“እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት
ሊገባ አይችልም።” (ዮሐ.3፥5)
|
ኒቆዲሞስ የማታ ተማሪ ቢሆንም መምሕር ተብሎም ተጠርቷል ፤ ምናልባት ቀን
ቀን ሕዝብ በተሰበሰበበትና ጌታን ዙርያውን ሕዝብ በከበበበት ሁኔታ እንደልብ ለመወያየት ስለማይመች ወይም በማታው ክፍለ ጊዜ በደንብ
እንወደደው ሊያወራውና ከእርሱ ሊማር ወይም የአይሁድ አለቃ ስለሆነ በቀን መምጣትን ስለፈራ ሊሆን ይችላል፥ ሌሊቱን በቋሚ ተማሪነት
በመምጣት የተጋው፡፡ ባለ ሥልጣን እንደመሆኑ መጠን ሰው ሳይልክ ራሱ መምጣቱ ሊማር ፤ ሊረዳ ከልቡ መውደዱን ፤ የመንፈስ ጥማትም
ያለበት መሆኑን እናስተውላለን፡፡ ከጌታ ለመማር እርሱ ድካምና ዝለት ፤ ሌሊትና ቀን የማይፈራረቅበት የዘላለም መምህር ነው፡፡ ሲያስተምር
በቅንነት ነው፡፡ ከታወቁ ሊቃውንትና ፕሮፌሰሮች የሚማሩ እጅግ ይደነቃሉ ፤ ከእርሱ የሚማሩ ግን እጅግ የተወደዱ ናቸው፡፡
ኒቆዲሞስ ስለኢየሱስ
በተለያየ መንገድ ካጠናው የተነሳ፥ ጌታ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ መሆኑን አምኖ፦ “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ
ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ
እናውቃለን” በማለት በግልጥ መስክሮለታል፡፡ እውነተኛ መምህር እውነተኛ ደቀ መዛሙርት አሉት፡፡ ምስክርነታቸው ለዘላለም ፤ የማይናወጥም
ነው፡፡ ስላዳናችሁ ጌታ ስንቶቻችሁ እውነተኛ ምስክር በልባችሁና በአንደበታችሁ ፤ በሥራችሁም ጭምር አላችሁ?!
ጌታ ኢየሱስ፥ ለዚህ ትጉህ ተማሪ የአዲስ ኪዳን ማዕከል የሆነውን ትምህርት
ሊያስተምረው ወዶ፥ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።”
ይህን ቃል የሰማው ኒቆዲሞስ ሁሉ ነገር ግራ ነው የሆነበት፡፡ ኒቆዲሞስ ምን ጠይቆ ጌታ ኢየሱስ ይህን መልስ እንደመለሰለት ግልጥ
አይደለም፡፡ የጌታና የኒቆዲሞስ ሰፊ ውይይትም በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል አልቀረበልንም፡፡ ስለዚህ ክፍሉን እጅግ በማስተዋልና ለቅዱሳት
መጻሕፍት ላዕላይነት በመገዛት መንፈስ፥ በማስተዋል ፤ በልበ ሰፊነት ልናጠናው ይገባናል፡፡ ይሁንና ኢየሱስ ለዚህ የእስራኤል መምሕር
ከልብ መልስ አጊኝቶ እንዲሄድ ወዶለታል፡፡
ከመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በሥጋ አእምሮ ማንም የማይረዳውን ምስጢር
ጌታ ኢየሱስ ተናገረ፡፡ ኒቆዲሞስም እንዲረዳው በምሳሌ ነገረው፡፡ ነፋስ በዐይን ባይታይም እንኳ በሚያከናውነው ተግባርና በሚያሰማው
ድምፅ እንደሚታወቅ አስረዳው፡፡ ነፋስ ባለመታየቱ ሳይሆን በሚሠራው ሥራው መኖሩ ይታወቃልና፡፡
ሁለተኛው በምሳሌነት ለኒቆዲሞስ የቀረበው ከሥጋ እናትና አባት በቀዳሚነት
የመወለድ ምሳሌ ነው፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ፤ ምድራዊ ልደት ብቻ ያለው ምድራዊ ነው ፤ ነገር ግን ከላይ ለመወለድ ወይም
ዳግም ለመወለድ ከውኃና ከመንፈስ መወለድ ግድ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ አለምም ሆነ በዘላለም የእግዚአብሔር መንግሥት [1]
ለመግባት ከእግዚአብሔር ዳግመኛ መወለድ ግድ ነው፡፡ ከላይ የሆነውን ልደት የምንወለደው ደግሞ ከውኃና ከመንፈስ እንደሆነ በግልጥ
ተነግሯል፡፡
“ውኃ” የሚለውን ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሲተረጉሙ፥ የመጀመርያው
አይሁድ የዮሐንስን የንስሐ ጥምቀትን ሊያሳይ ይችላል በማለት (ዮሐ.1፥33) ውጫዊ መንጻትን በውኃ ይፈጽሙ ከነበረው ትምህርት ጋር
በማያያዝ ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ግንኙነት ለማድረግ ዳግም መወለድ እጅግ ግዴታ ነው፡፡ ይህ አባባል ለኒቆዲሞስ
