አለቃ
ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ሆነ ደስታ ተክለ ወልድም የዘፈንና የዘፋኝነትን ዓለማዊነት ወይም ኀጢአትነት በግልጥ አስቀምጠዋል፡፡ በመጽሐፎቻቸውም
በግልጥ ቃል፦ “ዘፊን፤ ኖት፤ (ዘፈን ይዘፍን ይዝፍን፡፡ ዐረብ)፤ መዝፈን መወዛወዝ፤ ማሸብሸብ
ማጋፈት መዝለል መፈንጨት፡፡ … ዘፋኒ፤ (ኒት፤ ንያን፤ ያት)፤ የሚዘፍን ዘፋኝ፤ ተወዛዋዥ፡፡ ዘፈን፤(ናት)፤ በቁሙ ዝላይ እስክታ፡፡”[2]
የደስታ ተክለ
ወልድ መዝገበ ቃላትም “ዘፈን”[3] የሚለውን፣ “ዘፈን፤ (ዘፊን ዘፈነ)፤ ቀነቀነ
አወረደ ግጥም
ገጠመ፣ አዜመ፣ አንጐራጐረ፣ ዘለለ፣ ተውረገረገ፡፡” አሁንም ዘፈነ፤ ተንቀጠቀጠ ተንዘፈዘፈ፡፡
ዘፋኝ(ኞች)፤ የዘፈነ የሚዘፍን፤ አውራጅ አንጐራጓሪ ዘፈን ወዳድ(መዝ.፹፯፥፯)” በማለት ሲያስቀምጡት፣ ገላ.5፥21 ላይ የተቀመጠውን
ዘፋኝነት የሚለውን ሃሳብ ደግሞ፣ “መጽሐፍ ግን መሶልሶል[4][ሶለሶለ - አንሶለሶለ፣ አዞር፣ አንቀዠቀዠ፣ አንቀለቀለ መንሶልሶል፣ መዞር፣ መንቀዥቀዥ] ይላል” በማለት ጥቅሱን ጠቅሰው አስቀምጠውታል፡፡
ሰርጸ፣ ሽምጥጥ አድርጎ “የመጽሐፍ ቅዱስ መተርጉማን ሌላ ስያሜ
ስላጡለት ዘፈን አሉ እንጂ ዘፈን መባል አይገባውም” የሚል ጽኑ አቋሙን ደጋግሞ አስተጋብቷል፡፡ ምናልባት ይህንን ሲል ሁሉን
አዋቂ ነገር ጠንቃቂ ወደመሆን የተጠጋ ሳይመስለው፤ እንደሆነ ሳያስብ አልቀረም፡፡ ነገር ግን የእርሱን ሃሳብ መተርጉማኑም ሆኑ
የቋንቋው ሊቃውንት ሲደግፉት ፈጽሞ አይታይም፡፡
እንዲያውም በሌላ ሥፍራም፦ “ … ዘፈን ሲባል በመሠረቱ ሃይለ ፍትወት
የመረዘው ሁሉ ነው፡፡ ወንድም ሆነ ሴት የፍቅሩን ስሜት የሚገልጥበት ግጥም ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ለክፉዎቹም ሆነ ለደግ
ባንዱ ላይ የተወረወረውን ግጥም ሌላው በሚገባ የመለሰ እንደሆነ
እነእገሌ ተዛፈኑ ይባላል፡፡”[5]
ተብሎ በግልጥ ተቀምጧል፡፡ ከዚህም የተነሣ የቋንቋው ተናጋሪዎችና ሊቃውንት ሁሉ ዘፈንን ሲያስቡ “እግዚአብሔርን ማክበሪያና
ማመስገኛ” እንዳልሆነ እሙንና ልንክደው የማንችለው ሐቅ ነው፡፡
የትኛውም ኢትዮጲያዊ እግዚአብሔርን
በዘፈን አመልከዋለሁ ብሎ እንደማያስብ እኔው ራሴ እንኳ አንድ እማኝ ነኝ፡፡ እነሰርጸ እንግዲህ ይህን ዘፈንን ለእግዚአብሔር የማይለውንና የሚቃረነውን
ማኅበረሰብ “በዘፈን ብናመልከውም ችግር የለውም!” የሚል ፈሊጥን ለማለማመድ የተነሱ ይመስላሉ፡፡ለዚህ ሃሳባቸው ግን ተላላ
ትውልድ ያጣሉ ብዬ አላስብም፡፡
የመጽሐፍ
ቅዱስ ማህበርና የሰርጸ ፍሬ ስብሐት ማኅበሩን ማሞገስ
ሰርጸ በተደጋጋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርን ጽሁፍ “ሲያንቆለጳጵስ”
ነበር፤ “ማንቆለጳጰሱን” ሲደጋግም ደግሞ በሰርጸና በማኅበሩ መልእክት መካከል ይህን ያህል ምን መተሳሰር አለ? እውነት
የማኅበሩ መልእክት ይህን ያህል ለሰርጸና መሰሎቹ ተስማሚ ነውን? ከምን የተነሣስ ሰርጸና የማኅበሩ መልእክት እንዲህ
“ተፋቀሩ”? ይህን ያህልስ ማኅበሩ ለሰርጸና ባልንጀሮቹ አንገቱን ሰብሯልን? የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡
አንድ ነገር ሁል ጊዜ ግልጥ ሊሆን
ይገባል፡፡ በዓለማውያንና በመንፈሳውያን መካከል ግልጥና የማያጥበረብር መስመር በደማቅ ቀለም የተሰመረና የተለያየ መሆኑ መታወቅ
አለበት፡፡ እኛ በዓለማውያን ፊት ሙትና የማንጠቅም ነን፤ (ገላ.6፥14)፤ ስለዚህ ከእነርሱ ምንም ሙገሳ፣ ውዳሴ፣ አድናቆትና
ከበሬታን ፈጽሞ አንጠብቅም፤ ብንጠብቅ እንኳ ፈጽሞ አናገኘውም፤ (ዮሐ.16፥20)፡፡ ዓለምም በእኛ ፊት የማትረባና ከንቱ ናት፤
በክፋትም እንደተያዘችና ለእግዚአብሔር ሃሳብና ለክርስቶስ ለሆነው ሁሉ ነገር ጠላትና ተቃዋሚ እንደሆነች እናውቃለን፤
(1ዮሐ.5፥19)፡፡
ስለዚህ ሰርጸ፣ በምንም ዓይነት መልኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበርን ማወደስ
ቢጀምር በማኅበሩ ዘንድ አንድ የተድበሰበሰ ነገር ወይም ሴራ በሚመስል “ሽፍንፍን” ሰርጸንና ባልንጀሮቹን “ደግፏል” ወይም
እነሰርጸ በተሳሳተ መንገድ “ሳይረዱ ተረዳን” ብለዋል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በግልጥ ቃል የኮሞስን
ትርጉም ከኃጢአትና ከሥጋ ፍሬዎች ተርታ መድቦ አስቀምጧል፡፡
ምናልባት ሰርጸ፣ ኮሞስ የሚለው ቃል፣ “ከተትረፈረፈ መጠጥና ምግብ ጋር የሚከናወን ስነ ምግባር የጎደለው
የአምልኮ ጭፈራ” የሚለው ትርጉም ትንሽ “ያስፈነጠዘው” ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ሰርጸ፣ “እኛ የተትረፈረፈ
መጠጥና ሥነ ምግባር የጐደለው
የአምልኮ ጭፈራ አናደርግም፤ ከዚህ ውጪ ሆነን መዝፈንና መጨፈር እንችላለን” በማለት ሊያሞኝ የፈለገ ይመስላል፡፡
እንግዲህ ከሰርጸ ፍሬ ስብሐት ጋር፣ ፈጽሞ የማንገናኘውና ለእግዚአብሔር ክብር
በማድላት ዘፈንን ኃጢአት የምንለው እዚህ ጋ ነው፡፡ እኛ አንድን ነገር ኃጢአት ነው ለማለት ሚዛናችን ቅዱስ መንፈስና የተገለጠው
ቅዱስ ቃሉ ነው፡፡ እንኳን ዘፈንና መልካም ነገር ሆኖ እግዚአብሔርን የማያከብር ማናቸውም ነገር እርሱ ኃጢአት ነው፡፡ ዘፈን ለአምልኮ
ተጨፈረም አልተጨፈረ፣ የተትረፈረፈ ምግብና መጠጥ ቀረበበትም አልቀረበበትም” በውስጡ የሚተላለፈው መልእክት ምንድር ነው? የሚለው ጥያቄ አንኳርና
መሠረታዊ ነው፡፡ በውስጡ የሚተላለፈው መልእክት ጠማማና ኃጢአት ከሆነ “ሥነ ምግባር” ባለው መልክ ቢቀርብም እንኳ ኃጢአትነቱን አያስቀረውም፡፡
የኢትዮጲያ
መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዘፈንን አስመልክቶ በጻፈው ደብዳቤው በገጽ 4 እና 5 እንዲህ ይላል፤
“በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለመዝሙር፥ ዘፈንና ሰለጭፈራ የተጠቀሱበት
ስፍራዎችና ፍቺአቸው፤
መጽሐፍ ቅዱስ መጀመርያ የተጻፈባቸው ቋንቋዎች ዕብራይስጥና ግሪክ
እንደመሆናቸው፥ በቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉም ጊዜ ለሚነሱ ጥያቄዎች
ትክክለኛ መልስ ለመስጠት የሚቻለው በምንጮቹ ቋንቋዎች የተላለፈውንመልእክት በመመርመር ነው። ስለሆነም በአዲስ ኪዳን ውስጥከመዝሙር፥
ከዘፈን ወይም ከጭፈራ ጋር የተያያዙ ሀሳቦች የተጠቀሱባቸውን ክፍሎች የግሪኩን መጽሐፍ መሰረት በማድረግ እንመለከታለን። ቃላቱ የሚገኙባቸው
ክፍሎችና አጠቃላይ ፍቺአቸው የሚከተሉት ናቸው።
1)
ፕሳልሞስ
(ψαλμός)(ስም)፦ቃሉ“የውዳሴ
መዝሙር” የሚል ፍቺ ሲኖረው የሚገኝባቸው ሥፍራዎችኤፌሶን 5፡19፤ ቆላስይስ 3፡16 ወዘተ ላይ ነው።
2)
ኦዴ (ᾠδή)(ስም)፦ቃሉ“መንፈሳዊ ዜማ” የሚል ፍቺ ያዘለ ሲሆን የሚገኝባቸው ቦታዎች ኤፌሶን
5፡19፤ ቆላይስስ 3፡16፤ ራዕይ 5፡9፤ 15፡3 ወዘተ ላይ ነው።
3)
ኮሞስ
κῶμος(ስም)፦ቃሉ
“ከተትረፈረፈ መጠጥና ምግብ ጋር የሚከናወን ስነ ምግባር የጎደለው የአምልኮ ጭፈራ” የሚል ፍቺ የያዘ ሲሆን ቃሉ የሚገኝባቸው ስፍራዎች
ሮሜ 13፡13፥ ገላትያ 5፡21፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4፡3 ላይ ነው።
4)
ኮሮስ
(χορός)
(ስም)፦ቃሉ “የሕብረትውዝዋዜ” የሚል ፍቺ ያዘለ ሲሆን የሚገኝበት ሥፍራ ሉቃስ 15፡25፥ ላይ ብቻ ነው።
5)
ኦርኬኦማይ
(ὀρχέομαι)
(ግሥ)፦ቃሉ “መጨፈር፥ መወዛወዝ” የሚል ፍቺ የያዘ ሲሆን የሚገኝባቸው ሥፍራዎች ማቴዎስ 11፡17፤ 14፡6፤ ማርቆስ 6፡22፤
ሉቃስ 7፡32 ወዘተ ላይ ነው።
ከላይ እንደምንመለከተው በግሪክ አዲስ ኪዳን ከዘፈን ወይም ጭፈራ ጋር የተያያዘ መልእክት ያላቸው በተለይ ከተራ ቁጥር
3-5 የተጠቀሱት ቃላት ናቸው፤ እነኝህ ቃላት የሚገኙባቸው ክፍሎች የሚከተሉት ሲሆኑ በሁለቱ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ የተተረጎሙበት
መንገድ እንደሚከተለው ነው።
የግሪኩ ቃል የ1954 ዓ/ም ትርጉም የ1997 ዓ/ም ትርጉም
ኮሞስ κῶμος ሮሜ 13፡13፥ በዘፈንና ቅጥ
ባጣ ፈንጠዝያ
ገላትያ 5፡21፥ ዘፋኝነት ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያ
1ኛ
ጴጥሮስ 4፡3፥ በዘፈንም ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ
ኮሮስ (χορός) ሉቃስ
15፡25፥ የዘፈን ድምፅ የጭፈራ
ድምፅ
ኦርኬኦማይ ማቴዎስ 14፡6፥ ዘፈነች እየጨፈረች
(ὀρχέομαι)
ሉቃስ 7፡32፥ አልዘፈናችሁም አልጨፈራችሁም
ከዚህ ዝርዝር እንደምንረዳው የ1954 ዓ/ም መጽሐፍ ቅዱስ፥ኮሞስ κῶμος፥ ኮሮስ (χορός)፥ እና ኦርኬኦማይ
(ὀρχέομαι) የተባሉት ሦስት የግሪክ ቃላት በአንድ አይነት መንገድ
ማለትም “ዘፈን”ወይም ከዚሁ ቃል ጋር በሚዛመድ ቃል ተርጉሟቸዋል። ይህ የትርጉም አካሄድ በማኅበረሰቡ ውስጥ የማይታወቅ ነገርን
አጠቃላይ በሆነ ቃል የመተርጎም ዘዴን የተከተለ መሆኑን ያሳያል። ቀደም ሲል “ሥጋ” የሚለው ቃል በተለያዩ አውዶች የተለያዩ ፍቺዎች
ቢኖሩትም በ1954 ዓ/ም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሥጋ” የሚለውን ቃል እንዳለ ተወስዶ እንደተተረጎመ ሁሉ፥የተለያዩና ሆኖም በተወሰነ
ደረጃም ቢሆንተዛማጅ ፍቺ ያላቸውን እነዚህም ሦስት ቃላት “ዘፈን” በሚለው አንድ ቃል መተርጎማቸውን እንረዳለን። ስለሆነም ይህን
መጽሐፍ ቅዱስ ስንጠቀም የ“ሥጋ”ን ትክክለኛ ፍቺ አውዱን በግል በማጥናት
ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ መምህር መረዳት እንደሚያስፈልግ ሁሉ፥ “ዘፈን” የሚለውንም ቃል ትክክለኛ ፍቺ አውዱን ወይም የግሪኩን ምንባብ
በመመርመር መገንዘብ የሚያስፈልግ ይሆናል። ምክንያቱም ከዝሙት፥ ጣዖትን ከማምለክ፥ ከቅንዓት፥ ከአድመኛነት፥ ከመለያየት፥ከመናፍቅነት፥ ከምቀኝነት፥ ከመግደል፥ ወዘተ ጋር ተሰልፎ የቀረበ “ዘፈን” እና በጠፋው ልጅ
ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው “ዘፈን” አንድ አይነት ፍቺ ወይም መልእክት ሊኖራቸው እንደማይችል መገንዘብ
ስለማያዳግት ነው።
በሌላ ወገን ቀለል ባለ አማርኛ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ የተከተለው የትርጉም
ስልት መልእክት ተኮር በመሆኑ የቃላትን አውዳዊ ትርጉም በግልጽ ለማውጣት ይጥራል። በዚህም መሰረት የ1954 ዓ/ም እትም እሳቤው
እንግዳ የሆነን አንድ መልእክት፥ኮሞስን (κῶμος) ከሌሎቹ ጋር
ባለው የተወሰነ የፍቺ ዝምድና ምክንያት በተመሳሳይ አንድ ቃል የተረጎመውን፥ ቀለል ያለው የአማርኛ ትርጉም በሀረግ ደረጃ በማብራራት
መልእክቱን ያስተላልፋል፤ በተወሰነ ደረጃም በሦስቱ የግሪክ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት ለማሳየት ይሞክራል።
በእንግሊዘኛ ቋንቋ RSV፥ NIV፥ CEV፥ ወዘተ በመባል የሚታወቁ
አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በአቀራረባቸው፥ በአተረጓጎም ስልታቸው ወዘተ እንደሚለያዩት ሁሉ ቀለል ባለ አማርኛ የተዘጋጀው መጽሐፍ
ቅዱስ እና የቀድሞው የ1954 ዓ/ም መጽሐፍ ቅዱስ በቋንቋ አጠቃቀማቸው፥ በሚከተሉት የትርጉም ስልት፥ ታሳቢ በሆኑት ተጠቃሚዎች
እና ለዕብራይስጡና ለግሪኩ ቋንቋዎች ባላቸው የቃላት ቀጥተኛ ቀረቤታይለያያሉ፤ ሆኖም ሁለቱም ትርጉሞች የታለመላቸውን አገልግሎት
በተገቢው መንገድ እየሰጡ ይገኛሉ። ስለሆነም የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር “ዘፈን” በሚለው የቃል አጠቃቀም ምክንያት የተፈጠረው
ችግር፥የቃሉን አውዳዊ ንባብ ካለመረዳት የመነጨ እንደሆነ በማመን፥ ምእመናን በየአብያተ ክርስቲያኖቻቸው በሚያገለግሉ የመጽሐፍ ቅዱስ
መምህሮቻቸው አማካይነት ትክክለኛ የቃሉን አውዳዊ መልእክት በመገንዘብ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እንዲያንጹ ያስፈልጋል እንላለን፡፡“
ሰርጸ፣ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ዘፈንን አስመልክቶ የኢትዮጲያ
መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የጻፈውን በመጥቀስ ደጋግሞ “በማንቆለጳጰስ”፣ ማኅበሩ የዘፈንን ትርጉም “ማስተዋልና ማጤን” እንደሚገባ
በጻፉት ደብዳቤ ማሳወቃቸውን ደጋግሞ ተናግሮታል፡፡ ነገር ግን ማኅበሩ የጻፈውን ፈጽሞ በትክክል ያስተዋለው አይመስልም፡፡
የትርጉም ይዘትንም በተመለከተ ማኅበሩ በ1954 ዓ.ም ዕትም
ኮሞስን፣ “መጀመርያ
