Thursday 8 June 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥር)

Please read in PDF
5.  ውነተኛ ወታደር በማናቸውም የራሱ እቅድና ዝግጅት ቢኖረውም ዘወትር ግን ወደየትኛውም አቅጣጫ መሄድና ማናቸውንም ሥራዎች ለመሥራት ዝግጁ ነው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያንም የራሱ የሆኑና በግሉ የሚሠራቸው ብዙ መልካም ነገሮች ሊኖሩት ይችላሉ፤ ነገር ግን በክርስትና ሕይወት ጉዞው ቀዳሚውና ዋናው የሚኖርለት የክርስቶስ ነገር ሊሆን ይገባዋል፡፡
      ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ላነሰ ኑሮ ልንኖር አልተጠራንም፡፡ ክርስቲያን ከእርሱ ላነሰ ኑሮ የሚኖር ከሆነ ከሁሉ ይልቅ ምስኪን ነው፡፡ የክርስቶስ የሆኑቱ ታማኞቹ ደቀ መዛሙርት፣ “በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮች” (ሐዋ.1፥8) የሆኑት፣ ለየትኛውም ለጌታችን ኢየሱስ ሥራ ዝግጁና በማናቸውም አቅጣጫ ቢሄዱ በደስታ በመታዘዝ ነበር፡፡ ለየትኛውም አገልግሎትና ለኢየሱስ ጌታችን ሥራ የጨከነና የበረታ ልብና መንፈስ ነበራቸው፡፡

    ምንም ነገር ከኢየሱስ ጌታችን ሊበልጥብን አይገባም፡፡ ሥራችን፣ ትጋታችን፣ ዒላማችን፣ … በማናቸውም የሕይወት ጉዞ ውስጥ እርሱ ብቻ ቀዳሚ ሊሆነን ይገባል፡፡ አንዳንዶቻችን ከኢየሱስ ጌታችን ቃሉ ይልቅ የሰባኪ፣ የቄስ፣ የመጋቢ፣ የዘማሪ፣ የማኅበራችን፣ የሰበካ ጉባኤያችን፣ … ቃል ይበልጥብናል፡፡ የምናደንቀው ሰባኪ፣ ዘማሪ፣ ቄስ … ወይም ማኅበራችን ይወስን ወይም ይናገር እንጂ፣ ምንም ከማድረግ የማንመለስ “የሥጋ ለባሽ ደቀ መዛሙርት” የሆንን ብዙ አለን፡፡ ጌታ ግን የእርሱ ብቻ እንድንሆንና ለእርሱ ሥራ ብቻ የቀናን የጽድቅ ወታደሮች እንድንሆን ይሻል፡፡
    በአንድ ወቅት በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን፣ “እያንዳንዳችው፦ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፥ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፥ እኔስ የክርስቶስ ነኝ” (1ቆሮ.1፥12) በማለት ተከፋፍለው ነበር፡፡ ምናልባት ይህን የቅዱስ ቃሉን ክፍል የምናነብ ብዙ ክርስቲያኖች “እኛ ይህን ልናደርግ እንደማንችል” አፋችንን ሞልተን እንናገር ይሆናል፤ ነገር ግን በልባችን ሾመን ያከበርናቸው ብዙ ሰባኪ፣ ቄስ፣ መጋቢ፣ ዘማሪና … አገልጋይ አለን፡፡ ለዚህም ይመስላል በዘመናችን ከመቼውም ጊዜ በላይ መከፋፈል በ“ክርስቲያኑ” ማኅበረሰብ ሰልጥኖና ገኖ የሚታየው፡፡ ከኢየሱስ ቃሎች ይልቅ የምንታዘዝለት የየራሳችን ነገር በዙርያችን ተከማችቷል፡፡
     እውነት ሁላችን አንድ የክርስቶስ አጀንዳ ካለን ምን ሆን የከፋፈለን? እውን ሁላችን ከአንዱ ከሆንን ለምንድር ነው መቀባበል የተሳነን? በጎጥ፣ በጎሳ፣ በማኅበር፣ በትውልድ ቀዬና አገር፣ በደብርና አጥቢ …. አገልግሎት በሚል ፈሊጥ የተከፋፈልነው እውነት ስለክርስቶስ ነውን? በማናቸውም  መልካም ነገሮች ውስጥ ብናልፍ እንድንኖር የታዘዝነው ለክርስቶስና ለቃሉ ብቻ ነበር፤ ነገር ግን የእኔ የምንለውን ነገር በማስበለጣችንና በማግነናችን ከመንፈሳዊ ወታደርነት ወርደን የፍጡር ሎሌዎች ሆነናል፡፡
6.    ሞናዊ ትግል በውትድርና ዓለም የለም፤ ትግሉ የማያቋርጥና የዘወትር ነው፡፡ በክርስቶስ ያመንን ሁላችን ሳናቋርጥ እስከሞት ድረስ(2ጢሞ.4፥7)፣ ዘወትር መንፈስና ሥጋ የተባሉ እርስ በእርስ የሚቀዋወሙ ተዋጊዎች በውስጣችን አሉብን፤ (ገላ.5፥17)፡፡ ስለዚህም በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ አለን ማለት ነው፤ (ሮሜ.8፥13)፡፡ ጌታችን ኢየሱስም የድል መንሻው መንገድ መስቀሉን ዕለት ዕለት መሸከም እንደሆነ ነግሮናል፡፡
    መሆን የማንችለው ልጅ መሆንን ነው፤ ልጆች እንሆን ዘንድ እንዲሁ ያለዋጋ ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ አደረገልን፤ ልጅ ከሆንን በኋላ መዋጋትን ግን ለእኛ ተወው፡፡ በእስራኤል ልጆች ታሪክ ለትምህርትና ለተግሳጽ ይሆነን ዘንድ የተጻፈ ብዙ ነገር አለ፡፡ ከግብጽ ምድር ከፈርዖን እጅ ነጻ ሲያወጣቸውና ባሕርን ከፍሎ ሲያሻግራቸው በጸናች እጅ በተዘረጋች ክንድ ነበር፡፡ ታላቁን በረሃ አቋርጠው ወደርስታቸው በቀረቡ ጊዜ ግን፣  ከመና ይልቅ በእጃቸው እየሠሩ እንዲመገቡ፣ እነርሱ ራሳቸው ታላላቆቹን የአሕዛብ መንግሥታትን ተዋግተው ድል በመንሣት እንዲወርሱ አዘዛቸው፤ (ኢያ.5፥11-12) የኢያሱ መጽሐፍ በዋናነት የሚተርከውም ተዋግቶ ስለመውረስ ነው፡፡ እነርሱም ተዋግተው የወረሱ መሆናቸውን መጽሐፉ በሚገባ ይተርክልናል፡፡
     ከኃጢአት መላቀቅ[ነጻ መውጣት] በራሳችን አይቻለንም፡፡ በራሳችን መላቀቅ የማይቻለንን እርሱ ቤዛችን ሆኖ አላቀቀን፤ ነጻም አወጣን፡፡ ቀሪውን ግን ከተሸነፈው ጠላት ጋር እንድንዋጋ ጌታችን አዘዘን፡፡ ይህም ከወታደራዊ አደራረግ ተመሳስሎ ቀርቧል፡፡ በክርስትና መዋጋት በሃይማኖት ጸንቶ ፍጹም መጋደልን ያመለክታል፡፡
      ይህ ደግሞ ወቅታዊና ሰሞናዊ አይደለም፤ የጌታችን ኢየሱስ ወንድምና ባርያ የነበረው ቅዱስ ይሁዳ፣ “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” (ቁ.3) በማለት ይናገራል፡፡ መጋደል ግዴታ ብቻ ሳይሆን ታማኝ ክርስቲያኖች በዘመናቸው ሁሉ እምነታቸውን ለመጠበቅ ሊያደርጉት የሚገባቸውን ውጊያ ጭምር የሚያሳይ ነው፡፡
      ቅዱስ ይሁዳ፣ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ” ሲልም፣ በክርስቶስ ጌታችን ወደዘላለም ሕይወት የወሰደንና የሰጠን ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ የሰጠን ብቻም አይደለም፣ ደግሞም የሰጠንን የዘላለም ሕይወትን በፍቅሩ ራሳችንን በመጋደል እንድንጠብቅ የሚያስችለንን አቅምም ይሰጠናል፡፡ ከሐሰተኞች መምህራን አንዱ መከላከያው መንገድ ራስን በእግዚአብሔር ፍቅር መጠበቅ ነው፡፡ በሌላ ንግግር ሐሰት በሚፋንንባት ዓለም ላይ ተዘልለን መቀመጥ አልተባለልንም፡፡
    መጋደል በውስጡ መታገልን፣ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መግባትን አመልካች ነው፡፡ በማያቋርጠው ውጊያ ውስጥ ሳለን ማናቸውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁዎች መሆን አለብን፡፡ ምናልባትም እጅግ አስጨናቂ ነገር ስለወንጌል ጉዳይ ቢገጥመን፣ እስከሰማዕትነት ዋጋ ለመክፈል ዝግጁዎች መሆን ይገባናል፡፡ “በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ፤” (ፊል.1፥27) እንዲል፣ ወንጌል ለሰው ሁሉ እንዲደርስ የተገባን ሆነን ዘወትር ልንገኝ ይገባናል፡፡
     ዘወትር የተገባን ሆነን መገኘታችን ደግሞ፣ ለውጊያው ዝግጁዎች መሆናችንን ዋና ምስክር ነው፡፡  ደግሞም ልንወርሳት የተባለልን የጌታ መንግሥት የሰነፎች መናኸርያ አይደለችም፤ የትጉሃን እንጂ፣ እናም የክርስቶስ የሆናችሁ ሁላችሁ ሆይ! ተዋጉና ውረሱ እንጂ ተዘልላችሁ አትቀመጡ፡፡

ጌታ መንፈስ ቅዱስ በኃይሉ ብርታት ያበርታን፤ አሜን፡፡

ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment