Friday 23 June 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ ሁለት)

Please read in PDF

2.    ኃጢአት፦ በዕብራይስጥ [ኀቻታ] በግሪክ ደግሞ [ሐማርቲያ] ተብሎ የተነገረ ቃል ሲሆን፣  በተካካይ የአማርኛ ትርጉሙ ደግሞ “ዒላማን መሳት” ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር እንድንደርስበት የሚፈልገው ዋና ዒላማና ግብ አለ፡፡ እዚያ እርሱ ካሰበበት መድረስ አለመቻል ዒላማን መሳትና ኃጢአት ነው፡፡
     የእግዚአብሔር ልጆች ዋና ዒላማችን እግዚአብሔር ራሱ ነው፤ ከእርሱ ፈቀቅ ማለት ቀስትን እንደሚስት ዒላማ ሳች (መሳ.20፥16)፣ እግሩን በማፍጠን ከእውነት መንገድ ይስታል፤ (ምሳ.19፥2)፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ከእግዚአብሔር ያነሰ ዒላማ፣ ከእርሱ ያነሰ ግብም ሊኖረን አይገባም፡፡ ከእግዚአብሔር ያነሰ ዒላማ ካለን ግን፣ ያ የያዝነው ዒላማ መልካምም ቢሆን እንኳ ኃጢአት ነው፡፡