ከተጻፈባቸው ከዕብራይስጥ እና ከግሪክ ቋንቋዎች ጋር በማስተያየት የተረጎመ ሲሆን ትርጉሙ በይበልጥ “ቃል በቃል” (Literal)
ተብሎ የሚታወቀውን የትርጉም ስልት የተከተለ ነው። መጽሐፍ ቅዱሱ በቃላት አጠቃቀሙ፥ በፈሊጣዊ አነጋገሩ እና በብዙ ቦታዎችም በዐረፍተ
ነገር አወቃቀሩ የምንጩን ቋንቋ (የዕብራይስጡን ወይም የግሪኩን) ስርዐት ያንጸባርቃል። ትርጉሙ ለምንጭ ቋንቋዎቹ እጅግ የቀረበ
በመሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋዎችን ባሕርይና የአይሁዳውያንን ባህል ለማወቅ እጅግ የሚጠቅም” መሆኑን
በመግለጥ ትርጉሙን ዘፈን፣ ዘፋኝነት ብሎ
ሲያስቀምጥ፣ የ1997 ዓ.ም ትርጉም ደግሞ፣ “የተከተለው የትርጉም ስልት መልእክት ተኮር ተብሎ የሚታወቀውን በመሆኑ
ቃላትን በእኩያ የተቀባይ ቃላት ከመተርጎም ይልቅ መልእክቱን ግልጽ በሚያደርጉ የተቀባይ ቃላት ወይም ሐረግ ተመልሰዋል፤ እንግዳ
የሆኑ ፈሊጣዊ አነጋገሮች ትርጉማቸውን በቀላሉ ለመረዳት በሚያስችል መንገድ ተፈተው ተተርጉመዋል፤ ግር የሚሉ የዐረፍተ ነገር አወቃቀሮች
የአማርኛ ሰዋሰው ሕግን በተከተሉ ቀላል አገባብ ባላቸውና አጠር ባሉ ዐረፍተ ነገሮች እንዲተረጎሙ” መደረጉን
በመግለጥ፣ ትርጉሙን ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያ ወይም ጭፈራ ብሎ ገልጦታል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ ሰርጸ ግን ይክዳል፡፡ ደግሜ እላለሁ፣ እውነታው ግን ኮሞስ ለሚለው ቃል ዘፈንን
ሲያስገቡ ሌላ ቃል ፍለጋ በመንከራተት “እንዲያው” ያስገቡት አይደለም፡፡ በዘፈንና ዘፋኝነት፣ በጭፈራና ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ
መካከል ቀጥተኛ የሆነ የሃሳብ ተዛምዶ አለ፡፡ ሁሉም ሃረጋት ለኃቲአት በተጠቀሱት በተለይ [ሮሜ.13፥13 ፤ ገላ.5፥19 ፤
1ጴጥ.4፥3] ውስጥ እግዚአብሔርን ፈጽሞ አያከብሩም፤ ወደቅድስናም ፈጽሞ አይመሩምና፡፡
ዘፈንን በተመለከተ የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ትልቁ ስህተት
በኢትዮጲያ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን የትርጉም ሥራ በግንባር ቀደምትነት የሚሠራ ነው፡፡ ለሁሉም
አብያተ ክርስቲያናት በሚል መልኩም በተለያየ የትርጉም ሥራ ላይ ታላቅ የሰማያዊ መንግሥት አደራውንም ሲወጣ እየታየ ነው፡፡ እስከአሁንም
በኢትዮጲያ ውስጥ ሕዝቡ በራሱ ቋንቋ ቅዱሱን ቃል እንዲያነበው፣ “በዘጠኝ
ቋንቋዎች (አማርኛ፥ ኦሮምኛ፥ ትግሪኛ፥ ወላይትኛ፥ ጉራግኛ፥ አፋር (በተለያዩ ቅጾች የተዘጋጀ)፥ አኙዋክ፥ ሲዳምኛ፥ ማሌ) ሙሉ
መጽሐፍ ቅዱስ ተርጉሟል”፡፡
እንዲህ ያለ ሥራ ለመንፈሳዊ መነቃቃትና ለእግዚአብሔር የሥጋ ልብ ያለውን
አዲስ ትውለድን የማዘጋጀትና የማምጣት ሥራን ለመሥራት በግንባር ቀደምትነቱ የሚጠቅስ ምስጉን ሥራ ነው፡፡ ዳሩ በክፍል አንድ ጽሁፌ፣ “የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተረጎመችውና በስሟ ያዘጋጀችው
መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በገላ.5፥21 እና በ1ጴጥ.4፥3 ላይ ያሉትን ዘፋኝነትን ጨርሳ አውጥታቸዋለች፡፡ ይህ ያደረጉበት ምክንያታቸው ግልጥ አይደለም፤” ብዬ
መጻፌ የሚታወስ ነው፤ እናም የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ደግሞ የዚያ መጽሐፍ ቅዱስ ዋና አሳታሚ ነበር፤ በሕትመቱም ወቅት
ዘፈን የሚለው ቃል በግልጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲወጣ ተባብሯል፤ ዘፈን የሚለውንም ቃል ሙሉ ለሙሉ በማውጣት በስካር ብቻ ተክቶታል፤
ለንጽጽርም እንዲመች ከዚህ በታች ሁለቱንም ትርጉሞች አስቀምጫለሁ፤
የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተ ክርስቲያን የ2000 ዓ.ም ትርጉም
|
የ1954
ዓ.ም ትርጉም
|
“የሥጋም ሥራው ይታወቃል፤ እርሱም ዝሙት፥ ርኩሰት … መጋደል፥ ስካር ይህን
የመሰለ ሁሉ ነው፤” (ገላ.5፥19)
|
የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ … መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥
ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው፤ (ገላ.5፥19)
|
“ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋው ከሕይወቱ ዘመን የቀረውን፥ በሰው ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር
ፈቃድ እንዲፈጸም ነው እንጂ፡፡ የአሕዛብን ፈቃድ፦ ዝሙትንና ምኞትን፥ ስካርንና ወድቆ ማደርን፥ ያለልክ መጠጣትና ጣዖት ማምለክን
ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል” (1ጴጥ.4፥2-3)
|
“የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት
ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” (1ጴጥ.4፥2-3)
|
ማኅበሩ ይህን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ብዙ የሐረጋትና የሃሳብ ስህተቶችንም ፈጽሟል፡፡ ይህ ግን መሆን ያልነበረበት አሳዛኝ
ገጽታ ነው፡፡ ምንም እንኳ “የቤተ ክርስቲያኒቱ አንዳንድ አካላት” ይህንን ማድረግ ቢወድዱ፣ ማኅበሩ በእንዲህ ያለ ጉዳይ ፈጽሞ
መተባበር አልነበረበትም፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድና ሃሳብ ግን አንድና ግልጽ
ነው፤ እርሱም ቅድስና፡፡ ያለቅድስና ፈጽሞ እግዚአብሔርን ማስደሰት አይቻልም፤ ቅድስናን ከሚያሳድፉ ነገሮች አንዱ ደግሞ ኮሞሳዊ
ዘፈንና ዘፋኝነት ስለመሆኑ ምንም አያከራክረንም፡፡ ጌታችን መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን፣ የልብና የሕሊናን ቅድስናን ያብዛልን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …
ጌታ ባንተ አድሮ ብዙ አስተምሮናል ወንድሜ፡፡ ክብር ይግባው አምላካችን፤ በርታ በርታ በርታ
ReplyDelete