Tuesday, 28 January 2014

የኢየሱስ ደም - የመጨረሻ ክፍል


7- ደሙ መካከለኛችን ነው፡፡


ከጥንት “… በሀሳባችን ጠላቶች” … “ … ከፍጥረታችንም የቁጣ ልጆች የነበርነውን” … “አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቀን፡፡”(ቆላ.1÷22፤ኤፌ.2÷3) ከመጀመርያው የሀሳብ ጠላትና የቁጣ ልጆች የነበርነውን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአባቱ ጋር ሊያቀራርበን እንደያዕቆብ መሰላል መካከለኛ ሆኖ ተገለጠ፡፡ቅዱስ ሄኔሬዎስ እንዲህ አለ፦
          “አባታችን ያዕቆብ ወደሜሶፖታምያ በሚጓዝ ጊዜ ፣በህልሙ እርሱን /ወልድን/ አየው፡፡
           መሰላል ቆሞ(ዘፍ.28÷10-15)፤እርሱም ከምድር እስከሰማይ የተዘረጋ ዛፍ ነው፡፡በእርሱም
          ምዕመናን ሁሉ ወደመንግስተ ሰማያት ይደርሳሉ፡፡የእርሱ መከራ መስቀል ለእኛ ወደላይ 
          መውጫ መንገዳችን ሆኗልና፡፡”(ዳንኤል ክብረት(ዲያቆን)፡፡አበው ምን ይላሉ?፡፡
           (1999)አሳታሚና አከፋፋይ ማህበረ ቅዱሳን፣ቦታ አልተጠቀሰም፡፡)
      በእርግጥም ወንጌል የመሰከረለት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የተዘረጋው መሰላል ክርስቶስ ነው፡፡(ዮሐ.1÷52)ክርስቶስ መካከለኛ የሆነው ሰው ሆኖ ፤ደሙን አፍስሶ በሠራልን የቤዛነቱ ሥራ ነው፡፡ክርስቶስ በፍጹም ሰውነቱ እኛን ፤በፍጹም አምላክነቱ ደግሞ እግዚአብሔርን ወክሎ ሁለታችንን ያቀራረበ መካከለኛ አማኑኤል ነው፡፡እርሱወደአባቱ ለመድረስ ጐዳና ፤ወደወለደው ለመግባት የሚሆን በርነው፡፡ጎዳናው ልክ እንደመሰላሉ ከምድር እስከሰማይ የሚደርስና የቀናም ነው፡፡በዚህ መካከለኛነቱምየአብ ሊቀ ካህናት የሚሆን እርሱ የሰውን ባህርይ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ፡፡”(መጽሐፈ ቅዳሴ ጕልህ፡፡(1994)፡፡አዲስ አበባ፣ትንሳኤ ማተሚያ ድርጅት፡፡ገጽ 146፤የቅዳሴ ሥርዐት ገጽ.82)



            እግዚአብሔር የቀደመውን ኪዳን በሙሴ መካከለኛነትና በእንሰሳት ደም አማካይነት ሰጠ፡፡ ዳሩ  ከሰው ድካምና ነቀፌታ የተነሳ ጉድለት ስለተገኘበት በክርስቶስ መካከለኛነትና በራሱ ደም የሚሻለውን ኪዳን ሰጠ፡፡በቀደመው ኪዳን መካከለኞቹ የሌዊ ልጆች በእንሰሳት ደም አማካይነት ዕለት ዕለት ጊዜያዊ የኃጢአት ማስተስረያ ሥርዐትን ያደርጉ ነበር፡፡በሐዲሱ ኪዳን ግን እውነተኛው መካከለኛ ኢየሱስ አንድ ጊዜ ለዘላለም መስዋዕትን አቅርቦ ፍጥረትን ሁሉ በወርቀ ደሙ ህያው የኃጢአት ማስተስረያን አቆመ፡፡እንግዲህ ሌላ መስዋዕት ማቅረብ ሳያስፈልገው ዛሬም በሰውና በእግዚአብሔር መካከልያመኑትንና ንጹሐን የሆኑ ወገኖቹን ሊያድናቸው እርሱ የሐዲስ ኪዳን አስታራቂና መካከለኛ ሆነ፡፡
    ክርስቶስ እንደአሮጌው ሊቀ ካህንየገዛ ደሙን ይዞወደቅድስት የሚገባ አይደለም ፤ይልቁን ደሙን በቀራንዮ አንድ ጊዜ ብቻ አፍስሶ ወደሰማያዊቷ መቅደስበገዛ ደሙ ገባእንጂ፡፡አዎ! መካከለኛችን የሚሆን እርሱ ደም ይዞ አልገባም፤አንዴ ያፈሰሰው ደም ለዘላለም ይበቃልና፡፡(ዕብ፣9÷12)
     
                                  ማጠቃለያ
                     እንኪያስ ምን እናድርግ?
    ኃጢአት ከእግዚአብሔር ዕድል ፈንታ የሚያጎድለን ብቻ ሳይሆን ራሱን እግዚአብሔርን ሊያሳጣን ይችላል፡፡ትልቁ ገሀነም እግዚአብሔርን በህልውናው ማጣት ወይም የእግዚአብሔር ህልውናው ሳይሰማን ሲቀር ነው፡፡ሰው እግዚአብሔር እንዳለ ካልተሰማው የሚሰራውን ኃጢአት ድንበር አያበጅለትም፡፡ጌታ እግዚአብሔር ደግሞ መኖሩን የገለጠልን አለማትን ፈጥሮ ከመመገቡ በሚበልጥውድና አንድ ልጆች ለሰማያዊ ግብዣእንደሚታረድ በግ ሰውቶት ነው፡፡
    እግዚአብሔር ኃጢአታችን እንዲዋገድ ልጁን ሰውቶ የልጁን ደም የኃጢአታችን መደምሰሻ አድርጎ ደሙን ሰጥቶናል፡፡እንኪያስ የእኛ በጎነት ሳይሆን የልጁ ደም ኃጢአታችንን ዛሬም ሊያሥተሰርይ እንደቆመ እንመን፡፡የጠላትን የክስ ብዛት ሳይሆን ስለእኛ ሳይታክት መልካም የሚናገረውን የክርስቶስን የደሙን ድምፅ እንስማ፡፡
                      የክርስቶስ ደም!!!
ብርታት ነው    -   ያጸናል፡፡
ንጹህ ነው      -     ያነጻል፡፡
መድኃኒት ነው  -    ይፈውሳል፡፡
ብቃት ነው     -    በእግዚአብሔር ፊት ያቆማል፡፡
ህያው ነው    -      የሚሻለውን ሁሉ ስለእኛ ይናገራል፡፡
 ካሳችን ነው    -     መንግስቱን ያወርሰናል፡፡
አሜን፡፡እንዲህ እናምናለን ፡፡እንታመናለን፡፡
    በክርስቶስ ደም ኃይልና ጉልበት ተፈጸመ፡፡መመለክና ስግደት ኢየሱስ ተብለህ ለተወዳጀኸን ጌታ ላንተ ብቻ በሰማይና በምድር ይሁን፡፡አሜን፡፡

ዋቢ መጻህፍት


  • የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር(1962)መጽሐፍ ቅዱስ፡፡አዲስ አበባ፣ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፡፡
  • ሃይማኖተ አበው፡፡(1982)አዲስ አበባ፣ተስፋ ማተሚያ ቤት፡፡
  • መጽሐፈ ቅዳሴ ጕልህ፡፡(1994)፡፡አዲስ አበባ፣ትንሳኤ ማተሚያ ድርጅት፡፡
  • ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ ዘአፈወርቅ፡፡(1987) አዲስ አበባ፣ተስፋ ማተሚያ ቤት፡፡
  • ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡(1948 .)፤አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡
  • አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ አባ)፡፡(1996)፡፡ትምህርተ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ህይወት፡፡አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት(ማህበረ ቅዱሳን)፡፡
  • የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር(2002)፡፡የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9 እትም፣አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡
  • ኣማርኛ መዝገበ ቃላት፡፡(2001)፤አዲስ አበባ፣አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ ቤት፡፡
  • ዳንኤል ክብረት(ዲያቆን)፡፡አበው ምን ይላሉ?(1999)አሳታሚና አከፋፋይ ማህበረ ቅዱሳን፣ቦታ አልተጠቀሰም፡፡


No comments:

Post a Comment