Tuesday, 19 April 2016

በጋምቤላ ፤ በሜድትራኒያን ዳርቻ … የሆነው፥ ለእኛ የ“ንስሐ ግቡ” ደወል ይሆን?




“አባቶቻችሁም እንደ ነበሩ አንገተ ደንዳና አትሁኑ ፤ እጃችሁንም ለእግዚአብሔር ስጡ፥ ለዘላለም ወደ ተቀደሰው ወደ መቅደሱም ግቡ፥ ጽኑ ቍጣውም ከእናንተ እንዲመለስ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ። አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነውና፥ ወደ እርሱም ብትመለሱ ፊቱን ከእናንተ አያዞርምና ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁ በማረኩአቸው ፊት ምሕረትን ያገኛሉ፥ ደግሞም ወደዚህች ምድር ይመለሳሉ።” (2ዜና.30፥8-9)


    ከወደጋምቤላ እናት እስካዘለችው ልጇ ድረስ ተቀልታ በጠቅላላ ከ148 ሰዎች መታረዳቸውን ሰምተን ጆሮዋችን ሳያባራ፥ ከወደሜድትራኒያን ባሕር ዳርቻ ደግሞ ትውልደ ኢትዮጲያውንና ኤርትራውያን ይበዙበታል በተባለ የስደተኞች የባሕር ጉዞ ጀልባ ተገልብጦ ከ400 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ተረዳን፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ ኢትዮጲያውያን በዚሁ በሜድትራኒያን ባሕር ዳርቻ በሰው በላው አይ ኤስ አይ ኤስ ዜጎቻችን እንደዋዛ እንደበግ ታርደው ደማቸው በከንቱ ከባሕር ጋር ተቀላቀለ፡፡

    ለመሆኑ የዚህች አገር የሰቆቃ ድግስ መች ነው የሚያበቃው? የኢትዮጲያችን ዕልቂትና እንግልት የት ነው የሚገደበው? ለሰቆቃችን ፍጻሜ የሚያበጅለት የትኛው ብርቱ ክንድ ይሆን? ሞት ዕጣ ፈንታችን ፣ መታረድ ጽዋ ተርታችን ፣ በስደት ወጥቶ የባሕር እራት መሆን “የአርባና የሰማንያ” ቀን ዕድላችን ከመሆን የሚያከትመው መችና በማን ነው? ከውጋጋን ይልቅ ጨለማው ምነው ከበደ? የሕይወታችንና የኑሮአችን የጧፍ ክር ተስለምልሞ ከመብራት ወደመጤስ ምነው ቸኰለ? ያለፈውን ሃዘን አንደኛውን ዓመት “መታሰቢያውን ሳናከብር” ሌላ ምርር ያለው ሐዘን ምነው ሊያገኘን ፈጠነ? 
   ይህን ሁሉ ነገር የመልካም አስተዳደር ፣ የመንግሥት ችላ ማለት ፣ የመሪዎች ቅምጥልነት ፣ የሃብታም ዜጎቻችን ፍጹም ራስ ወዳድነትና ሌሎች ተመሳሳይ ምክንያት ጠቅሶ እንደዋዛ ማለፉ አልሆንልህ አለኝ፡፡ ሁሉን ነገር በመሪና በሕዝብ አለቃ ላይ አላኮ ማለፉን ነፍሴ አልወደደችም፡፡ እርግጥ ነው መሪ “የአንበሳውን ድርሻ” ተጠያቂ ነው ብንል እኛስ ከአንበሳው ድርሻ ከጽዋው አንካፈል እሆን እላለሁ?
   ይህ ሁሉ ለምን ሆነብን? ለምንስ አገኘን? ካለፈው ቀና ሳንል ሌላው መልሶ ለምን ያጐብጠናል? መሪና የሕዝብ አለቃ ላይ ብቻ ተጠያቂነትን ማስቀመጥ፥ እኛን ሊመጣ ካለው ቁጣና ፍርድ ያስመልጠን ይሆን? እውነት ለመናገር ሕግ ተላላፊው መንግሥትና የሕዝብ አለቃ ብቻ ነውን? አንድ በየቀኑ የሚገጥማችሁን ምሳሌ ላንሣ ፤ አሥራ አንድ ሰው መጫን በሚገባት መኪና ስትሄዱ፥ ሹፌርና ረዳት አሥራ ስድስት ፤ አሥራ ሰባት ሰው ሲጭኑ ፣ አንዱ “አይሆንም አትጫን … ለምን ይሆናል?” ቢል፥ “ተው ወዳጄ ጠጋ በል ፤ ለአጭር ደቂቃ ጉዞ ምን አጨቃጨቀህ? ያው ተለምዶ የለ ፤ ጠጋ በል ፤ አንተ ምን አጣላህ?” ብሎ አስተዛዝኖ ሕግ ተላላፊው ማን ነው? እኛ አይደለንምን?
    ጉቦ ሰጪ ማን ነው? … የሴቶችና የሕጻናትን ገላቸውን ቸርቻሪና ከዝሙታቸው ትርፍ ሃብት ሰብሳቢ ማን ነው? የውጪውን ዓለም እንደገነት፥ ያለንበትን እንደገሃነም ሲሳልልን አምነን የገዛ ልጃችንን ለሰው በላ ደላላ የሰጠን እኛ አይደለንምን? ጉልበታቸውን በዝብዘን ያሠራናቸውን ሠራተኞች ደመወዛቸውን ቀምተን በባዶ የምንሸኝ ፣ ደብድበን ደማቸውን እያዘራን ከመርዳት ፤ ከመራራት ይልቅ ከቤታችን ያሳደድን እኛ አይደለንምን?

