Friday 15 April 2016

አገርም፥ ይህን ያህል ይዘነጋል ለካ!




  መርሳት የተፈጥሮ ባህርያችን ነው ፤ ነገር ግን ጤነኞችና ኃላፊነት የሚሰማን ከሆነ ለዘወትር ልንዘነጋቸው የማይገቡን ነገሮች አሉ፡፡ በጦር ሜዳ ያለ ወታደር ትጥቅና የጦር መሣርያውን ፣ በሙሽርነት ያለች ሴት መጌጥና መዋብን ፣ በበሽተኞች የተከበበ ዶክተርና የሕክምና ባለሙያ ስለሚያክምባቸው የሕክምና መሣርያዎች ፍጹም ሊዘነጉ ከማይችሉ ጥቂት ነገሮች መካከል ናቸው፡፡ እነዚህንና ተመሳሳይ ነገሮችን መርሳት በሕይወት ጭምር አላስፈላጊ ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡
   ከምንም በላይ ደግሞ ሕዝብን ለማገልገል በኃላፊነት የተቀመጥን ሰዎች ዘወትር ልመናችን እንደንጉሥ ሰሎሞን ብዙ ሃብትና ብዕል እንዲሰጠን ከመመኘት ይልቅ ሕዝቡን መምራት የሚያስችለንን ማስተዋልና ጥበብን እንዲሰጠን ቢሆን መልካም ነው፡፡ ሰሎሞን ይህንን ስለለመነ (1ነገ.3፥11)፥ “እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው።” (1ነገ.4፥29) ብሎ ቃሉ ይነግረናል፡፡ ልበ ሰፊነት ብዙ የሚመረምርና የሚያሰላስል ልብ ስለሆነ በዝንጋኤ የማይጠቃ አስተዋይ ልብ ነው፡፡

     ይህ ጥበብና ማስተዋል የሌላቸው መሪዎችም ሆኑ ባዕለ ሥልጣናት ግን ሥራቸውን ብቻ ሳይሆን ትዳራቸውንና ልጆቻቸውን እስከመርሳት ሊደርሱ ቢችሉ ላይደንቀን ይችላል፡፡ ግን አንዳንዴ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን አገርም ይረሳልን? የሚል ጥያቄ እንዳስነሳ የቆነጠጠኝን ዜና አንብቤ ነበር፡፡ “ከሦስት ዓመታት በላይ አገልግሎት ሳይሰጥ የተቀመጠ የኩላሊት ማሽን በዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታሉ መገኘቱንና በሌላ ማጣርያ ግን ማሽኑ ለአሥራ አምስት ዓመታት መቆየቱን ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው ባለሥልጣናት ገልጠዋል፡፡” የሚል ዜና አንብቤ ለማመን ብዙ ተቸግሬ ፤ “አንቺ ኢትዮጲያዬ ሆይ ዝርክርክነትሽ እስከምን ድረስ ነው? ... እንዲህ ያሉ ነገሮች ከተረሱ ሌላውማ ምን ይሆን? ... እያልኩ ብዙ አሰላሰልኩ፡፡
   አንድ የኩላሊት ታማሚ በዚህ መሣርያ ለመታከም ቢያንስ በአንድ ቀን የአራት ሰዓት  አገልግሎት ያስፈልገዋል ፤ ከመሣርያውና ከግልጋሎቱ ውድነት የተነሳም ሊታከሙበት የሚችሉት እጅግ ጥቂት ሰዎች ሲሆኑ፥ ብዙዎቹ በብዙ እርዳታና ልመና ገንዘብ አሰባስበው ፣ ባህርና ውቅያኖስ አቋርጠው የመሔዳቸውም ምስጢር መሣርያው በአገር ውስጥ አለመገኘቱና ያለውም ከበሽተኛው ቁጥር ጋር ካለመመጣጠኑም ባሻገር እጅግ ውድ መሆኑ ነው፡፡ ደጉ ሆስፒታላችን ግን ይህን የመሰለ መሣርያ እጅግ ቢያንስ ለሦስት ዓመታት ምንጣፍ ሥር እንደተወሸቀ አሥርና አምስት ብር ረስቶታል፡፡
  ከግማሽ ሚሊዮን ብርና ከዚያ በላይ በብዙ ኡኡታና ጩኸት ፤ በእልፍ ማስታወቂያና ርብርብ የሚሰበሰብላቸው የኩላሊት ታማሚ ወገኖቻችን እንባና ልቅሶ እንኳ ይህንን ሆስፒታልና በዚህ ዙርያ የሚሠሩትን ሰዎች እንዴት ይሆን አላነቃ ያለው? እንዲህ ያለ ውድ ዋጋ ለብዙ ሕሙማን እረፍትና ከሥጋ ደዌ መታከሚያ የሆነው መሣርያ ይህን ያህል እንዴት ሊዘነጋ ቻለ? ኸረ ለመሆኑ እኛ የማንረሳው ነገር የጥንት ቂምና ሥራ የማይሠራውን የጥንት ጀግንነት ብቻ ነውን?
