Sunday, 3 April 2016

ደብረ ዘይት - ጌታ ይመጣል!



     መናፍቃን ከሚክዷቸው የክርስትና መሠረተ ትምህርት አንዱ የክርስቶስን በክበበ ትስብእት ፤ በግርማ መለኮት ዳግመኛ መምጣት ነው፡፡ የክርስቶስ ዳግም መምጣት ትምህርት ክርስትናና አስተምኅሮው የተመሠረተበትና የቆመበት ዋና ዓለቱ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የዳግመኛ መምጣትን ትምህርት ስናነሳ በአብሮነት የሙታንን ትንሣኤ ትምህርት በአንድነት ማንሳታችን የግድ ነው፡፡ ሁለቱ ትምህርቶች ሰፋፊና በየራሳቸው መቆም የሚቻላቸው ቢሆኑም፥ ተያያዥና የማይነጣጠሉ ዋና ዓምዶች ናቸው፡፡
       ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦
“በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።” (1ተሰ.4፥15-18) (ለአጽንዖት የተሠመረበት የእኔ ብቻ ነው)

      በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ያለውን ሥነ መለኮታዊ አስተንትኖት ለጊዜው ልለፈውና፥ ቅዱስ ጳውሎስ ከተገለጠለት ጌታ፥ የተማረው የጌታ ቃል እንደተረዳው የጌታ መምጣት ፤ ከመጣም በኋላ የእርሱን መቀበላችንንና ነገረ ትንሣኤ ሙታን የማይለያዩ ፍጹም ተዛምዶ ያላቸው መሆኑን ከንባቡ እናስተውላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ራሱን ከሚያምኑት አማኞች ጋር በመቁጠር “እኛን” እግዚአብሔር ከጌታ ጋር ያስነሣናል ፤ እኛም የዚያን ጊዜ ጌታን እንደምንቀበል፥ ይህም በብዙ ክብር ሊሆን እንዳለ በግልጥ ይናገራል፡፡ ስለዚህም የትንሣኤ ሙታንን ትምህርት መካድ የጌታን ዳግመኛ መምጣት መካዱ ፤ የጌታን መምጣት የሚክድ፥ የትንሣኤ ሙታንን ትምህርት የሚክድ መሆኑን ጠቅላላ ጭምቀ ሃሳብ ማቅረብ እንችላለን፡፡
     ቅዱስ ጳውሎስ፥ “ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።” እንዳለውም፥ አብያተ ክርስቲያናት የሚጽናኑበት ትልቁ ቃላቸው  ጌታ ይመጣል ፤ ደግሞም ወደራሱ ይወስደናል የሚለው እውነተኛና የታመነ የተስፋ ቃል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጌታ ኢየሱስ ወደሰማያት ሲያርግ ያየችው ብቻ አይደለችም ፤ ዳግመኛ እንዲሁ በክብር ደመና እንደሚመጣ ደግሞ የተስፋውን ቃል የያዘችም ፤ የምታምንም ናት፡፡ (ሐዋ.1፥11)
     ስለዚህ ለእውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ መምጣት ዋና ነገር ነው፡፡ ከሰው ልጆችም ባሻገር ግዕዛን የሆኑና ያልሆኑትም ፍጥረታትም ጭምር ለከንቱነት ከተገዙበት ማንነት ባሻገር በመቃተት፥ “የፍጥረት ናፍቆት የሆነውን የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ፍጹም ይጠባበቃሉ” (ሮሜ.8፥19-22)፡፡ በእርግጥ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ከዘላለም ሕይወት ወዲያ ምን አይነት ልዩና ታላቅ ክብር እንዳለን፥ “አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም።” (1ዮሐ.3፥2) እንደተባለ ወደፊት ምን እንደምንሆን ለመንፈስ ቅዱስ እንጂ ለእኛ አልተገለጠም፡፡ “ነገር ግን፦ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥” እግዚአብሔር ለእኛ ያዘጋጀው ውብና ልዩ ፤ ደስም የሚያሰኝ በፍጹም በማንም ያልታሰበ እንደሆነ እንዲህ እንናገራለን። (1ቆሮ.2፥9) እንዲህም እናምናለንንም፡፡
   ቤተ ክርስቲያን ከትንቢታት ሁሉ ዋናና የቀራት ፤ እንዲፈጸምላትና ቶሎ እንዲሆን የምትወድደው ነገር ቢኖር የጌታ እንደገና መምጣት ነው፡፡ ይህ ቃል ግን ፍጹም የሚሠራውና የሚያገለግለው በመታመን ቃሉንና ፈቃዱን በመፈጸም ፤ ለክርስቶስ ኢየሱስ ወንጌል በመታዘዝ ለኖረች ቤተ ክርስቲያን እንጂ በቅዝቃዜ ወይም ለብ ብላ ፤ ዘመኗን ንስሐ ባለመግባት ለኖረችው ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ከአፉ ልትተፋ ወይም ከእጁ ልትጣል ባለ ከባድ አደጋ ውስጥ ልትወድቅ እንዳለ ቃሉ በግልጥ ያስቀምጣልና፡፡ (ራእ.3፥16)
    ሰው የጌታን መምጣት ችላ ካለ በኃጢአት የመጨማለቅ እድሉ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ በኖኅ ዘመን የነበሩትን ሰዎች አስቡ ፤ ዘመኑ ረጅም መስሏቸው፥ “ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፥ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ ባለማወቅ” (ማቴ.12፥38-39) እንደተታለሉ፥ የጌታን መምጣት በመዘናጋት ረጅም ዘመን እንዳላቸው የሚያስቡ ፤ የራሳቸውን ደስታ በመከተል፥ “ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሳቸውን የሚያጠላልፉ” (2ጢሞ.2፥4) በኑሮ ፈተና ራሳቸውን ለወጥመድ የሚያዘጋጁ፥ ጌታችን ድንገት እንደሌባ ይመጣባቸዋል፡፡
    እርሱ ተግተው ለሚጋደሉ ፤ በዚህ ዓለም ነውር ላልተሰነካከሉ ፣ መብራታቸውን ሳያጠፉ በማናቸውም ሰዓት ዝግጁ ሆነው ለጠበቁት የሚመጣላቸው እንጂ ለሌሎቹ የሚመጣባቸው ነው፡፡ አስተውሉ! የተሰጠን የወንጌል አደራና የምንቀበለው ሽልማት እንኳ የተሳሰረው፥ “በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ ፤ ... ” (2ጢሞ.4፥1) በማለት ለዳግም መምጣቱ ልዩ ትኩረትን በሚሰጥ አገላለጥ የተነገረ ነው፡፡
   መናፍቃን የጌታ ዳግመኛ መምጣትን የሚቃወሙትና የሚክዱት በአብዛኛው ብንጠቀልለው እንደኖኅ ዘመን ሰዎችን በኃጢአት የነጻነት መንገድ ለማሠማራት ነው፡፡ ብዙዎች ተጠያቂነትንና ኃላፊነት መውሰድን እንደልብ ከመሆንና ከመፈለግ የተነሣ አይፈልጉም፡፡ ዳግመኛ መምጣቱ ደግሞ ተጠያቂነትና ኃላፊነትን የሚያስከትሉ ጥያቄዎችን አዝሎ ይመጣል፡፡ መክሊት የማትረፍና ያለመትረፍ ጥያቄ (ማቴ.25፥14-30) ፤ ለባልንጀራ የሚገባውንና የሚያስፈልገውን ስለማድረግና ስላለማድረግ ጥያቄዎች የሚቀርቡትና(ማቴ.25፥34-46) ስለወሰድነውና ስላልወሰድነው ኃላፊነት የምንጠየቀው መንፈሳዊ ጥያቄ በዳግም መምጣቱ ጊዜ የሚቀርብ ነው፡፡  ይህን ሊያደርግ ጌታችን ይመጣል፡፡ ስንቶቻችን ግን ለኃላፊነት ራሳችንን ዝግጁ ያደረግን ነን? ስለባልንጀራችን የሚገደን ነንን?!
      የዳግም መምጣቱ ቀን ቤተ ክርስቲያን ሽልማቷን የምትቀበልበት ቀን ስለሆነ፥ የምትናፍቀውና በሕይወት ዘመኗ ሁሉ የምትጓጓለት ቀን ነው፡፡ ያንን ቀን በጉስቁልናና ተስፋ በማጣት የተጨነቀው ፍጥረት ያርፍበታል ፤ በመዘበትና በመገዳደር ፣ በመናቅና በጥላቻ ፣ እግዚአብሔር የለም በማለት በተሳለቁትና ባፌዙት ፣ እውነትንና ፍትሕን በመርገጥ በሐሰት ድኃውንና ስደተኛውን ባስጨነቁት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ የምትበረታበት ቀን ፤ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንም ስለምስክርነቱ ውርደቷና መበደሏ ፣ መናቅና መገለሏ በፍጹም ክብርና ሞገስ በጠላቶቿ ሁሉ ፊት የምትከብርበት ፤ የምትገንበት ቀን ነውና እጅግ የምትናፍቀው ልዩ ቀኗ ነው፡፡
    ዳሩ፥ ለመከበርና ለመወደድ ፤ ልትመጣ ባለችው በእግዚአብሔር መንግሥት ሞገስ ለማግኘት የጌታን ቀን መናፈቅ ለቤተ ክርስቲያን ይገባታል ስንል ልብሷን ባለማሳደፍ ያለዕድፈት ልትጠብቀው ይገባታል ማለታችን ነው፡፡  ይህን ስንል ደግሞ ኃላፊነት እንደሚሰማው ክርስቲያን እየኖርን ነው ወይ? የሚል ብርቱ ሙግታዊ ጥያቄ ለራሳችን አስቀድመን ማንሳት ይኖርብናል ብዬ አምናለሁ፡፡ አዎን! ጌታ ይመጣል፡፡ ስለዚህም ከምንም በላይ በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር በራሳችን ሃሳብ በመጠላለፍና በምቾት ልባችንን ልናከብድ አይገባንም፡፡ ጌታ ይመጣል ፤ ነገር ግን ሲመጣ እኛ እንደሚገባን ተገኝተናል ወይ? የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ መጠየቅ ዋናና ዘላለማዊ አድራሻችንን  የሚወስን ነው፡፡
  ኢየሱስ ክብራችን ፤ ኢየሱስ ጽድቃችን ፤ ኢየሱስ ናፍቆታችን ፤ ኢየሱስ ዕድል ፈንታችን ይመጣል ፤ ሲመጣም በቤቱ ይሾመናል ፤ ያከብረናልም፡፡ አቤቱ ይህን እውነት እንድናስተውል እርዳን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment