Thursday 1 June 2017

ዘፈን - የወደቀው መልአክ እንጉርጉሮ (ክፍል 4)

Please read in PDF

የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ዘፈንን በኀጢአትነቱ ገልጠዋል፤

   የቤተ ክርስቲያን አባቶች ስንል እንዲሁ ከምንም ነገር ተነስተን አይደለም፡፡ እኒህ አባቶች ለእውነተኛው የክርስትና ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ ቆመው ዋጋ የከፈሉ በመሆናቸውና ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት “በመሟገታቸው” ነው፡፡ ትምህርቶቻቸው፣ ምክሮቻቸው፣ ተግሳጾቻቸው ብቻ ያይደለ የሕይወታቸውም ቅድስና ጭምር የተመሰከረላቸው፣ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነትና የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን አምነው የተቀበሉና በዚህም መሠረትነት ላይ ቆመው የጻፉ መሆናቸውን በመመዘን የምንቀበላቸው ናቸው፡፡
   ከእነዚሀ ቅዱሳን አባቶች መካከል ዘፈንን በግልጥ የተቃወመውና እንድንርቀው ያስተማረን አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡  ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በተግሳጹ እንዲህ አለ፣ “ስለዚህ … ዘፈንን ትተዉ ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡ ኀላፊ የሚሆን ፈቃደ ሥጋን ተዉት ብዬ እማልዳችኋለሁ፡፡ ሲዘፍኑ ላደሩት ጧት ለዋሉት ማታ መሸታ መግዛትን ተው ብዬ እማልዳችኋለሁ፡፡”[1] “ዳግመኛም ሲሰስን እንዳየኸው ጋሬዳ፤ ዘፈን፤ ጨዋታ፤ መሸታ ወዳለበት ሲሔድ ብታየው፡፡ ይህንንም ይተው ዘንድ መላልሰህ ማልደው፡፡”[2]

    ዘፈንን አስመልክቶ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የተናገራቸው ቃላት፣ ግልጥና የዘፈንን ኃጢአትነት በማያሻማ መልኩ የተነገሩ ናቸው፡፡ በተግሳጹም ዘፈንን እንዲተው፣ እንደዘፈን ካለ ሥጋዊ ተድላ እንዲርቁ፣ ከመሸታና ተመሳሳይ ሥፍራዎች እንዳይሄዱና የሚሔዱትንም እንዲከለክሉ ይናገራል፡፡ እርሱ ባለማሸፈን የተናገረውን ይህን እውነትና ሌሎች እንዲህ ያሉትን ምንባባት ሽረው የዘፈንን ቅድስና ሊነግሩን የመፈለጋቸው ሃሳብ ከማን እንደሆነ አንስተውም፡፡
      ፍትሐ ነገሥት በግልጥ ቃል፣ “ስለተግባረ ዕድ ግን በዓለም ከሚሠሩ ሥራዎች መንፈሳዊ ሕግን ከሚቃወም ሥራ በቀር ሁሉንም ሊሠሩ ይገባል፡፡ … እንደዘፋኝነት፣ እንደመጥፎ ጨዋታ፣ በእግር እንደማሸብሸብ[3] ካልሆነ በቀር ነው፤ … ጣዖትን የሚሠራ ሰው ሁሉ ለጣኦት እንዚራ የሚመቱና የሚዘፍኑ … ሁሉ ከዚህ ሥራ ይከልከሉ፡፡ አለዚያም ከምዕመናን ይለዩ፡፡“[4] ይላል፡፡ እነሰርጸ እኒህን ምንባባት አላነበቡም ወይም ማንበብን አይፈልጉም፡፡ ቢያነቧቸው ወይም እንዲህ ያሉትን ትምህርቶች ለማስተዋል ቢታደሉ አሁን እየተናገሩት ባለ ኃጢአታዊ ድፍረት ባልተያዙ ነበር፡፡
   ከዚህም በላይ የሚከፋው ነገር ደግሞ፣ ይህ የፍትሐ ነገሥት ቃል በዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ ከተሻሩ ሕግጋት መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ምክንያቱም በአደባባይ የምናውቃቸውና ትውልድን በየመሸታና የሌሊት ጭፈራ ቤቶች እንዲሁም በድምጽና በምስል የሚዘፍኑና የሚጨፍሩ ዘፋኞች ንስሐ ሳይገቡና አንዳች የይቅርታ ቃል ከአፋቸው ሳይወጣ ያለምንምና ማንም ከልካይ በየዓውደ ምሕረቱ ተጋብዘው ሲያገለግሉ እያየን ነውና፡፡[5]  እናም ቤተ ክርስቲያን ልታስተካክል ከሚገባቸው ግንባር ቀደም ነገሮች አንዱ ከኃጢአተኞች[ከሥጋውያን ዘፋኞች] ጋር ያላትን “ሽርክናዊ ግንኙነት” ነው፡፡ የዘፋኞቹን አሥራት በኩራት ከመፈለጋችን በፊት፣ እግዚአብሔር የሚፈልገው በንስሐ የሚመለሰውን ማንነታቸውን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
  
