Thursday 7 March 2024

መንፈሳዊውን ጾም እንጹም!

Please read in PDF

ጾም፣ በብሉይም ኾነ በአዲስ ኪዳን አማኞች ዘንድ፣ በጐላ መልኩ ሲተገበር የነበረ ደግሞም ያለ መንፈሳዊ ልምምድ ነው። ጾም በአማኞች ሕይወት እንደ መለኮታዊ ተግሳጽ የሚፈጸም መንፈሳዊ አምልኮም ነው። በብሉይ ኪዳን ንስሐ ሲገቡ (1ሳሙ. 7፥6)፣ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ፣ ከእግዚአብሔር ዕርዳታ ለመፈለግ (ዘጸ. 34፥28፤ ዕዝ. 8፥21-23)፣ ራስን በመንፈሳዊ ተግሳጽ ለመገሰጽና የኀጢአት ኑዛዜ በእግዚአብሔር ለማቅረብ መንፈሳውያን ሰዎች በግል (2ሳሙ. 12፥22) ወይም በማኅበር (መሳ. 20፥26፤ ኢዩ. 1፥4) በእግዚአብሔር ፊት ይጾሙ ነበር!

ጾም፣ ለተወሰነ ጊዜ ራስን ከምግብ፣ ከኀጢአት መጠበቅ ወይም ከኀጢአት ጋር መጋደል እንዲሁም ከሌሎች ነገሮች ራስን መከልከል ነው። ከምግብ ስንል ከጥሉላት ምግቦች ብቻ አይደለም፤ ከኹሉም እንጂ። በአገራችን ባለው የጾም ልማድ፣ ሰዎች ጥሉላት ነክ ከኾኑ ምግቦች ብቻ ሲታቀቡ፤ የጥሉላት ንክኪ ያለባቸውን ዕቃዎቻቸው ጭምር ሲሸሹ እንመለከታለን። ለምሳሌ፦ ሥጋ ከነካው ቢላዋ ወይም ወተት ከተቀዳበት ብርጭቆ ወይም መረቅ ከነካው እንጀራ የሚጾሙ ለሌላው ነገር ግን ግድ የሌላቸው ብዙዎች ናቸው፤ ይህ ግን ሃይማኖታዊ ግብዝነት ነው!

መጽሐፍ ቅዱስ ነቢያትና ሐዋርያት እንዲኹም የነቢያትና የሐዋርያት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጭምር እንደ ፆሙ ይነግረናል። በተለይም ጌታችን ኢየሱስ እንዴት መጾም እንዳለብን ሲናገር፣ “ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።” (ማቴ. 6፥16) ብሎአል፤ ጌታችን ኢየሱስ መጾም እንዳለብን ሲናገርም እንዲህ ይላል፣ “አንተ ግን ስትጦም፥ …”፣ እንግዲህ አማኞች ኹሉ ልንጾም ይገባናል፤ ለዚህም ከላይ እንደ ተናገርነው አያሌ አብነቶች አሉን፤ ሊቀ ነቢያት ሙሴ (ዘጸ. 34፥28፤ ዘዳ. 9፥9፡19)፣ እስራኤል (ዘሌ. 16፥29-31፤ ዘካ. 8፥19)፣ የቴስቢው ነቢይ ኤልያስ (1ነገ. 19፥8)፣ ነህምያ (ነህ. 1፥4)፣ ዕዝራ (ዕዝ. 8፥23)፣ ዳንኤል (ዳን. 10፥2-3)፣ እነ መርዶክዮስ (አስ. 4፥16፤ 9፥31)፣ የነነዌ ሰዎች (ዮና. 3፥5)፣ ቅዱስ ጳውሎስ (2ቆሮ. 11፥27)፣ ቅዱሳን ሐዋርያትና (ማቴ. 9፥14፤ ማር. 9፥29፤ ሉቃ. 2፥37፤ የሐ.ሥ. 13፥2-3፤ 14፥23) ሌሎችም።

የምንጾመው አንዳንዶች እንደሚሉት፣ የዳንንበትን ጸጋ ለመካድ ወይም ራሳችንን ወደ ሕግ ቀንበር ለማስገባት አይደለም፤ ይልቁን በእግዚአብሔር ጸጋ እጅግ በመደገፍ፣ ራሳችንን ለጌታ ይበልጥ ለማስገዛት፣ ነፍሳችንን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ በትህትና በፊቱ ለመመላለስ፣ በእግዚአብሔር ፊት ብዙ ጊዜ ለመቆየት፣ ፊቱን አብዝተን በመፈለግ በጸሎት ለመትጋት በተለይም ደግሞ የማኅበር ጾም ሲኾን የመንፈስ አንድነትንና መንፈሳዊ ዕድገትን በመፈለግና በመናፈቅ ነው።

-     ስንጾም እንደ ዳንኤል ከማናቸውም ከቅንጦት፣ ከጣፋጭ፣ ከሚለደልዱ ምግቦች መራቅ ይገባናል፤ ነገር ግን ዕድሜና የጤና ኹኔታ ቢታሰብበት መልካም ነው!

-     አማኞች ሲጾሙ ጊዜያቸውን ከምንም ነገር በላይ ቃለ እግዚአብሔር በማንበብና በጸሎት ሊያሳልፉ ይገባቸዋል (ዕዝ. 8፥23፤ ማቴ. 17፥21፤ ሉቃ. 2፥37)

ስለዚህም ጾምን በልማድ ብቻ ከሥጋና ከእንሰሳት ተዋጽኦ ብቻ በመከልከል፣ ከኀጢአትና ከርኩሰት ሳይርቁ መጾም አግባብ አይደለም፤ ለጌታ ከጾምንና ጾም መንፈሳዊ አምልኮ መኾኑን ከተረዳን፣ ይልቅ እየወደድን ልናደርገው የሚገባንና እንደ ቃሉም በመመላለስ ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን ብቻ ልናከብርበት ይገባናል፤ አማኞች ክርስቶስን ለመከተል ከጨከኑና ከእርሱ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍን ከወደዱ፣ መንፈሳዊ ጾምን እንዲወድዱ እንመክራለን!

  “ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

2 comments:

  1. Amen amen amen!

    ReplyDelete
  2. ጌታ ኢየሱስ አብዝቶ ይባርክህ ፀጋው በዘመንህ ሁሉ አይለይህ

    ReplyDelete