Sunday, 11 June 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ አንድ)

Please read in PDf
የምንዋጋው ከማን ጋር ነው?
    በአጭር ቃል፣ የየራሳችንን ሰባኪና ማኅበር፣ ዘማሪና መጋቢ፣ የሐሰት አጥማቂዎችን፣ የነቢያትና “መፍትሔ አምጪ ነን” ባይ የሆኑ የመጋብያን ትንቢተኞችን  … ቃል ከኢየሱስ ጌታችን ቃል ይልቅ በማድመጥና በመከተል ስተናል፡፡ ልክ እንዲሁ ከማን ጋር እንደምንዋጋ አለማወቃችን ከደካማው ፍጡር ጋር በመታገል ዘመናችንን እንድንጨርሰው አድርጐናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ከማን ጋር እንደምንዋጋ፥ “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ፤” (ኤፌ.6፥12) በማለት ገልጦታል፡፡
    የምንዋጋው ከሥጋና ከደም ጋር አይደለም፤ ደረጃቸውና ሥልጣናቸው ከታወቀ አለቆች፣ ሥልጣናቸውን ለዓላማቸው በትክክል ከሚያውሉ ሥልጣናት፣ ዓለምንና መላዋን የፈጠረውን ጌታ በመቃወም፣ በመጥላት፣ በመሳደብ… ይህንን ዓለም በቁጥጥራቸው ሥር ካዋሉ ከጨለማ ዓለም ገዦችና መኖርያቸውንም በሰማያዊ ሥፍራ “ካደረጉ” ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው፡፡
    ትግሉና ውጊያው ተዋጊውን ወዲያው በቁጥጥር ሥር ሊያውል እንደሚያስብ ታጋይ በቀላሉ የሚጠናቀቅ ቀላል አይደለም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የውጊያውን ሥፍራ በሰማያዊ ሥፍራ የማድረጉን ያህል፥ የውጊያውን የትየለሌት እስከሰማያት ድረስ መድረሱን ያሳያል፡፡ ስለዚህ ከደካማው ሥጋ ለባሽ ጋር አንዋጋም፤ ነገር ግን ለደካማው ሥጋ ለባሽ ፍጡር ራርተን ዋናውንና ተንኮለኛውን ጠላት በማወቅ ውጊያችንን ልንዋጋ ይገባናል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ቅዱስ ጴጥሮስ የሞቱን ነገር በተቃወመ ጊዜ፥ “ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው፤” (ማቴ.16፥23)፡፡ ጌታ ኢየሱስ “ወደ ኋላዬ ሂድ” ያለው፥ ከኋላው ይከተለው የነበረውን ጴጥሮስን ሳይሆን፥ የበጐ ነገር ጠላት የሆነውን ዲያብሎስን ነው፡፡
      በሩጫውም፣ በአገልጋይነቱም በወታደርነቱም ዘመናችን ዋና ጠላቶቻችን ሥጋን የለበሰው ፍጡር ሰው አይደለም፡፡ ልንዋጋቸውና ልንታገሳቸው የማይገቡን ዋና ጠላቶቻችን፦
1.     ለም፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ዓለም የሚለው ቃል ቢያንስ ሦስት የተለያዩ ፍችዎችን ይዟል፤
1.1.  ግዑዙ ዓለም፦ ይህንን ቄስ ኮሊን ማንሰል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላቸው፣ “... ቃሉ ጠቅላላ ፍጥረትን(ዮሐ.1፥10)...” ሊያመለክት እንደሚችል ይገልጣሉ፡፡[1] ማለትም፣ “ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ” (ሐዋ.17፥24) ሲልም እግዚአብሔር የፈጠረውን መላውን ዓለም የሚያመለክት ነው፡፡
1.2. ሁለተኛው ደግሞ ከላይኛው ሃሳብ ጋር የተያያዘ ሆኖ፣ “... ጠቅላላ የዓለምን ሕዝብ (ዮሐ.16፥21)፣ አይሁድንና አሕዛብን (ዮሐ.4፥42)” ማለትም፣ በየራሱ ግን ይህን ሰብዓዊው ዓለም ወይም የሰው ልጅ ራሱ ዓለም ይባላል፡፡ “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐ.3፥16) በሚለው ቃል ውስጥ የተጠቀሰው ዓለም፣ የሰውን ልጅ የሚወክል ነው፡፡
1.3. ሦስተኛውና ከርእሳችን ጋር የሚዛመደው ትርጉም ግን ይህ ነው፤ እርሱም “... ክርስቶስን የማይቀበሉትን ሁሉ (ዮሐ.17፥9)፣ ወይም እግዚአብሔር የማይከብርበት ኅብረተሰብ (ዮሐ.3፥19) የሚያመለክት ነው፡፡ የዓለም ሰው ኃጢአትን ይወዳል፤ (ዮሐ.3፥19) በሰይጣን እጅ[ቁጥጥር] ነው፤ (ዮሐ.14፥30)፣ ክርስቶስንና የእርሱ የሆኑትን ሁሉ ተከታዮች ይጠላል፤ (ዮሐ.15፥18)፡፡”
   በአጠቃላይ በዚህኛው ትርጉም ዓለም ማለት፣ በግሪኩ “ኮስሞስ” ተብሎ የተጠራው ሲሆን፣ ይኸውም በጊዜያዊነት በምንኖርባት ዓለም ላይ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤን፣ መልካሙን የእግዚአብሔርን ሥራ ለመቃወም ተሰናድቶ፣ ተደራጅቶ ያለውን የዓለሙን መዋቅርና አሠራር ሁሉ ነው፡፡ በተለይም በእግዚአብሔር ፊት የተጠላውን ክፋትና ዓመጻን ባደፈ ኅሊና የሚፈጽመውን መንፈስ፣ የክርስቶስን ጌትነት ባለመቀበልና በጌትነቱም በመዘበት ከእርሱ ግዛት ውጪ ያለውን ዓለም፣ ቅዱስ ደሙን መንፈሱን የሚያክፋፋውን፣ በጠቅላላው እግዚአብሔርንና ዓላማውን ሁሉ ለመቃወም የሚሠራውን ማናቸውም ሥርዐት በዚህ ሥር ሊጠቃለል ይችላል፡፡
     ይህንን እውነታ ለማጉላትም በዓለም ያሉና የሰይጣንን አሠራር በግልጥ የሚያስኬዱ ሁሉ ቅዱሱን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማሳትና ከሥነ ምግባር በታች ለመጣል ፍልስፍናን፣ ኪነ ጥበብን፣ ሙዚቃንና ዘፈንን፣ ባህልን፣ ትምህርትን፣ ሳይንስን፣ መዝናኛን፣ ሃይማኖትን፣ ድረ ገጻትን፣ የመድኃኒትን ቅመማና ሌሎችን ብዙና ውስብስብ መንገዶችን ሊጠቀሙና ሊሠሩበት ይችላሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ድረ ገጽን በምሳሌነት ብናነሳ፦ ጎግል ድረ ገጽ ላይ ብቻ ከ3.5 ሚሊየን በላይ የዝሙት ቪዲዮዎችን የሚለቁ ቻናሎች እንዳሉና በየቀኑም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ጣቢያዎች እንደሚከፈቱ ይናገራል፡፡ በዚህም ደግሞ እጅግ ተጠቂዎቹ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ጨቅላ ወጣቶች መሆናቸውንም ጨምሮ ይናገራል፡፡ ይህ እንግዲህ የዝሙቱ ብቻ ነው፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ በጥንቆላ አሠራር (Horoscope)፣ ከአሸባሪዎች ጋር መሻረክ፣ ከግብረ ሰዶማውን ጎራ መሰለፍ፣ ዕፅ አዘዋዋሪዎችና ሌሎችንም ጥፋቶች ወዳልታወቁት ዓለማት በአጭር ቅጽበታት የሚተላለፈውን ደግሞ ስናየውና ስናስተውለው ዓለሙ ምን ያህል በክፋት አሠራር እንደተተበተበ እናያለን፡፡
     በተራ ቁጥር አንድ ባለው ትርጉም ሥር ባለው ዓለም፣… ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን“ (1ጢሞ.6፥17) እንዲል፣ ፍጥረትን መጋቢው እግዚአብሔር ቁሳዊውን ዓለም እንደሰትበት ዘንድ ለጥቅማችን ሰጥቶናል፡፡ ልናደንቀውም ይገባናል፡፡ በሁለተኛውም ረገድ ባለው ትርጉም ውስጥ ያሉትንም ሁሉ[ጠላቶቻችንን፣ የሚረግሙንን፣ የሚያሳድዱንን ጭምር] እንድንወድድ፣ እንድንመርቅ፣ እንድንጸልይላቸው፣ እንድናከብራቸውም፤ እንዳንጠላቸውም ታዘናል፤ (ማቴ.5፥43-48)፡፡  
    ነገር ግን እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ቅዱሱ እግዚአብሔር ከሚጠላውና ከተሳሰተ ፍቅር እንድንርቅ አስጠንቅቆናል፡፡ “ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም” (ዮሐ.2፥16) የሚለው ቃል፣ ዓለምን መውደድ ከእግዚአብሔር ፍቅር ጋር መቃረን እንደሆነ በግልጥ ያሳያል፡፡ በሌላ ሥፍራም እውነተኛ አማኞች “ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ይርቁ ዘንድ … በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ የታመኑ” መሆናቸው ተነግሯል፤ (1ጴጥ.2፥11 ፤ ዕብ.11፥13)፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሥጋዊ ምኞት ነፍስን የሚዋጋ ክፉ መሆኑን ሲናገር፣ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ዓለሙ የታመኑትን የጌታን ልጆች ለማጥመድ የሚጠቀምበት ዋናና አንዱ ወጥመድ መሆኑን፣ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት” (1ዮሐ.2፥16) በማለት ተናግሮታል፡፡ ስለዚህም ከክፉ ምኞች፣ ነፍስን ከሚዋጋ ዓለማዊነት አጥብቀን መራቅ ይገባናል ማለት ነው፡፡
     እውነተኛ ክርስቲያኖች ያለክርክር ኃቲአትን የኑሮ ዘይቤ ካደረገው ዓለም መውጣት አለባቸው (ዮሐ.15፥19)፣ እንዲህ ያለውንም ዓለም መምሰል የለባቸውም (ሮሜ.12፥2)፣ ዓለምን ድል በነሣው ጌታ ተመክተው ድል መንሳትም አለባቸው (ዮሐ.16፥33 ፤ 1ዮሐ.5፥4)፣ የዓለምን ክፋት ሁሉ መካድና መጥላትም አለባቸው (ቲቶ.2፥12 ፤ ዕብ.1፥9)፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት”(ገላ.6፥14) ብሎ እንደተናገረው፣ ኃጢአትን በዘይቤነት ከሚያዘወትረው ዓለም ሁለንተናችን ሙትና የማይጠቅም መሆኑንን ማሳየት አለብን፡፡
     ከዓለም ጋር ያለንን ግንኙነት በማለሳለስ ሳይሆን በጦርነት ሥፍራ እንዳለ ጦረኛ ወይም ተዋጊ አጽንተን መቃወም ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ከቅዱሱ ጌታችን ጋር ያለንን ቅዱስ ግንኙነት አበላሽና በካይ፣ እንዲያውም የአባታችንን ፍቅር አሟጦ አጥፊ ነውና፡፡ በፍሜውም ለሞት ያበቃናልና፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔርን ከሚቃወምና ከሚጠላ ከየትኛውም ኃይልና አካል ጋር በጥቅሙም፣ በመሻቱም፣ በምኞቱና በፍላጎቱ፣ በሃሳቡም ጭምር አንድነትን ከመፍጠርና ከመስማማት፣ ለማግኘትም ከመጣርና ከመፈለግ፣ ለመደሰትም መመኘት ፈጽሞ አይገባንም፤ ይህ ሁሉ የሚያደርጉ ከዓለማዊነት ኃጢአት ጋር ተባባሪ ናቸውና፡፡
     መንፈሳዊ ባርያ፣ ሯጭ፣ ወታደር ከሆንን የደስታችን ምንጭ ካሰማራን ጌታ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ የደስታችን ምንጩ ለእርሱ በመታዘዝ፣ ያዘዘንን የእርሱን ሩጫ በአገባቡ እንደቃሉ ስንሮጥ፣ ፍጻሜውና ዓላማው እግዚአብሔርን ከሚበድል ክፉ ዓለማዊነት በመራቅና በመዋጋትም ጭምር ሊሆን ይገባል፡፡
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ብርታትና ኃይል ሁነን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …





[1] ገጽ.204

No comments:

Post a Comment