Sunday 17 March 2024

የ“ነቢይ” ጥላሁን ነገረ ማርያም!

 Please read in PDF

የ“ነቢይ” ጥላሁንን የተወሰኑ ስብከቶችን የማድመጥ ዕድል አጊኝቼ አውቃለሁ፣ በኋላ ግን እርሱም “በግሉ” ወደ “ቸርች ከፈታ” ሲያዘነብል ተደንቄ ራቅኹት። ከሰሞኑ ደግሞ ስለ ማርያም የተናገረውን አይቼ፣ የነዶክተር ወዳጄነህንና የነፓስተር ቸሬን መንገድ ለመከተል ምን አደከመው? ብዬአለሁ። በስብከቱ መካከል ማርያምን (የጌታ ኢየሱስን እናት) “እየሰበከ” በመካከል እንዲህ ይላል፣

 " ... የወንጌላውያን ጸሐፊዎች [አራቱ ወንጌላትን ማለቱ ነው] የማርያምን ኹኔታ ስላላወቁና እርሷም ምናልባት አብራርታ ስላልነገረቻቸው እንጂ ... መለኮት ልትወልጂ ነው ሲላት …" ይላል፡፡



የእኔ ጥያቄዎች፣

  1. “የማርያምን ኹኔታ ስላላወቁ” ማለት ምን ማለት ነው? ቅዱሱን መጽሐፍ ሲጽፉ፣ መንፈስ ቅዱስ ነዳቸው (2ጴጥ. 1፥20-21) ካልን፣ ወንጌላውያን መንፈስ ቅዱስ ያዘዛቸውን ብቻ እንጂ ሌላ ምንም ማድረግ አይችሉም። ስለ ማርያም ጻፉ ያላቸውን የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ ሰምተው ጽፈዋል፤ ሌላ ኹኔታ አልያም አላዋቂነት አለ ብሎ ማሰብና ማስተማር የነዳቸውንና የመራቸውን መንፈስ ቅዱስን የመንቀፍ ያህል ታላቅ ስንፍና ነው! “ነቢዩ” ሆይ፤ ወንጌላውያኑ የማርያምን ኹኔታ አለማወቃቸው ከቅዱሳት መጻሕፍት መልእክት ምን ጐደለ? ስለ ማርያም በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈው በቂ አይደለምን? መጽሐፉ የተናገረውን ተቀብለን ያልተናገረውን ዝም ማለት አይሻለንም ወይ?
  2. መጽሐፍ ቅዱስን የሚጽፉ ወንጌላውያን፣ ማርያም ብዙ ማብራሪያ ስለ ራስዋ ብትሰጥና ቢጽፉ መጽሐፍ ቅዱስ ሰው፤ ሰው በሸተተ ነበር፤ እግዚአብሔር የቅዱሳንን ሕይወት እንዲገለጥ ወይም እንዲጻፍ ያደረገው፣ ክብሩን ለመግለጥና ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ ይጠቅም እንደ ኾን ብቻ እንጂ አንድን ቅዱስ ገናና ለማድረግ አይደለም! እናም “ነቢዩ” ሆይ፤ ማርያም ስለ ራስዋ “ሰፋ ያለ ገለጣ” ለወንጌላውያኑ ብትሰጥ፣ ወንጌላውያኑ የማርያምን ገለጣ ወይስ የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ ብቻ የሚሰሙ ይመስልሃል?!
  3. መልአኩ ገብርኤል፣ ቅድስት ድንግል በሥጋ ኢየሱስን በፍጹም ሰውነቱ እንደምትወልድ እንጂ መለኮትን እንደምትወልድ ብሥራት አላበሠራትም፤ እንዲህ ብለው የሚያስተምሩ ካራ ኦርቶዶክሳውያን ናቸው። “ነቢዩ” ሆይ፤ ማርያም ኢየሱስን በሥጋ ብቻ የወለደች አይደለምን?

አንዳንዴ መሃል ሰፋሪ ለመኾንና ብዙዎችን ለማስደሰት ብለን የምንሰብከው ስብከት በወንጌሉ እንድንሸቅጥ ያደርገናል፤ እናም ካራ ኦርቶዶክሳውያንን ለማስደሰትና ደጋፊ ለማግኘት ባንቀማጠል መልካም ነው፤ ስለ ቅድስት ማርያም መጽሐፉ የሚለውን ብቻ ማለት ታላቅ ማስተዋል ነው፤ መጨመር ግን መንፈስ ቅዱስን ለማረምና ለማረቅ የሚደረግ ብርቱ ድፍረት ነው!

አዎን፤ ቅድስት ድንግል ኢየሱስን በሥጋ ወልዳለች፤ ደግሞም ይህን ያደረገ የእግዚአብሔር ታላቅ ምሕረትና መለኮታዊ መግቦት፤ ከጥንት ለሰው ልጅ ያሰበው የቤዝወት አንድ መንገዱ እንጂ ለማርያም የተለየ ምስጋና ማቅረቢያ ማወደሻ አይደለም፤ እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርስዋ የተናገረው “ያመነች ብጽዕት ናት”፣ በዚህም ታላቅ ተግባር ውስጥ ትውልድ ብጽዕት ወይም የተለየች ይላታል ይላል እንጂ፣ ወንጌላውያኑ በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን በጻፉት ታላቁ መጽሐፍ፣ ማብራሪያ ብትሰጥ የሚል አንድም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የለም! መጽሐፉ የተናገረውን እንናገራለን፤ ካልተናገረ አብረን ዝም እንላለን እንጂ እንዲህና እንዲያ እያለን አስተያየት አንሰጥም፤ ነውር ነው!

1 comment:

  1. አንዳንዴ መሃል ሰፋሪ ለመኾንና ብዙዎችን ለማስደሰት ብለን የምንሰብከው ስብከት በወንጌሉ እንድንሸቅጥ ያደርገናል!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

    ReplyDelete