በእስራኤል ልማድ ስለተዘፈነ አንዘፍንም፤

    ስለዘፈን ሲነሳ፣ አብዛኛዎቹ ዘፈን ደጋፊዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሱትና የሚያነሱት፣ ዳዊት ዘፈነ፣ እስራኤላውያን ጨፈሩ፤ እኛስ ብንጨፍር? የሚለውን ማንደርደርያ ጥያቄ ለማንሳት የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን ይጠቅሳሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን “ስንተረጉም” ዘወትር ማስታወስ ያለብን ነገር አለ፤ እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ሰው እንደመጻፉ መጠን ብሉይ ኪዳን በአብዛኛውና አዲስ ኪዳን በከፊል በዕብራውያን ወግና ባህልና ሲሆን፣ አዲስ ኪዳን ደግሞ በአብዛኛው በግሪክና በተወሰነ ረገድ በሮማውያን ወግና ባህል ውስጥ ነው፡፡[6]
     ሌላው ስንተረጉም ማስታወስ ያለብን ነገር፣ የተጻፈው ሁሉ፣ “ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀን እንሆን ዘንድ፥ … ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” ነው፤ (2ጢሞ.3፥16-17) ነው፡፡ ይህንን እውነት ግን ወደሥራ ስንተገብረው ከእግዚአብሔር ቀጥታ ለእኛ መነገሩንና በዚያ ባህል ውስጥ የተከናወነ ድርጊት መሆኑን ለይተን ማስተዋል አለብን፡፡ አስተውሉ! በዕብራውያን፣ በግሪካውያንና በሮማውያን ቢጻፍም የእነርሱን ባህል እንድንከተል ግን አልተባልንም፡፡
   የአዲስ ኪዳን አማኞች በክርስቶስ ኢየሱስ የተጠሩ ልዩና ቅዱስ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ስለዚህም በአዲስ ኪዳን አስተምኅሮ ኀጢአት የሚተረጎመው ወይም የሚታየው በድርጊታዊነቱ ብቻ አይደለም፡፡ “በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ” (2ቆሮ.11፥2-3)፤ እንዲል፣ ሃሳብን መመረዝ ለድርጊት ከግማሽ መንገድ በላይ የመሄድ ያህል ነው፡፡ ሔዋን ከድርጊት በፊት የተመረዘው ሃሳቧ ነበር፤ ጌታ ኢየሱስም፦ “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” (ማቴ.5፥28) አለ፡፡ አስተውሉ! ዓይቶ መመኘትና በልብ ማሰላለሰል ድርጊት አልባ፣ ግን ነፍስን መራዥ ክፉ ነገር ነው፡፡
     ጌታ ትኩረቱና ዓላማው፣ “እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ” (ኤፌ.5፥27) ነው፡፡ ለዚህም ነው ዘፈን ኀጢአታዊ ሃሳብና መንፈስን በካይ፣ መራዥ፣ አርካሽ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት በምልአት የሚመሰክሩት፡፡ ሰርጸና ባልንጀሮቹ ይህን የአዲስ ኪዳን ክፍል መናገር አይፈልጉም፤ ስለዚህም ስለኀጢአት ያላቸው እሳቤ ደካማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የራቀ ኢ አመክንዮታዊ ነው፡፡ ዘፈንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለማድረግ ከጣሩበት ጥረት ይልቅ፣ በአዲስ ኪዳን ኃጢአት ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ ትንሽ ቢያሰላስሉ እውነታውን ለማግኘት በታደሉ ነበር፡፡ ምክንያቱም ደግሜ እላለሁ፣ እንኳን ኀጢአት የሆነ ነገር ይቅርና መልካም ነገር እንኳ እግዚአብሔርን ካለከበረና ለሰው መንፈሳዊ ሕይወት ካልጠቀመ በራሱ ኀጢአት ነውና፡፡
  አቤቱ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ለትውልዱ ማስተዋልን አብዛ፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …




     [1] ተግሳጽ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፤ 1987 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ተስፋ ማተሚያ ቤት፡፡ ገጽ.326
     [2]  ዝኒ ከማሁ ገጽ.351
      [3] እንደመጥፎ ጨዋታ” የተባለው ስሜት ቀስቃሽ፣ አባባሽ ዝሙታዊ ንግግሮችንና ዘፈኖችን ይሆንን? “በእግር እንደማሸብሸብ” የሚለው ደግሞ ምናልባት ዘመናዊውን ዳንስ የሚመስል በእግር የመሽከርከርንና የመደነስን ሃሳብ በውስጡ የያዘ ይመስላል፡፡
   [4] ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ.23 ቁጥር 820 እና 822፡፡
    [5] አንዳንድ “የዋሐንና” የክርስትናን እውነተኛ ትምህርት ያልተረዱና የእግዚአብሔርን አምርሮ ኃጢአትን ጠይነት ያልተረዱ ወገኖች እነርሱ ንስሐ ገብተው ቢሆን በምን እናውቃለን? ስለዚህ ዝም ማለት ይሻለናል፤ ፈራጅ መሆን አይገባንም ሲሉ እሰማለሁ፡፡ ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍት ስንመረምር ይህ እውነት ግልጽና ምንም የማያሻማ ነው፡፡ እንኳን ዘፈንን በሚያህል እግዚአብሔርን በማያከብርና ለሰው በማይጠቅም ነገር ይቅርና መልካም ሆኖ እግዚአብሔርን በማያከብር ሥራችን ወንድም የሚሰናከልብንና እኛ ከቅድስና የምንጎድል ከሆንን ከዚያ ነገር በመራቅና መራቃችንንም በሚታይ ሥራና በተገለጠ ንስሐ ልናቀርበው ይገባናል፡፡
    ዘፈን ኃጢአትነቱ ለዘፋኙ ብቻ አይደለም፡፡ ሰምተው ከእርሱ ጋር የሚሳተፉትንም ጭምር የሚያካትት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ዘፋኝ ንስሐ ሲገባ የእርሱን ዘፈን ሰምተው ከእርሱ ጋር አብረው የወደቁትን ንስሐ በመግባት ይቅርታ መጠየቅ፤ ያ ዘመን የውድቀት ዘመኑና እግዚአብሔርን ያላከበረበት ዘመኑ መሆኑን በግልጥ ምስክርነቱ ሊናገረው ይገባዋል፡፡ በግልጥ የሠራነውን ኃጢአትና በደል ማረምና ማስተካከል በግልጥ በአደባባይና ያሰናከልናቸውም ሰዎች እንዲመለሱ ሊጋብዝ በሚያስችል መንገድ መሆን መቻል አለበት፡፡
[6] ለምሳሌ፦ በማቴ.25፥1-13 የተጠቀሰው የጋብቻ ባህል፣ በዮሐ.10፥5 ላይ እረኛን በጎች የመከተላቸው ሁኔታ፣ በማር.2፥4 ላይ ያለው ጣርያና ግድግዳን ለያይቶ ቤትን መገንባት፣ እንደእስራኤላዊ ያለ አለባበስ(ቀሚስ መሳይ ጀለቢያ)፣ እንደእስራኤላዊ ያለ አመጋገብ(ለምሳሌ፣ እጅን በወጭት ማጥለቅ) … የዕብራውያን ባህልና ወግ እንጂ የእኛ አይደለም፡፡ ወይም እኛም እንድናደርገው መጽሐፍ ቅዱስ አያዘንም፡፡ እኒህንና ሌሎችን የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍሎችን ብናነሳ የድርጊቱን መከናወን እውነተኛነት ለመግለጥ የተጠቀሱ እንጂ፣ የነገሩን “ጊዜ አይሽሬነትና እኛም እንድንተገብረው” የሚያደርገን ምንም አምላካዊ ትዕዛዝ በውስጡ የለውም፡፡
    ከዚህ የተነሳ እስራኤላውን ቢዘፍኑ፣ ቢጨፍሩ … እንደባህላቸው ያደረጉት እንጂ እኛ እንድናደርገው የታዘዝነው አይደለም፡፡ ዳዊት በኪዳኑ ሕዝብና በኪዳኑ ጌታ ላይ ዘባች የነበረው ጎልያድን በመግደሉ ተዘፍኖለታል፤ ይህ የእስራኤል ሴቶች ባህልና ወግ ነው፤ ጸሐፊው ድርጊቱ መከናወኑን እንጂ እንድናደርገው በሚያዝዝ አንቀጽ አልጻፈልንም፡፡ የሰይጣን ንግግሮች ሳይቀሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፈዋል፤ ይህ ማለት የድርጊቱ የመከናወን እውነታነትን ያጎላል እንጂ፣ እርሱ የተናገራቸውን ቃላት እንድንናገራቸው አልተባልንም፡፡ ስለዚህም በሌሎች ቦታ ተዘፈነ፣ ተጨፈረ፣ ዘለሉ … የሚል ቃላትን ብናነብ ከዓውዱ ሳንወጣ የተነገረበትን ምክንያትና ለምን ዓላማም እንደተፈጸመ ከክፍሉ ልናነብ፣ በምን ዓይነት ባህል ውስጥ እንደተፈጸመም ልናስተውል ይገባናል ማለት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment