Tuesday 1 December 2015

የኖድ ምድሩ ሰው (ዘፍጥ.4፥16)

     

    እግዚአብሔር ፍጥረትን ከፈጠረበት ጥበብ በሚልቅ ጥበብ፥ የሰውን ልጅ ፈጠረው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንደሚሉትም ሌሎቹን በቃልና በዝምታ ሲፈጥር ሰውን ግን “በእጁ አበጅቶ ግብር እምግብር” ፈጠረው ይሉናል፡፡ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም፥ ሰው እጅግ በታላቅ ክብርና ሞገስ መፈጠሩን ይናገራሉ፡፡ (ዘፍ.1፥27 ፤ 2፥7 ፤ መዝ.139፥14 ፤ 145፥10) ዕለትም ዕለትም ከእግዚአብሔር ጋር እጅግ የሚያስደንቅ ንግግርና ጨዋታ ያደርግ እንደነበርም ታላቁ መጽሐፍ ሲነግረን ልባችን እጅግ መደመሙና እጁን በአፍ ጭኖ መደነቁ አይቀርም ፤ ትልቁ ጌታ ከፍጡሩ ጋር ዕለት ዕለት እንደመነጋገር የሚያስደንቅ ምን አለ!? (ዘፍጥ.3፥8)
     ታላቁ መጽሐፍ፥ ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድንና ሁለትን እጅግ የሚደንቅ ትስስር ከአምላኩ ጋር እንደነበረው የሚነግረን ብዙም ሳይርቅ በሦስተኛው ምዕራፍ አሳዛኙን ውድቀት ይነግረናል፡፡ ዔደን ገነት ልዩና የእግዚአብሔር ሠላም የሰፈነባት ሆና ለሰው ልጅ የተሰጠች ፤ እንዲሁም የሰው ልጅ ቅዱስና ጻድቅ እግዚአብሔር ራሱን በሚገልጥበት በኪሩቤል አጠገብ መኖር እንዳልሆነለት ፥ በኃጢአት ምክንያት ሁከት ፣ ፍርሃት ፣ ሽሽት ፣ ዔደን ገነት ጭንቀት የሰፈነባት ሆና ሰው ማረፊያ ሲያጣባት እናስተውላለን፡፡  ኖድ ማለት የስሙ ትርጓሜ መቅበዝበዝ ማለት ነው፡፡

      እግዚአብሔር ሰው በእርሱ ዘንድ ከእርሱ ጋር እንዲኖር ቢወድም ፥ ሰውን የመምረጥ ነጻነቱን አልከለከለውም፡፡ ምርጫዎቻችንን ከወደድን የመረጥነው ምርጫችን ውጤቱንም የመቀበል ግዴታ አለብን ፤ ሰው በምርጫው ከፈጣሪው ተለየ፡፡ ስለዚህም የምርጫውን ውጤት ተቀብሎ ፍርድ ከአምላኩ ተላለፈበት፡፡ እግዚአብሔር ከፍርድ በኋላ እንኳ ሰውን መጣልና መተው ፤ ለጠላትና ለራሱ ፈቃድ አሳልፎ መስጠትን አልወደደም፡፡ ስለዚህም ባሳተው ጠላቱና በእርሱ መካከል ጠላትነትን አኖረ ፤ ከፊቱም እንዲርቅ አልወደደም ማለት ነው፡፡(ዘፍጥ.3፥15)
      ሰው ምንም እንኳ የወደቀ ፤ በማመጽ ያልታዘዘ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ግን ፈጽሞ ከፊቱ አልጣለውም ፤ ላያየውም አልጠላውም ፤ ራራለት እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ሲቀጣውም እንኳ፥ ከፍቅር ባህርይው ፈጽሞ ሳይለይ ነው፡፡ እግዚአብሔር የራራለት ሰው ግን ይህን ርኅራኄ ቸል ብሎ ሌላ ከባድ ስህተትን ሲሠራ እናያለን፡፡ “ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ።” (ዘፍ.4፥16) ይለናል ታላቁ መጽሐፍ፡፡
     “ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ” የሚለው ቃል፥ ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ለማፈንገጥ ማሰቡንና ፤ በእግዚአብሔር ቁጥጥርና ዓይኖች ለዘወትር መታየትን መጠላቱን የሚያመለክት ድርጊት ነው፡፡ ቃየል በዳይና ነፍሰ ገዳይ ቢሆንም ይኖር የነበረው ግን በእግዚአብሔር ፊት ነበር፡፡ በጥንት ሞገስ ያላገኙ (ሚስትም ብትሆን) ሰዎች በንጉሥ ፊት ያለመቆም ልማድ አለ ፤ ሞገስን ሲያገኙ ግን ንጉሡ ሞገስን ይሰጣቸዋል፡፡ (አስ.4፥11 ፤ 5፥2) ይህም በፊቱ ሞገስን ማግኘት ማለት መወደድን ፣ መደመጥን ማግኘት ማለት ነው፡፡
       በእግዚአብሔር ፊት ደግሞ፥ በእግዚአብሔር ፊት መሆን ማለት ሞገስ ማግኘትን ያመለክታል ፤ “ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ የበፍታ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር፡፡” (1ሳሙ.2፥18)ሲል ፥ ሕጻኑ ነቢይ ቅዱስ ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት የካህናቱን ልብሰ ተክህኖ በፍታ ኤፉድ ለብሶ በሞገስ አገልጋይ ነበር፡፡ በሌላ ሥፍራም፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ” (ሉቃ.1፥19) ሲል፥ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሞገስና በባለሟልነት በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም መሆኑን ያሳያል፡፡ ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ፊት ውብ መወደድ ነበራት፡፡(ሉቃ.1፥30) ይህም ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት መሆን ማለት ኃጢአትን ፈጽሞ መጠየፍም ነው ፤ ቅዱስ ዮሴፍ እንዲህ አለ፦ “… በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?” (ዘፍጥ.39፥9) በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን በመጠየፍ መሆንን ወድደን ይሆንን?!
      ቃየል እግዚአብሔር እርሱን ካስቀመጠበት ከዔደን ገነት ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በኖድ ምድር መቀመጥን ፈለገ፡፡ በዚህም አለመታዘዙን አሳየ ፤ መታዘዝን ማሳየት ቢፈልግ ኖሮ እግዚአብሔር እርሱን ዘወትር ሊያገኘው በወደደው ሥፍራ መገኘት በቻለ ነበር፡፡ ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ተፈጥሯልና ለእግዚአብሔር የመገዛት ወይም እግዚአብሔርን የማምለክ ወይም እግዚአብሔርን የመፍራት ልማድ አለበት፡፡ ከእግዚአብሔር ፊት ሲነሳ ፥ ተነስቶም ሲወጣ እግዚአብሔርን ለማምለክ ፤ ለእግዚአብሔር አለመገዛትን ፈልጓል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔርን ማምለክ ባልፈለገበት አቅሙ ልክ ሌላውን ባዕድ ነገር ያመልካል ማለት ነው፡፡
      በሌላ አነጋገር ከመገዛትና ከማምለክ ነጻ ያልሆነው ሰው ለእግዚአብሔር አልሸነፍ ባለው መጠን ልክ ፥ ከራሱ ለሚያንሰው ነገር መገዛቱ ግድ ነው፡፡ ሰው ሌላውን አመለከ ማለት ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እግዚአብሔርን መቃረንና መቃወም ውስጥ ገብቷል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርን ሲቃወም ደግሞ በራሱ ምርጫ መደሰትና መርካትን መርጧል፡፡ ስለዚህም “ብርድ ነበረና ባሮችና ሎሌዎች የፍም እሳት አንድደው ቆሙ ይሞቁም ነበር፤ ጴጥሮስም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር።” (ዮሐ.18፥18) እንዲል ከእግዚአብሔር ውጪ የሆነውን ነገር መምረጥ ይጀምራል፡፡
   በኖድ መኖር የጀመረው ሰው ጣዖትን ማምለክ ጀመረ፡፡ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ተቃወመው፡፡ የኖድ ምድር ነዋሪ መሆን ከእግዚአብሔር ፊት ለጊዜው መሸሻ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ፍጻሜው ፈጽሞ የማያምርና የዘላለም ቅጣት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ለዘወትር አለመሆን ፤ ከእግዚአብሔር ፊት መውጣት ለሞትና ለኃጢአት አሳልፎ ይሰጣል፡፡ በእውነት ፊቱን ልንፈልግ ይገባናል እንጂ ከፊቱ መሸሽ አይገባንም ፤ ከፊቱም መውጣት አይገባንም፡፡
     በእግዚአብሔር ፊት መኖር ለእግዚአብሔር መታየት ፣ መራቆት ፣ መገለጥ ፣ መናዘዝም ነው፡፡ እንደኖድ ምድር ኗሪ ከእግዚአብሔር ፊት መውጣት ግን ራስን ለክፉ ጠላት አሳልፎ መስጠትና እግዚአብሔርን በራስ ምርጫ መቃወም ነው፡፡ እኛስ የት ነን? በእግዚአብሔር ፊት በእርሱ ቁጥጥር ሥር ለመሆን ወደን ፈቅደን ነው ወይስ በራሳችን ደስታ ማግኛ በመሰለን መንገድ በሥካር ፣ በዝሙት ፣ በሴሰኝነት ፣ በዘፈን ፣ በጣዖት አምልኮ ፣ በግብረ ሰዶም ፣ ከሚጭበረበርበት ንግድ ምድር ላይ ሆነን ነው ያለነው? የትነው ያላችሁት ለሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት በዔደን ገነት ወይስ በኖድ ምድር በኃጢአቱ ሥፍራና ከእግዚአብሔር ፈቃድና ቁጥጥር ሥር በመራቅ?

ጌታ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡ 

1 comment: