ዜመኛው ቅዱስ ያሬድ የዓቢይን ጾም ሳምንታት በሰየመበት ስያሜው፥ ይህን
ሳምንት መፃጉዕ ብሎ ሰይሞታል፡፡ ትርጓሜው በቁሙ ሲፈታ “ጐባጣ” ማለት እንደሆነ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(አለቃ) መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ
ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በሚለው መዝገበ ቃላቸው ገጽ 605 ላይ ፈትተውታል፡፡ ለስያሜው መሰጠት ምክንያቱ ደግሞ ቅዱስ ያሬድ የአጽዋማቱን
ሳምንታት ስያሜዎች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲወርሰው አድርጎታል፡፡ ይህ ስያሜም በምን ምክንያት ከጌታ ጋር እንደተገናኘ
ሲናገር እንዲህ አለ፦
“በሰንበት ቀን ኢየሱስ ታላላቅ ተአምራትን ያደርግ ነበር፡፡ ከዚህ
ሁሉ የሚበልጥ ያደረገውንም እናገራለሁ፡፡ ጭቃ ደህናውን ዓይን ያጠፋል፣ እርሱ ግን በምድር ላይ ተፍቶ ጭቃ አድርጎ ዕውር ሆኖ
የተወለደውን አዳነ፡፡ ይህ ግሩም ምስጢር ነው፡፡”
|
ቅዱስ ያሬድ ጌታ ድውያንን መጎብኘቱንና መፈወሱን በማስተዋል ያነሳል፡፡ ይህንንም
አጉልተው ከሚያወሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት በማንሣት በማሰናሰል ያዛምዳል፡፡ የዛሬ ዘመን እጅግ አብዛኛው አገልጋዮች ችግር የወንጌሉን
እውነት ከሰው ሕይወት ጋር አዛምዶ የማቅረብ ችግር ነው፡፡ የወንጌሉ ታሪካዊ ወይም ነገረ መለኮታዊው አውድ ከተተረከ በኋላ ከሰው
ሕይወት ጋር በማስተዋል ማዛመድ አማኙ ማድረግ የሚገባውን ነገር በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እንዲወስን እናደርገዋለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ
አማኙ በራሱ ወስኖ ማድረግ የሚገባውን እኛ ስለምንናገራቸው አገልግሎታችንን የሐሰት መምህራን አገልግሎት ያስመስልብናል፡፡ የሐሰት
መምህራን ዋና ጠባያቸው “እውነቱን በመናገር” አያርፉም ፤ ደቀ መዛሙርትን ወደኋላቸው በብዙ ለመሳብ ወደሕግ ያተኩራሉና፡፡ ቅዱስ
ጴጥሮስና ሐዋርያቱ የወንጌሉን እውነት በግልጥ በተናገሩ ጊዜ የሰሙት ሁሉ ወደእነርሱ መጥተው፥ “ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ?
አሉአቸው።” (ሐዋ.2፥38) ወንጌሉን ሰሚዎች በራሳቸው ማድረግ ያለባቸውን እስኪወስኑ ማገልገልና እንዲገባቸውም ከሕይወታቸው ጋር
በማዛመድ ማቅረብ የአስተዋይ አገልጋዮች ባህርይ ነው፡፡ቅዱስ ያሬድ የጌታን ትምህርቶች ሁሉ አውዳቸውን በመጠበቅ እጅግ ማዛመድ ይችልበታል፡፡
የስያሜው ዋና ታሪክ፥በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ
በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ በምትባልና አምስትም መመላለሻ በነበረባት አንዲት መጠመቂያ ሥፍራ ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ ስለታመመ
አንድ ሰው የሚተርክ ነው፡፡ ጌታ ወደዚህ ሥፍራ የመጣው በሰንበት ቀን ነው፡፡ በዚያም የመጠመቂያውን ቦታ ውኃ
የእግዚአብሔር መልአክ ባንቀሳቀሰው ጊዜ ቀድሞ በመግባት ለመፈወስ፦ “በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም
የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር።”(ዮሐ.5፥2)
ይህ ሰው የነበረበት በሽታ ከፍ ሲል የሥጋ ደዌ ወይም የሰውነት መስለል
ወይም ሽባነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከንባቡ እንደምንረዳውም ሰውየው እጅግ በጣም ተስፋ የቆረጠ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም እንደእርሱ
አይነት ሰዎች ውኃው በተንቀሳቀሰ ጊዜ ፈጥነው ገብተው መፈወስ የሚያስችል አቅም ወይም ዘመድ ሲኖራቸው እርሱ ግን አልነበረውም፡፡
ጌታችን ወደዚህ ሰው በመምጣት ነው ታዲያ ፦ “እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ፦ ልትድን ትወዳለህን?
