“ገና ያልተሰናሰናለው” ዘመናዊው መናፍቅነት የሆነው፥ ድኅረ ዘመናዊነት
ወጣቱን ትውልድና “አዳዲሶቹን አማኞች” እያነሆለለበትና ኃጢአትን ያለገደብ ለማለማመድና ለማስፈጸም ከሚጠቀምበት አንዱ ማቀንቀኛ
ሃሳቡ፥ “ሰው ነጻ ፍጡር ፤ ለማንም የመገዛት ግዴታ የለበትም ፤ ተገዝቶም አያውቅም” የሚል የጸና አቋም አለው፡፡ ይህ አባባል
ሁለት ነገሮችን ሊናገሩበት ያሰቡ ያስመስላቸዋል ፤ (1) ድኅረ ዘመናዊነትን በልካቸው ለብሰው የታዩት አብዛኛዎቹ ምዕራባውያን ከፈሪሃ
እግዚአብሔር ተፋተው “በፊታቸው መልካም መስሎ የታያቸውን በማድረግ፥ ለምናደርገው ነገር ሁሉ ኃላፊነቱን የፈጠረን ይውሰድ የሚል
ኅሊና ቢስ ምክንያት ሲያቀርቡ ፤ (2) እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው የሰጠውን የምርጫ ነጻነት አጣመው ይተረጉሙታል፡፡
ይህን ሃሳብ ሳስብ ትዝ የሚሉኝ፥ ከአንገታቸው ያመኑት አይሁድ ናቸው ፤
ጌታ በአንድ ወቅት “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ቢላቸው፥
“የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ፦ አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ?” ብለው መለሱለት፡፡
(ዮሐ.8፥31-33) ንግግራቸው እጅግ ውሸታሞች መሆናቸውን ያሣያል፡፡ እንኳን ከዚያ በፊት ይህን በሚሉበት ሰዓት እንኳ በሮማውያን
ቅኝ ግዛት ነበሩና፡፡ ከዚያ በፊት በፈርዖናውያን ፣ በባቢሎናውያን ፣ በአሦራውያን ፣ በግሪካውያን ለብዙ ዘመናት ተገዝተውም ነበር፡፡
ነገር ግን ይህንን ሁሉ ሽምጥጥ አድርገው ካዱ፡፡ሁሉ የሚያውቀውን እውነት መካድ እልኸኝነትና አመጸኝነት ነው፡፡ አይሁድ ምንም መልካም
ነገር ቢወጣ ሊቀበሉት ያልወደዱት ትክክለኞች ሆነው ሳይሆን ሐሰተኝነታቸውን ለአደባባይ ስላሰጣውና በዚያም ንስሐ ስላልገቡ ነው፡፡
አካላዊ ባርነት ማንም ሊገጥመው የሚችል ነገር ነው ፤ ከኃጢአት ባርነት መውጣት ግን ያለጌታ ጉልበት ከንቱ የከንቱ ከንቱ የማይቻል
የራስ ጥረት ብቻ ነው፡፡
እንግዲህ ድኅረ ዘመናዊነት ይህን ያረጀ ኑፋቄ በአዲስ መልክ አመጣልን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ “ለጌታ ተገዙ” ይለናል(ሮሜ.12፥11)፡፡ ይህን እውነት ካሰላሰልን ሰው ከመገዛት ነጻ አይደለም ፤ሰው የሚገዛውን
መምረጥ ይችላል እንጂ ከመገዛት ነጻ አይደለም፡፡ቅዱስ ጳውሎስ፥ የሚበልጠውንና የመጨረሻውን ነገር ለጌታ ስለመገዛት ይነግረናል ፤
ሰው ለጌታ በፈቃዱ በጌታ ጉልበት ባይገዛ፥ አስጨንቆ የሚገዛው ሌላ ክፉ አካል አለ፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ፥ “ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው፦ አርነት ትወጣላችሁ እያሉ
ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና።”(2ጴጥ.2፥19) በማለት ከመንፈስ ቅዱስ የተናገረውን ቃል ፍጹም ዘንግተውታል፡፡
ነጻ ያልሆነውን ፍጡር ነጻ ትሆናለህ እያሉ መሸንገል፥ ከግብረ ገብ ግዴታ ነጻ ለመሆን መቃተትን ፤ ከሕግ ተገዢነት ነጻ ነኝ በማለት
እንደልብ ፤ ያለገደብ ኃጢአትን ለመፈጸም የሚያደረድር አጸያፊ ትምህርት ነው፡፡ አዎን! በጸጋ ብንድንም ከጸጋው በታች ሆነን ለእግዚአብሔር
ቅዱስ ፈቃድ ብቻ ልንታዘዝም ይገባናል እንጂ በነጻነት ሰበብ ከኃጢአት ጋር ዕቃቃ እንድንጫወት አልባለልንም፡፡ እንዲያውም ለምን
ይሆን ሰዎች(አሸባሪዎች) ለትምህርታቸው ተገዝተው ሰዎችን የሚያርዱት? በአደንዛዥ ዕጽ የሚናውዙት ፣ የዝሙት ዕርቃን ምስሎችን በማየት
የሚጠመዱት ፣ በጭላጭ መለኪያ አረቄና ለቁራጭ ሲጋራ የሚናውዙት ... በእውኑ እንደባርያ ባይገዛቸው ነውን?ጌታ ኢየሱስስ፥ “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው
ማንም የለም፤” (ማቴ.6፥24) በማለት አስረግጦ ሲናገር በእውኑ ተሳስቷል ልንል እንደፍራንን!? አዎን! ሰው ምርጫው እንጂ ነጻነቱ፥
ካለመገዛት ነጻ ፍጡር አይደለም፡፡
ሎሌ ምንደኛ ነው ፤ ጌታውን እስከከፈለው ድረስ የሚያገለግል፡፡ በሌላ
ንግግር ሎሌ ቅጥረኛ ነው፡፡ ድካሙ ለደመወዙ ፤ ጥረቱ ስለሚያገኘው ምንዳ ነው፡፡ ጥቅሙ ቢቀርበት መከራከርና መብቱን ማስከበር ይችላሉ፡፡
ጌታ ይህንን፥ “ … በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም
ይበትናቸዋል።” (ዮሐ.10፥12) በማለት የቅጥረኛ ወይም የሞያተኛ ባሕርይን በሚገባ ገልጧል፡፡ ሎሌ አገልጋይና ሎሌ አማኝ አንድ
የሚያደርጋቸው ባሕርይ ሁለቱም ጥቅመኞች መሆናቸው ነው፡፡ ጌታ ከስሌት አገልግሎትና ከስሌት ሕይወት ነጻ ያውጣን፡፡ አሜን፡፡
እኛ አገልጋዮች ለክርስቶስ ባርያዎች ነን ስንል፥ “ … እንደ እግዚአብሔር
ባሪያዎች ሁኑ እንጂ …” ወይም “በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ።” (1ጴጥ.2፥16 ፤ ገላ.5፥13) የሚለውን መጽሐፍ
ቅዱሳዊ ቃል መርሕ አድርገን ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በፍጹም ሰውነቱ ለእኛ ራሱንአሳልፎ የሰጠ ጌታ ነው፡፡ እርሱ ጌታና መምህር ሳለ
ከባርያም በታች ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ፡፡ በእስራኤል ባሕል ባርያ እንዳይረክስ ከእራት በኋላ እግር ያጥባል ፤
ጌታ ኢየሱስ ግን ከእራት በፊት የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ፡፡እንዴት ይደንቃል ይህ ትሁት ጌታ! እናንተ በመንፈሳዊ ሕይወታችሁ
ለክብራችሁና ለማንነታችሁ ምን ያህል ጊዜ ተጨንቃችሁ ይሆን? እስኪ ክብሩን የተወውን ጌታ አስታውሱ ፤ ምንስ ታወሳችሁ?
በጥንት ለጌቶች የሚሸጡ ባሮች ነበሩ ፤ ልዩ ምልክታቸውም፥ አንድ ባርያ
የጌታውን ፈቃድ ብቻ የሚሰማ ስለመሆኑ ጆሮውን ይበሳል ፣ የሄደበትን ሥፍራ እንዳያውቅ ዓይኑን በጨርቅ ይታሰራል ፤ ያለበትንና የመጣበትን
ነገር እንዳይናገር ደግሞ ምላሱን ይጠቀጠቃል ፤ ከዚያን ቀን ጀምሮ የጌታውን ፈቃድ ብቻ ይኖራል እንጂ የእኔ የሚለው ጊዜ ፣ ገንዘብ
፣ ኑሮ ፣ ሕይወት ፣ እቅድ ፣ መብት … አይኖረውም ፤ ሁለንተናው ጌታው ብቻ ነው፡፡
ክርስቶስ በከበረ ደሙ ዋጅቶ ከኃጢአት
ባርነት ነጻ አውጥቶ በፍጹም ፍቅር ለራሱ ገዝቶናል፡፡ “በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን
አክብሩ።” ፤ “በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ።” (1ቆሮ.6፥19 ፤ 7፥23) እንዲል፡፡ ባርያ ስለታማኝነቱ ከማንም
ይልቅ ጌታውን ብቻ ይሰማል፡፡ ክርስቲያኖችንሁላችንም በማናቸውም ደረጃ ላይ ብንገኝ እንኳ ታምኝነታችንን ማሳየትና ፍጹም የሆነ መታዘዝን
ከሰዎች ይልቅ በደሙ ለገዛን ጌታ እጅግ ሊሆን ይገባዋል፡፡
ለክርስቶስ ባርያ የሆንነው በፈቃዳችንና ያደረገልን እጅግ ልባችንን ነክቶት
ነው፡፡ እርሱ ያላደረገልንና ከዚህ ይበልጥ ሌላ ያደርግልን ዘንድ የሚገባው ምን ነገር የለም፡፡ አብ ሁሉን ነገር ከልጁ ጋር ሰጥቶናል
፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ይህን እውነት በልባችን ላይ አትሞታል ፤ እንኪያስ ልንገዛለት የሚገባን አንድ ምርጫችን እርሱ ቅድስት ሥላሴ
ብቻ ነው!!!ጌታ ኢየሱስ ምንም ነገሩን ሳይሰስት ለእኛ ራሱን አሳልፎ ከሰጠ ፤ እኛም እንደሎሌ ሳይሆን እንደባርያ ፤ መብቱንና
ጥቅሙን እያሰበ እንደሚያገለግል ምንደኛና ሞያተኛ ሳይሆን፥ ፍጹም ታዛዥ በሆነ ባርያ መንፈስ በታማኝነት ልንታዘዘው ፤ ልንኖርም
ይገባናል፡፡ ጣዕሙ ባለቀ ወይም በሚመርር ማንነት ውስጥ ሆነን ለመታዘዝ ከምንመጣ አሁን በጉብዛናችን ወራት እንመጣ ዘንድ እንዲገባን
ቃሉ፥ “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ፤” እንዲል አሁን በጤናችንና
በመልካም ቀኖቻችን ጌታን እንደባርያ እንታዘዘው (መክ.12፥1)፡፡ ለጌታ እንዲህ ያሉት መልካም ባርያዎች ያስፈልጉታል!!!
ጌታ ሆይ ለትሁታን ባርያዎችህ ማስተዋልን አብዛልን፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment