“የዛሬን አያድርገውና” ዲያቆን ትዝታው ሳሙኤል፣ ለድንግል ማርያም “ከዘመራቸው ዝማሬዎች” መካከል “የአሚናዳብ
ሠረገላ” የሚል ይገኝበታል። ብዙ አገልጋዮች ከኦርቶዶክስ አገልጋይነታቸው ራሳቸውን አግልለው ወደ ወንጌል እውነት ሲመለሱ፣ አስቀድሞ
“ለፍጡራን በግልጥ የዘመሩትን ዝማሬ” በትክክል ስህተት መኾኑን አምነው፣ ንስሐ ሲገቡ አላየኹም፤ ምናልባት የገቡ ካሉና መግባታቸውም
እንደ ዝማሬያቸው አደባባያዊ ከኾነ እንዴት መልካም ነበር!
ወደ መልእክቴ ዐሳብ ልመለስና፣ ስለ አሚናዳብ ሠረገላ አንድ ነገር ማለትን ግን ወደድኹ!
የእስራኤል ልጆች ኃጢአትን በማድረጋቸው ምክንያት፣ የኪዳኑ ታቦት በፍልስጥኤማውያን
ተማረከ፤ ይህ በመኾኑም ክብር ከእስራኤል ለቀቀ (1ሳሙ. 4፥22)፤ ታቦቱም ተማርኮ
ለሰባት ወራት ከተቀመጠ በኋላ (5፥1)፣ ፍልስጥኤማውያን ታቦቱን ሊመልሱ ወደዱ። ምክንያቱም አስቀድሞ ከአምላካቸው ከዳጎን ጋር
ቢያስቀምጡት፣ አምላካቸውን ፈጠፈጠባቸው (5፥2-5)፣ እነርሱም በእባጭ ለመመታታቸው ምክንያት ኾነ (5፥6-12)፤ ከዚያም እንደ
ጣዖት ልማዳቸው ታቦቱን ለመመለስ ፈለጉ፤ እናም ለእስራኤል ልጆች በሠረገላ አድርገው ታቦቱን ሰደዱላቸው (6፥1 ጀምሮ)፤ ነገር
ግን የቤት ሳሚስ ሰዎች ታቦቱን በመመልከታቸው ተቀሰፉ!
እናም የእግዚአብሔር ታቦት በቂርያትይዓሪም በአሚናዳብ ቤት ለ20 ዓመታት ያህል
ተቀመጠ (1ሳሙ. 7፥2)፤ ከ20 ዓመታት በኋላ ንጉሥ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል
ሲነሣ፣ ታቦቱን ወደ ተወደደችው ከተማ ጽዮን ማምጣት ወደደ። ከዚያም፣
“የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑ፥ በኮረብታውም ላይ ከነበረው
ከአሚናዳብ ቤት አመጡት፤ የአሚናዳብ ልጆችም ዖዛ እና አሒዮ አዲሱን ሰረገላ ይነዱ ነበር።” (2ሳሙ. 6፥3)
ይላል።
በአሚናዳብ ሠረገላ የተጫነውን ታቦት የተሸከሙት ላሞች እየፋነኑ ሲሄዱ፣ ድንገት የአሚናዳብ ልጅ ዖዛ፣ ታቦቱ
የሚወድቅ መስሎት በመደገፉ ተቀሰፈ! ዳዊት በዚህ ጉዳይ እጅግ ተደናገጠ፤ ታቦቱንም መውሰድ ትቶ እንደገና ታቦቱ ወደ አሚናዳብ ቤት
ተመለሰ (6፥10)።
እንግዲህ ይህን ታሪክ ነው ቀጥታ በምሳሌነት ለድንግል ማርያም የተሰጠው፤ ማለትም ታቦቱን የተሸከመው የአሚናዳብ
ሠረገላ የድንግል ማርያም ምሳሌ ነው በማለት። ነገር ግን የዚህን ታሪክ ክፍል እንደ ቅዱስ ቃሉ መልሰን በትክክል ብንፈትሸው፣ አያሌ
ስህተቶች አሉበት። አንዱንና ዋናውን ብንጠቅስ፦
- ዳዊትም ኾነ አሚናዳብ፣ የእግዚአብሔርን ታቦት
በሠረገላ ላይ እንዲጭኑ የሚያዝዝ የእግዚአብሔር ትእዛዝ የለም፤ ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል፣ ዳዊትን፦ “እንደ ሥርዓቱም አልፈለግነውምና አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን ስብራት አደረገ” በማለት በገዛ አንደበቱ የሚወቅሰው፤ (1ዜና. 15፥13)። ታቦቱን በተመለከተ የእግዚአብሔር
ሥርዓት፣ ሠረገላ ሳይኾን ሌዋውያን ራሳቸው በጫንቃቸው እንዲሸከሙት ነው ያዘዘው!
“በዚያን ጊዜ
የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ይሸከም ዘንድ፥ እርሱንም ለማገልገል በእግዚአብሔር ፊት ይቆም ዘንድ፥ በስሙም ይባርክ ዘንድ
እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ድረስ የሌዊን ነገድ ለየ።” እንዲል (ዘዳግ. 10፥8፤ በተጨማሪም ዘኊ. 4፥5-6፥15 ይመ.)
ዳዊትም ይህን እውነት በፍጻሜው ባስተዋለ ጊዜ እንዲህ ብሎ አዘዘ፤
“በዚያን ጊዜም ዳዊት፦ የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከሙ ዘንድ፥ ለዘላለሙም
ያገለግሉት ዘንድ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር ማንም የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከም ዘንድ አይገባውም አለ።” (1ዜና.
15፥2)።
እንግዲህ
ዳዊትና አሚናዳብ የእግዚአብሔርን ታቦት በሠረገላ በመጫናቸው ትልቅ ስህተት ሠርተዋል፤ ትክክልም አልነበሩም። ታቦቱን፣ ሌዋውያን
እንዲሸከሙት እንጂ እንደ ጣዖት አምላኪያን ልማድ በሠረገላ እንዲጫን (1ሳሙ. 6፥7) እግዚአብሔር አላዘዘም፤ እስራኤል(ዳዊትና
አሚናዳብ) ምንም እንኳ እግዚአብሔርን ለማገልገል እጅግ ቢጓጉም፣ እግዚአብሔር የሚገለገለው እንደ ሕጉና ሥርዓቱ ብቻ እጅግ ከፍ
ባለ ጥንቃቄ እንጂ ከአሕዛብ ወይም ከዓለማዊያን በተቀዳ ሥርዓት ፈጽሞ አይደለም። እግዚአብሔር በዚህ እስራኤልን (ዳዊትንና አሚናዳብን)
ፈጽሞ አስጠነቀቀ (ዘሌ. 10፥1-3፤ ኢያ. 7፥24፤ 24፥19፤ የሐ. ሥ. 5፥1-11)።
ታድያ
ይህን እውነተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከተረዳን፣ በአሕዛብ ልማድ ታቦቱን በሠረገላ መጫን የሚነቀፍ እንጂ የሚወደድ ምሳሌ የለውም!
ድንግል ማርያምን፣ ተወዳጅ የጌታችን ኢየሱስን እናት፣ የመጀመሪያዪቱን የአዲስ ኪዳን አማኝ፣ ለአምላክዋ ራስን ባሪያ በማድረግ ያቀረበችውን
ብላቴና … መልካም ምሳሌነት በሌለው “በአሚናዳብ ሠረገላ” መመሰል አግባብ ነውን? ወደ ቃሉ እንመለስ!
No comments:
Post a Comment