ያለው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ነጋሪ የማያስፈልገው ሁሉን አዋቂ ነው፡፡
በዚህ ክፍል አንድ ልዩ ነገር እናያለን፡፡ ጌታ ብዙ ጊዜ ሲፈውስ የምናየው
ሰዎች እንዲያድኑት በጠየቁት ጊዜ ነው፡፡ በእርግጥ ሰውየው፥ “አድነኝ” ቢለው እንኳ የጌታ ኢየሱስ ጥያቄ ተገቢና ትክክል ነው፡፡
እርሱ መሻታችንን አስገድዶ የሚገባ አመጸኛ አይደለምና፡፡ ስለዚህም ጠየቀው፡፡ እግዚአብሔር ማናቸውንም ነገር በሕይወታችን የሚያደርገው ፈቃዳችንን በመጠምዘዝ
አይደለም፡፡ ፈቃዳችንን “ያከብራል”፡፡ አንፈልግህም ብንለው አያስገድደንም፡፡ ለመዳን ፣ ለማግኘት ፣ ድል ለመንሳት ፣ ለመዋጋት
፣ አብሮን ሊሆን እግዚአብሔር ሁልጊዜ ሙሉ ፈቃዳችንን ይሻል፡፡ እርሱ በእናንተ ሕይወት እንዲያዝ ፈቃደኞች ናችሁ? ፈቃዳችሁን እሺ
በ‘ጄ ብላችሁ ስጡት፡፡
ሰውየው ስለሁለት
ነገር እንቢ ሊል ይችላል ፤ (1) ቢፈወስ በልመና የሚተዳደርበትን የቀን ገቢውን ያጣል ፤ (2) ደግሞም የሚያድነኝ የለም ብሎ
ፍጹም ተስፋ ቆርጦ ሊሆን ይችላል፡፡ ጌታችን ለዚህ ነው፥ “ልትድን ትወዳለህን?” በማለት የጠየቀው፡፡ ለእኛም ዛሬ ይህ ጥያቄ ሲቀርብ ስንቶች ነን ከምንወደው ነገር ለመላቀቅ የምንሻ?
እናጣዋለን ብለን የምንፈራው ነገር የለም? ለጌታ ብቻ ብኖር ትዳሬን ፣ ሥራዬን ፣ ሥልጣኔን ፣ ፍቅረኛዬን ፣ ጓደኛዬን ፣ ዝናዬን
፣ ክብሬን ፣ ደመወዜን ... አጣለሁ ብለን የምሰጋ የለን ይሆን?
የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ ፍቅረኛውን ላለማጣት ብሎ ለብዙ ዓመታት “የእግዚአብሔርን እውነት ሲሠዋ ኖሯል”፡፡ እባካችሁ እኒህ ነገሮች ሁሉ
ከፊታቸው ምንም ቁጥር እንደሌለ የብዙ ዜሮዎች ድርድሮች ናቸውና ፈቃዳችሁን ለሚወዳችሁ ስጡት፡፡
ሰውየው ሁለተኛውን ምክንያት መረጠና፦ “ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ
በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።” (ቁ.7) ሰው
የለኝም ብሎ ተስፋ በመቁረጥ የሚኖር ሰው ነበር፡፡ ሰውየው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው 38 ዓመት መጠበቁ ይሆናል፡፡ በእርግጥ የዘመኑ
ርዝመት ነፍስን ያዝል ይሆናል ፤ ነገር ግን ታማኙ ጌታ በዙፋኑ አለ፡፡ ለዚህ ሰው ዙርያው ሁሉ ጨለማ ነው ፤ ጌታ ግን በዚህ ሁሉ
ውስጥ መጥቶ አጠገቡ ቆመ፡፡ የረዘመ መከራ ፣ እልህ አስጨራሽ ሙከራ ፣ ባለመድኃኒትቶች ሁሉ ያላወቁት የሕመም እንቆቅልሽ ፣ ዳኛ
ያጣመመው ፍርድ ... ደርሶባችሁ ዙርያው ሁሉ ገደል የሆነባችሁ አይዟችሁ አዳኙ በደጅ ነው፡፡
የሰውየው ናፍቆት ፈጥኖ ከውኃው በመግባት መፈወስ ነበር፡፡ ለዚያ ደግሞ
የሚረዳው ሰው የለውም፡፡ ይህ እጅግ የሚያም ነገር አለው ፤ ቀና ማለት ፣ ከሰው እኩል መቆም ፣ መፈወስ ፣ መዳን ፣ ከመከራ መውጣት
መሻቱ ቢኖረውም ... በኢየሱስ ላይ ያለው እምነት ደካማ ነበር፡፡ እንዲያው ከፈወሰውም በኋላ እንኳ ጌታን አያውቀውም፡፡ ጌታ ግን፦
“ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ።”
ጌታ ብዙ በሽተኞች በዚያ ቢኖሩም የሄደው ግን ምንም ሰው ወደሌለው ወደዚህ
