2÷51)ፍጥረትን በፈጣሬ ቃልነቱ ፈጥሮ ያስገኘው ጌታ በኋለኛው ዘመን ለዘመዶቹ መጥቶ ታዘዘ፡፡ሥራ ፈት ክፉዎች በበዙባት በናዝሬት ከተማ ከእናቱ ጋር ሲኖር እናቱን በሥራ እየረዳት በነገር ሁሉ ታዘዛት፡፡ለአገልግሎት በግልጥ በተመላለሰበት ወራቱም ማንንም ሳይጠየፍ ህሙማንንና ደካሞችን እየፈወሰና እየረዳ ታየ፡፡
      ቅዱስ ጳውሎስ ከመንፈሳዊ የወንጌል አገልግሎቱ ባሻገር ሥራ ወዳድ ትልቅ ሐዋርያ ነበር፡፡ የተጠራለትን የወንጌል አደራ ፈጽሞ ሳይረሳ የሰው እጅ ላለማየትና ላለመጠበቅ በነበረው የድንኳን መስፋት ሙያ ሥራ ተሰማርቶ በሚያገኘው ገቢ ራሱን ይችል ነበር፡፡በሰው ቤት ተቀምጦ እንኳ ሥራውን በማክበር ይሰራ ነበር፡፡(ሐዋ.18÷3) የሚያበራይ በሬ አፉ ሊታሰር አይገባውም ፤እውነት ነው የሚያገለግል አገልጋይ ዋጋ ሊከፈለው ይገባል ነገር ግን በነጻ የተቀበለውን የወንጌል እውነት በነጻ ይሰጥ ዘንድ አቅምና ጊዜ ካለው ለወንጌል ሥርጭት ሊረዳ የሚችለውን ማናቸውንም ሥራ ሳይንቅ ሊሰራ ይገባዋል እንጂ አለአገባብ በሌሎች ላይ ጥገኛ በመሆን የሌላን እጅ መመልከት አይገባውም፡፡
       የመጀመርያይቱ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ትልቅ ወግ ይህ ነው፤(2ተሰ.3÷6) ሁሉ የገዛ እንጀራውን ይበላ ዘንድ ሥራ መስራት ይገባዋል፡፡ሥራ መስራትን አለመውደድ ኃጢአት ነው እንጂ ሥራ አለመስራት ኃጢአት አይደለም፡፡ሥራ መስራት እጅግ እየፈለጉ ነገር ግን ሥራ መስራት ያልተቻላቸው ብዙዎች አሉ፡፡ቃሉ “የማይሰራ አይብላ” አላለም፤ “ሊሰራ የማይወድ አይብላ” እንጂ፡፡ አለመስራት ውስጥ ጊዜና ፈቃዱ እያለ ጉልበቱ ላይኖር ወይም ጉልበቱና ፈቃዱ እያለ ጊዜው ላይኖር ይችላል፡፡አለመስራትን መውደድ ውስጥ ግን ጊዜውና ጉልበቱ እያለ እንኳ ፈቃዱ ፈጽሞ የለም፡፡ለዚህ ነው ቃሉ ካለመስራት ይልቅ መስራት አለመውደድን ለይቶ ያወጣው፡፡በበሽታና በተለያዩ ምክንያቶች የማይሰሩ ሰዎች ቢኖሩ እንኳ አደገኞቹና ለቤተ ክርስቲያን ፈታኝ የሆኑቱ ሊሰሩ የማይወዱት ናቸው፡፡
    ሊሰራ የማይወድ በእርግጥም አይብላ፡፡ብዙ ጊዜ እነዚህ ሊሰሩ የማይወዱ ሰዎች ዘዋሪዎች ናቸው፡፡ስለዚህም በሰው ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ነገርን እንጂ የገዛ እንጀራቸውን አይመገቡም፡፡ (2ተሰ.3÷11)፡፡የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ጥቂት ያይደሉ አገልጋይቿ አለመስራታቸው ብቻ ሳይሆን ሥራ የማይወዱና እጅ በማየት ብቻ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በከተማ መካከል የያዙትን ሁዳድ መሬት ከማልማትና “ለወንጌሉ ክብር የሚዘረጋውን ድባብና ጃንጥላ ከመዘቅዘቅ ነጻ ለማውጣት” ከመስራት ይልቅ እርስ በርስ እየተነካከሱ በሐሜት፣በስድብና በፍርድ ቤት ክስ መዘላለፍን እንደሙያ ተክነውታል፡፡
     አዎ! ይህን ሁሉ ሀብትና የህዝብ ብዛት ይዘን የተራብነው፣ጥላ አዘቅዝቀን የምንለምነው ፣ወንጌል አስር ደቂቃ ሰብከን አንድ ሰዓት የልመና ዲስኩር የምንቀሽረው ፣ሰርቶ ከማሳየት ለምኖ መኖርን የተዛመድነው፣የመበለቶችን ቤት በሰበብ በአስባቡ እየበዘበዝን የጮምነው፣በየ“ደጀ ሰላሙ” የጠብ፣ የአመጽና የአድመኝነት ዕቅድ የምንነድፈው … ሥራን ላለመስራት ከመውደዳችን የተነሳ ነው፡፡የአንዳንድ መነኮሳት፣ቀሳውስት፣ዘማርያንና ሰባክያንን … ተክለ ሰውነትና ወዘና ያየ ሰው ታስረው ለእርድ የሚቀለቡ እንጂ አንድም ቀን በሥራ ደጅ ያለፉ አይመስሉም፡፡አዎ! ትውልድ በስንፍና መቃብር ቆፍረን የምንቀብረው እኛው በገዛ እጃችን ነው፡፡ሰርቶ የሚያልፍለትን ሳይሆን “ሰርቆ የሚያልፍለትን” ትውልድ ያፈራነው እኛው የሥራ መንፈስ ጠላት ወላጆቹ ነን፡፡
   ሊሰሩ የማይወዱትን በመጥላትና በመናቅ ሳይሆን በመምከር መመለስ ይሁንልን፡፡ልትሰሩ የምትወዱና የምትሰሩ ጌታ የህሊናችሁንና የእጃችሁን ሥራ ይባርክላችሁ፡፡አሜን፡፡

                        

                                                 ይቀጥላል …
 

No comments:

Post a Comment