     በእርግጥ ይህ ነገር የመንፈሳዊ ሕይወታችን መደንዘዙና አዚም ያንዣበበበት ከመሆኑ የተነሣ፥ የአስተዳደር ፣ የኦዲት ፣ የክትትልና የቁጥጥር ሂደታችን እጅግ የሞተ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ለቁጥር የሚታክቱ ለብዙዎች “ዕድሜ ማቆያ” መሆን የሚችሉ ነገሮች መበላሸታቸው ፤ መውደማቸው ፤ ሥራ ላይ ሳይውሉ የአገልግሎት ዘመናቸውን ጨርሰው የተቃጠሉ ፣ የተቀበሩ ፣ የተወገዱ መድኃኒቶች ፣ ምግቦች ፣ የሕክምና ፣ የእርሻ ፣ ለምርምር የሚረዱና ሌሎችም መሣርያዎች ... ስንት ይሆኑ? ለመሆኑ ኃላፊነት እንደሚያስከትል ተሰምቶን እንውቃለን?  
     በዚህ ምክንያትስ በስማቸው የመጣላቸው ምግብ ፣ መድኃኒትና መሣርያ ስላልደረሳቸው ስንት ድኾች ጮኸውብን ፣ ስንት በሽተኞች አልቅሰውብን ፣ ስንት ጉዳተኞች አዝነውብን ፣ ስንት የተራቡ ረግመውን ፣ ስንት የተጠሙ ምሬታቸውን ለአምላክ ተናግረውብን ፣ ስንት ልባቸው የተሰበረባቸው ስብራታቸውን ከአምላክ ተነጋግረው “ተበቀልልን ፤ በእኛ ላይ የሆነውን እይ” ብለው ለአምላክ አሳልፈው ሰጥተውን ይሆን? ኢትዮጲያዬ የስንት ድኃ ፣ ታማሚ ፣ እንባ ፣ ረሃብተኛ ፣ ተጠሚ ... እንባ ይሆን ያለብሽ? ስንቱን ይሆን የምትረሺውና የማታስታውሺው?