አንድ ሰው እንደሆነ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ በእርግጥም እርሱ፦“ለድሃ አደጉና ለመበለቲቱ ይፈርዳል፥ መብልና ልብስም ይሰጠው ዘንድ
ስደተኛውን ይወድዳል።” (ዘዳግ.10፥18) “ለድሀ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ።” ፤ “እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥
ለባልቴቶችም ዳኛ ነው።” (መዝ.10፥14 ፤ 68፥5) “ ... መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፥ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፥
እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፦ ...” (ሚል.3፥5) አዎ! እግዚአብሔር ሰው ለሌላቸው ሰው ሆኖ በሥጋ የተገለጠ ነው፡፡ ሰው ለናቃቸውና
ለገፋቸው ፣ ሰው ለሚጠየፋቸው ፣ ጐባጣና ድውይም ... እርሱ የድሆች አምላክ ነውና ከመከራ ሁሉ ያድናቸዋል ፤ ይሟገትላቸዋልም፡፡
እኛም ይህን እውነት ከክርስቶስ ተምረናል፡፡ (1ጴጥ.2፥21)
አዎ! ዛሬ አገራችን ኢትዮጲያ እንዲህ ያለ ሰው እጅግ ያስፈልጋታል፡፡
ብዙዎች ሰው አጥተው እንባቸውን እየዘሩ ነው፡፡ በቤተ መንግሥትም ሆነ በቤተ ክህነት ዘርና ብሔራቸው ተጠንቶ ሥራ ያጡ ፤ ዘመድና
ወገን ስለሌላቸው ብቻ እውነት ቢኖራቸውም ፍትሕ ያጡ ፣ ያልተያዘው ዋና ሌባ የሚያሳድዳቸው ብዙ ንጹሐን ፣ ረሃብና ጥም በከተማውና
በገጠሩ የሚያረግፋቸው ፣ በርበሬ ብለው ቀይ አፈርና ባዕድ ነገር
ቀላቅሎ በሸጠላቸው ነጋዴ ተጭበርብረው ጤናቸውን ያጡ ፣ በባለ መድኃኒት ቤቶች ጤናቸውንም ገንዘባቸውንም የተዘረፉና ያጡ ፣ ጉቦ
ስላልሰጡ የተፈረደባቸውና ፍትሕ ያጡ ፣ በፖሊስ አካላቸው የጎደለባቸው ፣ የሚያለቅሱቱና የሚያነቡቱ ሁሉ ሰው የለንም እያሉ ኢትዮጲያችን
የሰው ያለህ ትላለች፡፡ ዘር ፣ ቀለም ፣ አጥንት ፣ ወንዝ ፣ ድንበር ፣ ጎሳ ፣ ነገድ የማይቆጥር ከዚህ የተዋጀ ሰው ኢትዮጲያችን
ትሻለች፡፡ ልጆችዋን በአንድ ታዛ የሚሰበስብላትን ሰው ፤ ሰው ሆይ ትፈልጋለችና ማን ይሆን የሚገኝላት?!
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ሰውየው ጌታን እንኳ ባያውቀውም ጌታ ኢየሱስ
ግን በበሽታው ላይ ያለውን ፍጹም ሥልጣን አሳይቶናል፡፡ ጌታ ኢየሱስ
በሁሉ በሽታዎች ላይ ሥልጣን አለው፡፡ ሰውየው ባያውቀው እንኳ ጌታችን ከደዌው ሁሉ ፈውሶታል፡፡ ውለታን ሳይጠብቅ ፈወሰው፡፡ እናንተስ
ለሰዎች መልካምን ነገር የምታደርጉትና ሰው ለሌላቸው ሰው የምትሆኑላቸውን የራሳችሁን ማንነት ከዘረዘራችሁ ፤ ነጋሪት ካስመታችሁ
መለከት ካስነፋችሁ በኋላ ነውን? ወይስ እንደኢየሱስ ባያውቋችሁም የምታደርጉ ናችሁ? እባካችሁ ለኢትዮጲያችን ሰው ሁኑላት ፤ ሰው
ስትሆኑላትም ዘር ፣ ቋንቋ ፣ ነገድ ፣ ሃብት ፣ ሥልጣን ፣ ዝና ... አትዩ! ይልቅ ለተጠቃውና ለድኃው ፤ የሰው ያለህ እያለ
ለሚጮኸው ድረሱለት፡፡ ተምዋገቱለትም፡፡
ጌታ ሆይ ሰው
የሌላቸውን ሰው እንድንሆንላቸው ማስተዋልን አብዛልን፡፡ አሜን፡፡
ተባረክ
ReplyDelete