ከባድ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም አይሁዳዊ በመሆኑ ብቻ እንደሚድን በልቡ ይመካ ነበርና፡፡ ሌሎች ደግሞ ክርስቲያኖች ለምስክርነት
በውኃ የሚጠመቁትን ጥምቀት እንደሚናገርም ያስተምራሉ፡፡ ይህንንም ከሞቱና ከትንሣኤው ጋር በማስማማት ያስተምሩታል፡፡ በእርግጥም
በውኃው ስንሰጥም ሞቱን ፤ ስንወጣ ደግሞ ትንሣኤውን መተባበራችንን ማሳየቱ እሙን ነው፡፡ (ሮሜ.6፥4) ሦስተኛዎቹ፥ ደግሞ ውኃ
የሚለው ቅዱስ ቃሉን እንደሚያመለክት ይናገራሉ፡፡ “ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን።” (ያዕ.1፥8)
፤ “እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤” (ዮሐ.15፥3) የሚለውንም ቃል በማንሳት ከቅዱስ ቃሉም መወለድ እንዳለብን
እርግጠኞች ሆነው ያስተምራሉ፡፡ አስተዋይና በልበ ሰፊነት ቃሉን የሚመረምር ሰው ደግሞ በቃሉ ሚዛንነት መመዘን ይገባል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የሚተረጎመው በመጽሐፍ ቅዱስ ነውና፥ “ከውኃና ከመንፈስ
መወለድን” በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር፥ “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን”
(ቲቶ.3፥5) እንዲሁም፦ “በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት” (ኤፌ.5፥26) ተብሎ ተገልጧል፡፡ በዚህ ሥፍራ ውኃ
መንጻትን ሲያመለክት፥ መንፈስ ደግሞ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ መወለዳችንን የሚያሳይ እውነት ነው፡፡ ይህም ፍጹም የሆነ የልብ መለወጥን
ከሚያሳይ ማንነት ጋር ያለን መወለድ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ከፊተኛው ልደት የሚሆን ሳይሆን ማለትም በግልና በራስ ጥረት የማይሆንና
ከእግዚአብሔር ብቻ የሚሆን መሆኑን እናስተውላለን፡፡
ከዚህም የተነሣ ከእግዚአብሔር የሆነ የዘላለም ሕይወት ሠርጾ በአማኙ
ልብ ውስጥ ይገባል (ዮሐ.3፥16 ፤ 2ጴጥ.1፥4) ያመነውም የእግዚአብሔር ልጅና የአዲሱን ሰው ማንነት ይለብሳል (ዮሐ.1፥12
፤ ሮሜ.8፥16 ፤ ገላ.3፥26 ፤ 2ቆሮ.5፥17 ፤ ቈላ.3፥9)፡፡ እንግዲህ ስለዳግም መወለድ ስናነሳ የራስ ጥረት ምንም ድርሻ
እንደሌለበት ፍጹም ልናስተውል ይገባናል፡፡ የሆነልን ከእርሱና በእርሱ ብቻ ለእኛ የሆነ ነው እንጂ፡፡
በሌላ ንግግር ኢየሱስ ነፋስን [2]
በመንፈስ ቅዱስ መስሎ ይናገራል፡፡ ነፋስ መኖሩን በሥራው እንደምናውቀው ሁሉ መንፈስ ቅዱስንም በሥራው እናውቀዋለን ፤ የሰዎችን
ሕይወት ሲለውጥ ፣ ሲያድን ፣ ከርኩሰት ሲያስመልጥ ፣ የቃሉን ፍቺ አብርቶ ሲገልጥ … ብናየውም አሠራሩንና አደራረጉን በፍጹም አናስተውለውም፡፡
አንድንም አማኝ እንዴት አድርጐ ለእግዚአብሔር መንግሥት ብቁና ሙሉ አድርጎ እንደሚያዘጋጀው አናውቅም ፤ ግን ሲሠራ እናየዋለን ፤
እናምነዋለንም፡፡ ይህ ነገር እንዴት ልብን የሚመላ ምስጢር ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ይህ ነገር በጊዜው ፍጹም አልገባውም ፤ በኋላ ግን
ገብቶትም ፤ አምኖትም በሕይወት ፍጹም ኢየሱስን እንደተከተለው በቀራንዮና በጎልጎታ እናየዋለን፡፡ (ዮሐ.19፥39)
አዎን ጌታ መንፈስ ቅዱስ ይለውጣል ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ በቤዛው ደም
ያነጻል ፤ የቃሉንም ፍቺ በልባችን ያበራል ፤ በዐይን የማይታይ ቢሆንም አዲስ ሕይወትን ፤ አዲስንም ልብስ ፤ አዲስ ማንነትን ፤
አዲስ ተፈጥሮን ይሰጠናል፡፡ ይህም በዳግም ልደት ከውኃውና ከመንፈሱ መወለዳችን ነው፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ስለዚህ ድንቅ
ነገር እናመሰግንሃለን፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment