እግዚአብሔር የሰማይና የምድር ፈጣሪ ነው፤ “እነሆ፥ ሰማይ
ሰማየ ሰማያትም፥ ምድርም በእርስዋም ያለው ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር ነው።” (ዘዳግ. 10፥14) እንዲል፣ ከእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ያልኾነ ፍጥረት ፈጽሞ የለም። በአዲስ ኪዳንም፣
“እርሱ[እግዚአብሔር]
በክፎዎችና በበጐዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።” (ማቴ. 5፥44-45) በሚለው ንግግሩ እግዚአብሔር ለመላለሙ ግድ ይለዋል።
ለእግዚአብሔር አገልጋዮች ግን ይህ እውነት ዘወትር የተገለጠ አይደለም፤ ምሳሌ
ብንጠቅስ ነቢዩ ዮናስን በምሳሌነት መጥቀስ እንችላለን፤ እግዚአብሔር፣ ዮናስን፣ “ተነሥተህ
ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ።” (ዮና. 1፥2) ቢልም፣ ዮናስ ግን፣ “ዮናስ ግን
ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ይኰበልል ዘንድ ተነሣ፤”
(ዮና. 1፥3) ይለናል።
በሌላ ስፍራም፣ እግዚአብሔር ነነዌን በማዳኑ ዮናስ ፈጽሞ ደስተኛ አልነበረም፤
“አንተ
ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ
ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር።” በማለትም በቍጣ ቃል ተናገረ፤
(4፥2)። እግዚአብሔር አሕዛብን መቅጣት እንዳለበትና ደግሞም ሳይቀጣ ቍጣውን መልሶ እርሱን ሐሰተኛ በማድረጉ ዮናስ እጅግ ተናደደ።
በርግጥ የአሦርዋ ከተማ ነነዌ፣ በጭካኔያቸው ወደር የሌላቸውን ወታደሮች የያዘች
ናት፤ በዚያን ዘመን ነነዌና አሦር ለጠላቶቻቸው በሚያሳዩት የጭካኔ ተግባር ማለትም፣ ጠላቶቻቸውን በሕይወት ሳሉ መቅበር፣ ቆዳቸውን
መግፈፍ፣ ከነሕይወታቸው ለጨካኝ አራዊት መስጠት፣ ምላሳቸውን ጐልጕሎ በማውጣት ማሰቃየትና ሌሎችንም ጭካኔ የተመላባቸውን ተግባራት
ይፈጽሙ እንደ ነበር ዮናስ ያውቅ ስለ ነበር ወደ እነርሱ መሄድን አልወደደም፤ እናም እንዲህ ላሉ ጨካኞች የእግዚአብሔርን ዐሳብ
ሊያካፍል አልፈለገም!
እግዚአብሔር የጨካኞቹን የነነዌ ሰዎች ልብ አዘጋጅቶ ነቢዩን ወደዚያ ቢልከውም፣
ዮናስ ግን ለእግዚአብሔር ዐሳብ ራሱን ማዘጋጀት አልፈለገም ወይም አልወደደም። በዮናስ ልብ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ብቻ
ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የመላለሙ እንጂ የእስራኤል አምላክ ብቻ አልነበረም፤ (3፥10፤ 4፥2፡ 11)። እግዚአብሔር ለመላለሙ
ያለውን የቤዝወት ልብ ሲናገር እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው
እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐ. 3፥16)፣ “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ
ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤”
(1ጢሞ. 1፥15)።
እግዚአብሔር ርኁሩኅ ነው፤ እግዚአብሔር ጨካኞቹና በኀጢአታቸው ታዋቂዎቹ የነነዌ
ሰዎች እንዲጠፉ አልወደደም ዳሩ ግን እንዲመለሱ ዕድል ሰጣቸው። ዮናስ ምንም በተደጋጋሚ ቢቈጣም፣ እግዚአብሔር ግን በትጋት አንድን
የአሕዛብ ከተማ ለማዳን በብርቱ ሲጥር እንመለከታለን።
እግዚአብሔር ለተጣሉትና ለተናቁት ኀጢአተኞች፣ ለተገለሉና አገልጋዮች እንኳ ለማይፈልጓቸው ሕዝቦች ወይም አንድ ሰው የበዛ ምሕረትና የሚፈልግ ልብ አለው፤ ስሙ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤ አሜን።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ.
6፥24)።
No comments:
Post a Comment