    ምነው አገሪቱስ ድኃ አይደለችም ይህንን ምን ማጋነን ያስፈልጋል? ትሉኝ ይሆናል፡፡ ድሆች መሆናችንን በትክክል የምናውቅ አይመስለኝም፡፡ የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያንን ታውቋታላችሁ? እንዲህ ነበር የተባለችው፦ “ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥ ... ” (ራእ.3፥17) ድሀ መሆንን ማወቅ ለንስሐ እድል ነው ፤ ድሀ ሆነን፥ መሆናችንን አለማወቅ ግን እጅግ አደገኛ አዚም ነው፡፡ ድሀ መሆኑንን የማያውቅ ምን እንደሚያስፈልገው እንኳ በትክክል አያውቅም፡፡ ስለዚህም ድህነትን አለማወቅ መታወርና መራቆት መጎሳቆልና እጅግ ምስኪንነት ነው፡፡
     ኢትዮጲያ ድሀ መሆንዋን በትክክል የምታውቅ አይመስልም፡፡ የሃብት ፣ የብር ፣ የወርቅ ... አይደለም ፤ የማስተዋልና የጥበብ ድህነት እንጂ፡፡ የታመሙ ፣ የተራቡ ፣ የተጠሙ ፣ የተሰደዱ ፣ የተጎሳቆሉ ፣ የሚሰቃዩ ፣ የሚማቅቁ ፣ ልጆችዋን የምትረሳ እናት ምን አይነት እናት ናት? ኢትዮጲያ ማለት አንተ ፣ እኔ ፣ እኛ ፣ ሁላችን ነን፡፡  የምንረሳ እኛ ነን ፤ የምንዘነጋ የማናስተውል እኛ ነን? ድሃ የምናስጨንቅና ፣ የማንራራለት እኔና አንተ ነን? በሽተኛውን በተኛበት ፣ ረሃብተኛውን ከክትክታ ዛፍ ሥር የምንረሳ ፣ በወኅኒ ያለውንና ፍርዱንና ቅጣቱን የጨረሰውን የምንረሳ ፣ ለድኃ የመጣውን መድኃኒት ፣ ምግብ ፣ ... ከመስጠት የምንረሳ እኔ ፣ አንተ ፣ እኛው ነን፡፡ ታዲያ የስንት ድሃ እንባ ፣ የስንት እስረኛ ጩኸት ፣ የስንት ረሃብተኛ ምሬት በእኔና በእኛ ያለብን ይመስላችኋል? በእውኑ እግዚአብሔር የማይሰማቸው ይመስላችኋልን?
    ኢትዮጲያዬ እንዲህ የሚል ወዮታ አለብሽ፥ ዳኞችሽ፦ “መበለቶችም ቅሚያቸው እንዲሆኑ፥ ድሀ አደጎችንም ብዝበዛቸው እንዲያደርጉ፥ የድሀውን ፍርድ ያጣምሙ ዘንድ፥ የችግረኛውንም ሕዝቤን ፍርድ ያጐድሉ ዘንድ የግፍን ትእዛዛት ለሚያዝዙ፥ ክፉንም ጽሕፈት ለሚጽፉ ወዮላቸው!” (ኢሳ.10፥1) ... ባለሥልጣኖችሽ ከድሃው መሬትን እየነጠቁ መሬትን ለራሳቸው እያከማቹ ሃብትን ያበዛሉና፦ “ስፍራ እስከማይቀር ድረስ እናንተም በምድር ላይ ብቻችሁን እስክትቀመጡ ድረስ፥ ቤትን ከቤት ጋር ለሚያያይዙ እርሻንም ከእርሻ ጋር ለሚያቀራርቡ ወዮላቸው!” (ኢሳ.5፥8) የሃይማኖት መሪዎችሽ የሕዝቡን መንፈሳዊና ሥጋዊ ባዶነት አይተው ፍጹም በመራራት አልጸለዩለትም ፤ አልማለዱለትም ፤ ካላቸውም አላካፈሉትም ፤ በትክክልም አላዩልሽምና በብዙ ስላንቺ ልቤ ተጨነቀ፡፡
     ለዘረኝነት ፣ ቅማንትና ምንጅላታቸውን ቆጥረው የማይዘነጉት ልጆችሽ በሽተኞችና የተራቡ ልጆችሽን ለደቂቃ ማስታወስ አቅቷቸዋልና እባክሽ አገሬ ንስሐ ግቢ ፤ በልብሽ አትመኪ ፤ ወደፈጣሪሽ ልብሽን አዘንብለሽ ንስሐ ግቢ ፤ የኩራትና የትዕቢት ልብስሽን ከልብሽ ቅደጂና በዚህ ወራት ንስሐ ግቢ፡፡ አገሬ ታመሻልና እግዚአብሔር ይማርሽ፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment