Sunday 24 March 2024

ምኩራብ

 Please read in PDF

አይሁድ በምርኮ ዘመን መሥዋዕት የሚያቀርቡበት መቅደስ ስለ ፈረሰባቸውና፣ ወደ አገራቸውም ተመልሰው መሥራት ስላልተቻላቸው፣ በየጊዜው የሚገናኙበትንና ቃሉን በማንበብ፣ በመተርጐም የሚተጉበትን ምኵራብን መሥራት ጀመሩ። በምኩራብ ራቢ ወይም መንፈሳዊ መሪ ያለ ሲኾን፣ ሌሎች ደጋፊ ሰዎች ወይም ሠራተኞችን በተካተቱበት የሚመራ አነስተኛ ጉባኤ ነው።

ለአይሁድ ማኅበረ ሰብ ምኵራብ ማለት የአምልኮ ቦታና መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ነው። አስቀድሞ በግለሰብ ቤትም እንኳን የምኩራብ አገልግሎት ይካሄድ ነበር። ይሁን እንጂ የምኵራብ አገልግሎት ሕዝባዊ አጽዋማትም የሚካሄድበት በኅብረት የሚመገቡበት ሥፍራ ሲኾን በዋነኛነት ጸሎትና የእግዚአብሔር ቃል ንባብ ይካሄድበታል። በአይሁድ እምነት ጸሎትና የእግዚአብሔር ቃል ንባብ በጣም ከፍተኛ ነገር እንደ ኾነ ተደርጐ ይቈጠራል። “በየሰንበቱም ሁሉ በምኵራብ ይነጋገር ነበር፥” (የሐ.ሥ. 18፥4) እንዲል፣ በየሳምንቱ የአምልኮ ሥርዓቱ መደበኛ ሥርዓት ወጥቶለት ይካሄድ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ምኩራባት በጣም አስፈላጊ የኾኑ የትምህርት ቦታዎች ናቸው። የአይሁድ ልጆች እስኪጐለምሱ ድረስ ሕጐችንና ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚማሩበት ቦታ ነው። ከጐለመሱም በኋላ ቅዱሳት ጽሑፎችን እንዲያጠኑ፣ እንዲመረምሩና እና አይሁዳውያን በዕድሜያቸው ዘመን ሙሉ እንዲያማክሩ ይጠበቃሉ። ጌታችን ኢየሱስ፣ “አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብ” (ዮሐ. 18፥20) ሲል፣ አይሁድ ኹሉ በዚያ ቤት ይሰበሰቡ እንደ ነበር ነው፤ ከዚህም የተነሣ ቅዱሳት መጻሕፍት በምኩራብ ኹሉ ይነበብ ነበርና፣ አብዛኞቹ ምኵራቦች ቤተ መጻሕፍት አላቸው።

ምኵራብ ከቤተመቅደስ በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ማለትም በቦታ በሥርዐት እና በአገልጋዮች ይለያል። በመጀመሪያ እያንዳንዳቸውን በተናጠል እንመልከታቸው፦ ምኩራብ በየትኛውም ቦታ እንዲሠራ ይፈቀድ ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ከእስራኤል ምድር ውጭ አይሁድ ሲበተኑ በግሪክ-ሮም ግዛት ሁሉ ምኵራቦችን መሥራት እንደ ጀመሩ የሚታወቅ ነው። ምኩራብ የታነጸው በቅዱሱ ስፍራ ሳይኾን በየትኛውም ስፍራ በማንኛውም ስፍራ ነበር።

ኹለተኛው ልዩነት የሥርዓት ልዩነት ነው። የቤተ መቅደስ አምልኮ መሥዋዕት ነበረው። ይህ ማለት የእርድ እና የመጥበስ የመቀቀል ሥርዓት ነበረው። በጣም ብዙ ደም የሚበዛበት ሥራ ነበረው። በተቃራኒው በምኵራብ እንዲህ ዓይነት አምልኮአዊ ሥርዓት የለም።

ወደ ሦስተኛው ልዩነት ስንመጣ፦ ሥርዓቶቹን የሚያከናውኑ አገልጋዮችን እንመለከታለን፤ በቤተ መቅደሱ ለሕዝቡ ኹሉ ሥርዓቱን የሚያከናውኑ ካህናቱ ነበሩ። ጠቅላላ ሥርዓቱን የማከናወን ኃላፊነት ማለትም፣ ማረድ፤ ማቃጠል እና በአብዛኛው የአመጋገብ ሥርዓት የሚከናወኑት በካህናት ብቻ ነበር። እስራኤላውያን በጌታ ፊት ለማገልገል ይችሉ ዘንድ ቅዱሱን የመሥዋዕት ሥርዓት ማከናወን አልተፈቀደላቸውም።

ምኩራቦች ግን እጅግ ቀላል የኾነ አደረጃጀት ያላቸውና፣ ከመቅደሱ አገልግሎት ይልቅ፣ በምኵራብ የሚገኙ ኹሉ አገልጋዮች ናቸው፤ ኹሉንም ዓይነት ሥራዎች ማለትም [የቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ፣ ጸሎት እና የምስጋና መዝሙር …] ላይ ኹሉም (ሴቶችን ጨምሮ) ይሳተፉ ነበር።

ከምርኮ ዘመን በኋላ እስከ ጌታችን መምጣትና እስከ ሐዋርያት ወንጌልን በአይሁድ ከተሞች ኹሉ ማድረስ ድረስ፣ የነበረው የምኵራብ አገልግሎት፤ ለአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንም መልካም ምሳሌነት አለው፤ ምክንያቱም ኹሉም በአዲስ ኪዳን አማኞች ኹሉ፣ “በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን።” (ሉቃ. 1፥74) እንዲኹም፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።” (1ጴጥ. 2፥5) ተብሎ እንደ ተነገረው አማኞች ኹሉ አገልጋይ ካህናት ናቸውና፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ማንበቢያ፣ ማጥኛ፣ ጸሎት ማድረጊያ … “ምኵራብን” በየቦታው ሊያበዙ ይገባቸዋል። 

1 comment:

  1. አሁንም እግዚአብሔር አምላክ እድሜና ጤና አገልግሎትህንም ያብዛልህ ተባረክልን እንወድሃለን

    ReplyDelete