Friday 8 March 2024

ኢየሱስ እስኪመጣ - ላለፉት አሥራ አንድ ዓመታት!

 

የማይዋሸውና (ቲቶ 1፥2) በምሕረቱ ባለጠጋ የኾነ እግዚአብሔር (ኤፌ. 2፥4)፣ ነፍሴም ሕያው ወደ አደረጋት ሕያው አምላክዋ ሳትመለስ (መክ.12፥7) ኢየሱስ እስኪመጣ ድረስ ዕንኾ፣ አሥራ አንድ ዓመታት በብሎግ(በጡመራ መድረክ) አገልግሎት በጌታ ፊት አለኹ! በዚህ አጭር ዘመኔ ከእርሱ በቀር የረዳኝ፣ ያጸናኝ፣ ከፍ ከፍ ያደረገኝ፣ ሞገስ የሰጠኝ፣ ብርሃኑን ያበራልኝ፣ ስጠወልግ ያለመለመኝ፣ ስደክም መንገድ አቋርጦና አሳብሮ መጥቶ ያበረታኝ፣ እጆቼን ይዞ “አይዞህ!” ያለኝ ከጌታ በቀር ማንም የለም፤ ክብር ይኹንለት!

በእነዚህ ጊዜያት ይህ አገልግሎት እንዲሰፋ፣ ለብዙዎችም እንዲደርስ በጸሎት፣ ዐሳብ በመስጠት፣ ርዕስ በማቀበል፣ የብርዔ ቀለሙ እንዳይነጥፍ ላተጋችሁኝ፣ በገንዘብ ለረዳችሁኝ፣ መጻሕፍትን የጠቈማችሁኝ … ስማችሁን መጥቀስ ዋጋችሁን ማሳነስ የሚኾንብኝ ወዳጆቼ ኹሉ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊው በረከት አብዝቶ፤ የእጆቻችሁን ሥራ የአእምሮችሁን ዐሳብ ኹሉ በጸጋው አትረፍርፎ ይባርካችሁ! አሜን!

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ “… የክርስቶስን ምሥጢር እንድንነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤ ልናገር እንደሚገባኝ ያህል እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ።” (ቈላ. 4፥3-4) ብሎ የቈላስይስ ቤተ ክርስቲያንን “የጸሎት ደቦ” እንደ ተማጠነው፣ እኔም በጌታ ዘወትር የበረታኹ እኾን ዘንድ በጸሎታችሁ አስቡኝ፤ የቀኝ እጁ ረድኤት ትረዳኝም ዘንድ በጌታ ፍቅር ጸልዩልኝ!

  “ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

No comments:

Post a Comment