    በመሳፍንት መጽሐፍ፣ “ … እነዚህም ሁሉ ድንጋይ ይወነጭፉ ነበር፤ አንዲት ጠጕርስ እንኳ አይስቱም፤” የተባለላቸው፣ በዘመኑ የልብ በሚያደርሰው መሣርያ ቅንጣት እንኳ የማይስቱ ሰዎች ነበሩ፡፡ የኀጢአትም ትርጉም በንጽጽር ከዚህ ቃል ተነግሯል፡፡ ክርስቲያንም በማናቸውም መንገዱ እጅግ ላለመበደልና ላለመሳት መጠንቀቅ ይገባዋል፡፡ ከለበሰው ሥጋ የተነሳ ቢበድል ግን፣ “ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ፤” (1ዮሐ.2፥1-2) እንዲል፣ ፈጥኖ ወደኃጢአቱ ማስተሥረያ በመቅረብ ንስሐ ሊገባና መጋደሉንና ውጊያውን ሊቀጥል ይገባዋል፡፡
     በሌላ እይታ፣ ኃጢአት ዓመጸኝነት መሆኑን ተገልጧል፤ “ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፥ ኃጢአትም ዓመፅ ነው” (1ዮሐ.3፥4) እንደተባለ፡፡ ዓመጸኝነት የእግዚአብሔር ከሆነው ከማናቸውም ቅዱሱ ትእዛዝ መራቅና ለፈቃዱ አለመታዘዝን ያመለክታል፡፡ ዓመጸኝነት ስሜትን፣ አስተያየትን፣ ዝንባሌንና ድርጊትን ሁሉ አመልካች ነው፡፡ ይኸውም የታወቀውን ቅዱስ ሕግና እግዚአብሔር በሰዎች ልብ ያኖረውን መልካሙን ነገር ሁሉ መቃወም ነው፡፡
    ሕዝብም አሕዛብም ሕግን ያውቃሉ፤ ነገር ግን መፈጸም ባለመቻልና ባለመታዘዝ በእግዚአብሔር ላይ ዓመጹ፤ ሕግንም በመጣስ ተላለፉ፤ (ሮሜ.4፥15)፡፡ ከመጀመርያው ሰው አዳምም በኋላ ሁሉ ፍጥረት በበደልና በኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ተከሰሰ፤ (ሮሜ.3፥9)፡፡ ላልታዘዘው ቀዳሚው አዳም በመታዘዝና ሕግን ሁሉ በመፈጸም ሁለተኛው አዳም ፍጥረትን ሁሉ ተቤዠ፤ ከዚህም የተነሣ ሁላችን ከክርስቶስ ጋር እንተባበር ዘንድ በጽድቅ ሕይወት ልንመላለስ ተጠራን፡፡
   ከዒላማችን ላለመሳትና በዝንባሌያችንና በፈቃዳችን በኃጢአት እንዳንጸናና በእግዚአብሔር ላይ እንዳናምጽ፣ “በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ፡፡ ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤” (ዕብ.12፥3-4) እንደተባለ በብዙ ገና መጋደልና ኃጢአትን መቃወም እንዳለብን ተነገረን፡፡
     ኃጢአትን ማድረግም ሆነ አለማድረግም የገዛ ፈቃዳችን ጉዳይ ነው፤ ወደን ባደረግን ጊዜ ግን በገዛ ፈቃዳችን በእግዚአብሔር ላይ እናምጻለን፡፡ አዳም የተወቀሰበት ዋናው ምክንያትም ይህ ነበር፤ እግዚአብሔር በጠየቀው ጊዜ፣ “ …በገነት ድምፅህን ሰማሁ፤ ዕራቁቴንም ስለ ሆንሁ ፈራሁ፥ ተሸሸግሁም” (ዘፍ.3፥9)አለ፡፡ ባለመታዘዙ ዕራቁትነቱን አወቀ፤ “በሚወዳት” ሚስቱ ፊት መቆም እስኪያሳፍረው ድረስ የኀጢአት ራቁትነቱን አወቀ፤ ከኀጢአት ጋር ባለመጋደል ላገኘው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥጦታ እንደዋና ምንጭነት ኰነነ፡፡ ነገር ግን አዳም ሁሉን ነገር ያደረገው በፈቃዱ ነበር፡፡
     አዳም ኃጢአትን ያደረገው ከፈቃዱ የተነሣ እንጂ ነጻ ፈቃዱን ያስጨነቀና የጠመዘዘ አልነበረም፤ ከልባችን የምንሰጥለት ነገር እርሱ ሊገዛንና ሊሰለጥንብን ይችላል፡፡ አዳም አምላክ የመሆን ፍላጎቱ እንዲሸነፍና ፍጹም ተጋድሎውን እንዲተው አደረገው፡፡ ብዙዎች ኃጢአትን የኑሮአቸው ዘይቤና ዝንባሌያቸው እስከማድረግ የሚደርሱት እንደቅዱስ ቃሉ በትክክል ካለመዋጋታቸው የተነሣ ነው፡፡ በእርግጥ ከውጭ የሚያስገድድና እጅግ ጫና የሚፈጥር አካል አለ፤ ነገር ግን በዳግም ልደት ከማይጠፋው ዘር ከክርስቶስ ኢየሱስ በመወለድ ድል እንነሣውና እናስወግደው ዘንድ ተጠርተናል፡፡
    ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ አለ፦ “እርሱም ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም፡፡ በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም፡፡ ልጆች ሆይ፥ ማንም አያስታችሁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው፡፡ ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና፤” (1ዮሐ.3፥5-8)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ እርሱ ያለኀጢአት ነው፤ ወይም ኃጢአትን ፈጽሞ አላደረገም፤ አያውቀውምም፡፡ ከእርሱ ጋር የሚኖር የትኛውም እውነተኛ አማኝ ከእርሱ[በእርሱ] ተወልዷልና ከኃጢአት ጋር ፈጽሞ አይተባበርም፡፡
    እውነት ነው፤ ከክርስቶስ ከእርሱ ጋር ሞቱንና ትንሣኤውን ከተባበርን፣ በእርሱ ሆነን ከኅጢአት ጋር ፈጽሞ እንጋደላለን እንጂ ኃጢአትን አናደርገውም፤ አስተውሉ! “ኀጢአት ስላለማድረግ እያወራን አይደለም”፤ ከለበስነው ሥጋ አንጻር ልንበድል እንችላለን፤ ነገር ግን ኀጢአትን ዝንባሌያችንና የኑሮአችን ዘይቤ አናደርገውም፤ ማንም ማን ኀጢአትን አለሳልሶ ቢነግረን ፈጽሞ አንቀበለውም፤ ልንሰማውም አንታገሰውም፡፡ ኃጢአት ኀጢአት ነው፤ ሌላ ምንም መገለጫ ሊሰጠው አይችልም፤ ወዲያው እንደበደልን ግን እንደዳዊት(መዝ.50)፣ እንደጴጥሮስ(ማቴ.26፥75) ፈጥነን ልንመለስ ይገባናል፡፡
     አንዳንዴ ኀጢአት በ“ጌታ አገልጋዮች” መካከል ሊሽሞነሞን፤ ሊወደስና ሊንቆለጳጰስና ሊሞሸርም ይችላል፡፡ በጽድቅ እርሻ መካከል እንክርዳድ፣ “የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራም ቆሞ” (ማቴ.24፥15) ልናየው እንችላለን፡፡ በዚህ ጊዜ ስብከቱን፣ ተአምራቱን፣ መዝሙሩን፣ … ወደንና አድንቀን ወይም የላይ ላዩን ብቻ ተመልክተን በዚያው ከመቅረት ልንከለከል ይገባናል፡፡ ተኩላ ከሆኑ ከሐሰት መምህራን ብቻ ሳይሆን “ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ከሚሉ፣ በስሙም ትንቢት ከሚናገሩ፣ በስሙም አጋንንትን ከሚያወጡ፣ በስሙም ብዙ ተአምራትን ከሚያደርጉ” ነገር ግን ምንም የመንፈስ ፍሬ ከሌለባቸውና በኀጢአት ዓመጸኞች ከሆኑ “የጌታ አገልጋዮችም” እንድንርቅ ታዘናል፡፡ “ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ” (ማቴ.7፥22-23) ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ከተናገረ፣ እኛ እውቅና ልንሰጣቸውና ልንቀርባቸው አልተባለልንም፡፡ አዎ! ትኩረታችንና ዋናችን ኢየሱስ እንጂ ጸጋው ወይም “የወንጌሉ ሎሌ” ሊሆነን አይገባም፡፡ አዎን! ኀጢአትን በማናቸውም ሥፍራ ቢገለጥ በብዙ ልንዋጋውና ልንጋደል ይገባናል፡፡
ጌታችን መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ላንተ የሚያደላና የጨከነ መንፈስን ለልጆችህ አድለን፤ አሜን፡፡

ይቀጥላል…

1 comment:

  1. Yetwededke Wendeme YEDENGEL lege Geta Amlake EYESUSE KIRSTOSE Zemenhen Yebarkew. 30,60,100 yamare fre Yafra.

    ReplyDelete