     ለዝሙታቸው መደበቂያ ምድሪቱን በውርጃ የደም ምድር ያደረጉት የእኛው ሴቶች ልጆችና ኪሳቸውን ለማደለብ የጨከኑ የሕክምና “ባለሙያዎቻችን” አይደሉምን? የመጠቀሚያ ቀኑ ባለፈበት ምግብና መድኃኒት ፤ ከቅቤ ጋር ሙዝ ፣ ከስኳር ጋር አሷ ፣ ከበርበሬ ጋር ቀይ አፈር … የሚሸጡልን የእኛው ከወገን ልጅ ይልቅ ገንዘብ ያስበለጡ ስግብግብ ነጋዴዋቻችን አይደለምን? ደግሞስ የስንቱ ጤና ፣ ደህንነት … የተናጋው በእኒሁ ነጋዴዎች አይደለምን?
   ትላንት በገዛ መሳርያችን ታጥቀን የውድ ወገናችንን ደም በአደባባይ አፍስሰን ፣ አካል ጉዳተኛ ካደረግንበት ክፋታችን ንስሐ ገብተናልን? በስንቱ ዳኛ ፍርደ ገምድልነትና ጠማምነት ስንት ሰው ሃብቱን ፣ ትዳሩን ፣ ነጻነቱን ያጣ ይመስላችኋል? እኛ በእነዚህና በሌሎች እጅግ ብዙ ነገራችን ንስሐ ገብተናል? ሁሌ መንግሥትን ከመክሰስና በሌላው ላይ ጣታችንን ከመቀሰራችን እኛ ውስጥ ያለውን ምሰሶ አስተውለናል?
    የእኛ እጆች ከበደል የጠሩ ናቸው? አልሰረቁም? ፣ አልተማቱም? ፣ ደም አላፈሰሱም? ፣ ውርጃ አላስወረዱም? ፣ ጉቦ አልሰጡም? ፣ ጠማማ ፍርድን አልጻፉም? ፣ የሰውን ሰነድ ሰርዘው ፤ አልደለዙም? ፣ ስም የሚያጠፋ ጽሁፍ አልጻፉም?
   አንደበቶቻችን ንጹሐን ናቸውን? አልተሳደቡም? ፣ አላሙም? ፣ አልዋሹም? ፣ አልሸነገሉም? ፣ በሐሰት አልማሉም? ፣ ደግሞስ አልመሰከሩም? ፣ በቃሉ እውነት ላይ አላፌዙም? ፣ አልዘፈኑም? ፣ የአመጽን ቃል አልተናገሩም? ፣ በከንቱ አልተቆጡም? ፣ ጻድቁን ወቅሰው ኃጥኡን አላመሰገኑም?
    መላ ብልቶቻችን በእግዚአብሔር ፊት እንደሚገባ ንጹሐን ናቸው? አዎ! በጋንቤላና በሜድትራኒያን ዳርቻ የሆነው ምናልባት በእኛው ኃጢአት ቢሆንስ? በእኛው ነውር ቢሆንስ? እኛ ንስሐ ከመግባት ደንድነን ቢሆንስ? ዘወትር መንግሥትን ፣ ሁሌም የሕዝብን አለቃ መኰነን በእግዚአብሔር ፊት ንጹሐን አያደርገንም፡፡
     አዎን! ከመሞት ቤታችንን ብናስተካክልና በሕይወት ብንኖር አይሻልምን? (2ነገ.20፥1 ፤ ኢሳ.38፥1) እኛ ብንመለስ ፣ በፍጹምም በንስሐ ተዋርደን በፊቱ ብንቆም ግን እግዚአብሔር ፦
   ፍርድን ያደርግልናል፥ ምንም ብንበድለው እንኳ ከልጁ ከክርስቶስ ኢየሱስ የተነሣ በደላችንን ሁሉ ይቅር  ይለናል ፤ ይራራልናል ፤ በማረኩንም ፊት ምሕረትን ይሰጠናል ፤ (2ነገ.8፥50 ፤ 2ዜና.30፥8 ፤
   አዎ! እንደፈቃዱና እንደሃሳቡ በፊቱ በንስሐ ብንመለስ፥ ከተበተንንበት ፣ በምርኮና በኃጢአትም ፤ በማስጨነቅም ከሚገዙን ምድር ሊመልሰን ይቻለዋል ፤ (ነህ.1፥8-9)
   አዎ! ወደእርሱ ብንመለስ ከስብራት የሚፈውሰን ፣ ከተመታንበት ምት የሚጠግነን እርሱ እግዚአብሔር ነው ፤ (ሆሴ.6፥1)
   የከበደብንና ያጎበጠን የነውርና የኃጢአት ቀንበር ፤ አላሳርፍ ያለን ከባዱ ሸክማችንን የሚያወርድልንና ቀሊሉን ሸክም ለእኛም ለትውልዳችንም የሚሰጠን ፤ ከመቅበዝበዝም የሚያሳርፈን እርሱ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ (ዘጸ.33፥14 ፤ መዝ.116፥7 ፤ ማቴ.9፥36 ፤ 11፥28 ፤ 1ጴጥ.2፥25)
    ስለዚህም እባካሽ አገሬ ሆይ! ለምድርሽ ፈውስ መካሰስ ፤ መወነጃጀል አይረባንም ፤ ራሳችንን በዚህ በጾሙ ወራት እናዋርደው! ንስሐም እንግባ፡፡ እርሱ በቃችሁ ብሎ እንዲያሳርፈን እኛ ጨክነን ከክርስቶስ ደም የተነሣ ኃጢአትን በቃን ብለን እንመለስ ፤ በስሙም የተደረገልንን ሥርየትና መዳናችንን አምነን በመቀበል በሕይወት እንኑር፡፡
      አቤቱ ማስተዋልን አብዛልን፡፡ አሜን፡፡




4 comments:

  1. እግዚአብሔር አምላክ አብዝቶ ይባርካችሁ። ህዝባችን ዛሬም ለልዑል እግዚአብሔር ልቡን ማስገዛትና እርሱን ብቻ ማምለክ እስካልጀመርን ድረስ እርሱ ቁጡ በእኛ ላይ ነው። ዛሬ በዚህ ዘመናችን የአምልኮት ሥርዓታችን ሁሉ ጠፍቶ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ካላይ እስከ መጨረሻው ድረስ ያሉት ሁሉ የነዋይ አገልጋዮች እና እውነት የማይነገርበት ወቅት ላይ ነው ያለነው።በየቤተ ከርስቲያናችን ከታርክ ባሻገር ምን በእያንዳንዳችን የሕይወት ለውጥ በአገልጋዮችና በተከታዮች ዘንድ አይታይም። ለዘህም ነው እግዚአብሔር በቃሉ ይናገረናል።ሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። ማር ም 7 ቁ 7። አምልኮታችን የውሸት የማስመሰል ለግል ጥቅም ብቻ ነው። እወነቱን ክደን በሐሰት መንገድ ላይ እየተጓዝ ነን።እግዚአብሔር የምህረት እጁን ዘርግቶ በንስሀ እንድንመለስ በትግስት ይጠብቀናል። ከከንቱ የሐሰት ሕይወት ካልተመለስን ለእዉነትኛ ቅድስትና አገልግሎት እራስችን ላልሰጠን በቀር ከቁጣው ማምለጥ አንችልም።
    ት ኢሳ ም 1 ቁ 15
    እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል። በመጀምሪያ በመቅደስ ውስጥ ከመቆማችን በፊት ህይወታችንን በንስሐ ማጠብና በየዋህነት ራስን ዝቅ በማድረቅ መስዋዕቱን ለማቅረብ መዘጋጀት መንፈሳዊ ግደታችን ነው። ማንም አያየኝም እየተባለ ከመጋረጃው በስተጀርባ ወንጀል እሰራን በማስመሰል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርንን ማታለል አንችልም። እስት እግዚአብሔር ያሳያችሁ በየስፍራው በቤተ ከርስትያናችን ዛሬም ድብድብ የጡንቻ ማሳያና መሞከርያ ቦታ ሆኖዋል። ማነው እውነተኛ ምምህር ወይንም ሰባክ? ሁለም ለራሱ ዝና ክብር ነዋይ ነው በማስተማር የራስን ሀብት በአላፍው ምድር ላይ እያከማቸወን ነን። ከእግዚአብሔር ቁጣ ለመዳን ልባችንን በመስበር ለንስሐ መዘጋጀት ብቻ ነው። ቤተ ከርስቲያኛችንና ህዝቧ ከተከፋፈሉ እነሆ ድፍን ሦስት ሱባኤ አልፈናል። ሁሉም ዝም በማለት ከጌታችን ትዕዛዝና ሕግ ጋር የማይስማማ አገልግሎት በጥላቻ ውስጥ እያቀረብን ነንን።

    ReplyDelete
  2. God bless you the writer of this massage,unless the holy spirit helps you you cant post it, hope every Ethiopian with open hearts listen it,leave on it , may God bless Ethiopia, and Ethiopia will rise hands to God!!!

    ReplyDelete
  3. This is a good message to Ethiopian government and any other people or groups,God Bless you so much my friend;

    ReplyDelete