Friday, 11 December 2015

ወንድሜ ማን ነው? (ክፍል ሁለት)

     

     ቃየን በልቡ ያሰላሰለውን ኃጢአት ከፍጻሜ ማድረስ አድብቷል፡፡ “ኃጢአተኞች እነሆ ቀስታቸውን ገትረዋልና፥ ፍላጻቸውንም በአውታር አዘጋጅተዋልና፥ ልበ ቅኖችን በስውር ይነድፉ ዘንድ።” (መዝ.10፥1) እንዲል ልበ ቅኑን አቤልን ይነድፍ ዘንድ ቃየን በስውር ይናደፍ ዘንድ ተነሳ፡፡ ስለዚህም፥ “ቃየንም ወንድሙን አቤልን፦ ና ወደሜዳ እንሂድ አለው።” ልምድ ያላቸው ወንጀለኞች “ትልቁ ክፋታቸው” ወንጀሉ እንዳይታወቅና ፤ እውነተኛ ፍርድ እንዳያገኙ የምስክር ደብዛ ያጠፋሉ፡፡
       ቃየን ወንድሙን “ወደሜዳ እንሂድ” ያለው አብሮት ሊጫወት ፤ እንደወንድምም ሊያወጋው አይደለም፡፡  አቤል ግን ወንድሜ እንዲህ ያደርግብኛል ስላላለ አብሮት ሄደ፡፡ ለዳኝነት ብይን መስጫው ቁልፉ ምስክር ወይም ማስረጃ ነው፡፡ ቃየን ያለምስክር “በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም።” (ዘፍጥ.4፥8) የጨለማ ሥራ ካልተሸሸገ በቀር ብቻውን መቆም አይችልም፡፡ “የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ።” (ዮሐ.8፥44) እንደተባለ የዲያብሎስን ፈቃድ ሊያደርግ እግሩን አስቸኰለ፡፡ ኃጢአተኞች ትልቁን ምስክር ህሊናቸውን ዘንግተው የሰው ምስክር ይሸሻሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁሉን ያያል!!!

       አይቶም ፤ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” (ዘፍጥ.4፥9) አለው፡፡ እግዚአብሔር ቃየንን እያወቀ እንዳላወቀ ሆኖ የቀረበው በፍቅር ልብ ነው፡፡ ቃየን ግን የመለሰው መልስ ልብ ያደማል ፥ “አላውቅም የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?” (ቁ.9) ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ ራሱን ከኃላፊነት ነጻ ሊያደርግ ዳዳው፡፡ ቃየን በንግግሩ አሽሙረኛም ነበር ፤ “የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?” ሲል የአቤልን የበግ ጠባቂነት እጅግ የነቀፈም ይመስላል፡፡ ወንድሙን መግደሉ ሳያንስ “በሟች ወንድሙ” ላይ ያሽሟርራል፡፡ መጽሐፍ “ከሞተ ሥራ ሕሊናችንን እናነጻ ዘንድ” በእጅግ ይመክረናል፡፡ የሞተ ሕሊና ለጭካኔውና ለክህደቱ ድንበር የለሽ ብቻ ያይደለ አለመራራቱ እጅግ ይደንቃል!!!
      ቃየን አብሮ መኖርን “ገደል ግባ” አለው፡፡ አቤልን ከፊቱ ገለል በማድረጉ ሠላማዊ የሚሆን መስሎት ነበር ፤ ነገር ግን ውድ ወንድሙን ሲገድል ደም አፈሰሰ ፤ በፈሰሰው ደም ምክንያት ምድር ፊቱን ነፈገችው ፤ ፍሬን አልሰጥህ አለችው ፤ ንስሐን ጠልቷልና ከእግዚአብሔርም ከሰውም ፊት ወደኖድ ምድር ሊኮበልል ተነሳ፡፡ አንዱን ወንድሙን ገድሎ መላ ቤተሰቡን አጣ፡፡ በተጨማሪም ምናልባት ቃየን በራሱ እጅ ሥራ የተመካን ሰው ይመስላል ፤ ግና እግዚአብሔር በሰው እጅ ሥራ፥ በመልካም ምግባሩም ቢሆን ሊረካ እንደማይችል በግልጥ ተናግሯል፡፡ (ኢሳ.64፥6) አቤል ደግሞ የክርስቶስን መሥዋዕትነትና አዳኝነትን አሻግሮ ከሩቅ ያየ ይመስላል ፤ ለዚህም መሥዋዕት ሊሆን ያለውን በግ አቀረበ፡፡
       ቅዱስ መጽሐፍ አቤል ለቃየን ወንድሙ እንደነበረ እንጂ ቃየል ለአቤል ወንድሙ እንዳልነበረ ይነግረናል፡፡ ቃየን ወንድሙን መጠበቅ ፤ ለወንድሙም ወንድም መሆን ነበረበት ግን አልሆነም፡፡ እግዚአብሔር አቤልን አደመጠው ፤ ቃየንንም የአቤል ወንድምነቱ ትዝ እንዲለው ደጋግሞ ወደእርሱ መጥቶ “ምን አደረግህ?” ቢለው ቃየን ፍጹም ሕሊናው ዝግ ነበር፡፡
     እኛ ለእናታችን ልጅ ወንድም ነን? እንዳያዝንብን ፣ እንዳያለቅስብን ፣ እንዳይራብብን ፣ እንዳይታረዝብን ፣ በመንፈሱ እንዳይቅበዘበዝብን … እንጠብቀዋለን? በእውኑ እኛ ለሃይማኖት ቤተ ሰዎቻችን ወንድም ነንን? …
ለዮሴፍ ከ“ወንድሞቹ” ወንድም የሆነው ማን ነው?

     ያዕቆብ ከአንድ አብራኩ የወጡት ልጆቹ ዥንጉርጉር ሆነውበት በጣም ተቸግሯል፡፡ እጅግ በጣም እንደነፍሱ ከሚወዳት ሚስቱ ራሔል፥ የወለደውን ዮሴፍን እርሱ አብልጦ ቢያቀርበው[1] ፥ “ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንዲወደው ባዩ ጊዜ ጠሉት፥ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም።” (ዘፍጥ.37፥4) የዮሴፍ ወንድሞች ወንድማቸውን ለመጥላት ምክንያታቸው ይህ ብቻ ሳይሆን በተለያየ ሁለት ጊዜ ያየውን ሕልም ለእነርሱ መናገሩም እጅግ አበሳጭቷቸዋል ፤ “እንደገና በብዙ ጠሉት።” ፤ “እንደገናም ስለሕልሙና ስለነገሩ ይልቁን ጠሉት።” (ቁ.5 እና 8)
     ቅዱስ ያዕቆብ የዮሴፍን ነገር ችላ አላለውም ፤ ድንግል ማርያም ሁሉን በልቧ እያሰላሰለች በክርስቶስ ኢየሱስ ሕይወት ይሆን የነበረውን ትጠብቅ እንደነበረው ያዕቆብም እጅግ ይጠብቀው ነበር፡፡ (ዘፍጥ.37፥11 ፤ ሉቃ.2፥19 ፤ 51) ዮሴፍ ባለመብሰሉና በወንድሞቹ ላይ ከፍ ከፍ ለማለት በማሰቡ ቢሳሳትም፥ እግዚአብሔር ግን ስለአላማው ለዮሴፍ እጅግ ይጠነቀቅለት ነበር፡፡ ዮሴፍ በወንድሞቹ መካከል መከበርን እጅግ የወደደ ይመስላል ፤ ምላሹ ግን ፍጹም ጥላቻ ነበር ፤ አባቱ እንኳ በኋላ ላይ ነገሩን በልቡ መጠበቅ ጀመረ እንጂ መጀመርያ ላይ በተግሳጽ ቃል ተናግሮት ነበር፡፡
     እግዚአብሔር በወንድሞቹ መካከል መክበር የፈለገው ዮሴፍን “የግብጽ ሁሉ መሪ” ሊያደያርገው ከወንድሞቹ መካከል ገፋው ፤ ወንድሞቹ ትንሹን ከለከሉት፥ እግዚአብሔር ግን ትልቁን አየለት፡፡ ከመካከላቸው ሲያስወግዱት ባርያ ሆኖ ይኖራል ብለው ነበር ፤ እግዚአብሔር ግን በገፉት መጠን ከፍታውን አበዛው፡፡ ሰዎች ብድራታችሁን ክደው ፤ እጅግ የምታምኗቸው ጀርባቸውን ሲሰጧችሁ ፤ ያጐረሳችሁት ምላስ ሲነክሳችሁ … ምን ታስባላችሁ? … ወደከፍታችሁ እየገፋችሁ ነውና በጸሎት ልብ በልባችሁ ጠብቁት፡፡
ይሁዳ ተሳሳተ ፤ ተገበዘም ፤
    ያዕቆብ በቤት ያለ ልጁ ዮሴፍን፣ በሴኬም በጐች ይጠብቁ ያሉት ልጆቹ ደህና ስለመሆናቸው ወሬ ይዞለት እንዲመጣ ላከው ፤ ልጁም እሺ ብሎ ለአባቱ ታዞ ወንድሞቹን ፈልጎ አገኘ፡፡ ገና ከሩቅ ሳለ “የሕልሙ አለቃ” መጣ ብለው አሽሙረውበት፥ ሊገድሉት ተማከሩበት፡፡ ከዚህ ምክራቸው ሮቤል አስጣላቸው፡፡ ስለዚህም ቀሚሱን ገፈው ውኃ በሌለበት ጉድጓድ ውስጥ ጥለውት ምግባቸውን ተቀምጠው መብላት ጀመሩ፡፡ እኒህ “ወንድሞች” ምን አይነት ደንዳና ልብ ነው ያላቸው!?
       ምግባቸውን እየበሉ ሳለ ከሩቅ አሻግረው ሲያዩ እስማኤላውያን ነጋዴዎችን አዩ፡፡ በዚህ ጊዜ ይሁዳ፦
1.    ወንድሙ እንዲሸጥ የመጀመርያውን ሃሳብ አቀረበ ፤
      የይሁዳ ታሪክ በውድቀት ፤ የውድቀቱ ታሪክ ደግሞ የዮሴፍን ታሪክ በማቋረጥ ይጀምራል፡፡ የዮሴፍ መሳጭ ታሪክ በይሁዳ አሳዛኝም አስደናቂም ታሪክ ይቋረጣል፡፡ ለዮሴፍ የመሸጥን ሃሳብ ለመጀመርያ ጊዜ ያቀረበው ይሁዳ ነው፡፡ ወንድሞቹንም በአንድ አስማማ ፤ ወንድሞቹ ከሮቤል ይልቅ ይሁዳን ሰምተዋል፡፡ ሮቤል በዮሴፍ ክፉ እንዳይደርስ ቢጥርም ይሁዳ ግን የወንድሞቹን ልብ በወንድማቸው ላይ አነሳሳ፡፡
     ዮሴፍ ይህን የይሁዳን ሃሳብ ያውቃል፡፡ ይሁዳ የእንሽጠው ሃሳብ እንዳቀረበም ያስተዋለም ይመስላል፡፡ ወንድማማችነት ሲከፋ እንደማየት ልብ የሚያደማ ምንም ነገር የለም፡፡ “በማማጠን ነፍሱ እየተጨነቀች አይተውት” (ዘፍጥ.42፥21) ከመስማት ቸል አሉት፡፡ ይሁዳ በወንድሙ መሸጥ የተስማማ ብቻ ሳይሆን ለመሸጡ ዋና ሃሳብ አመንጪ ነው፡፡
2.   ዮሴፍን ወደግብፅ ወሰዱት … ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ወረደ ፤

    ዮሴፍ ወደግብጽ የወረደው ተገዶ በባርነት ተሸጦ ነው፡፡ የዮሴፍን የቅድስና ሕይወት እየነገረን የነበረው መጽሐፍ፥ የይሁዳን ፍጹም መውደቅና መርከስ ደግሞ በአዲስ ትርክት ይጀምርልናል፡፡ ዮሴፍ በተሸጠበትና በግድ ወደግብጽ በወረደበት ወራት ይሁዳ በገዛ ፈቃዱ ወደዓዶሎማዊው ሰው ቤት ገባ፡፡ በዚያም ከከነናዊት ሴት ጋር ተኛ፡፡ [2]
3.   የይሁዳ ፍጹም ግብዝ ፍርድ ፤
      ይሁዳ ከከነናዊቷ ሴት ሦስት ወንዶች ልጆችን ወለደ፡፡ ለመጀመርያ ልጁ ለዔርም ትዕማርን አጋባው ፤ ስለትዕቢት ክፋቱ ፣ ሁለተኛም ልጁ ወደወንድሙ ሚስት ቢገባም ፤ እርሱም ስለምቀኝነቱ እግዚአብሔር ቀሰፈው፡፡  ይሁዳ ሦስተኛ ልጁን ወደልጆቹ ሚስት ማስገባት ትቶ እርሷን ወደቤቷ ሸኛት፡፡
    ከብዙ ጊዜ በኋላ የይሁዳ ሚስት ሞተች ፤ ከተጽናና በኋላ በጐችን ሊሸልት ወደተምና ሊወርድ እንዳለ ትዕማር ሰማችና ጋለሞታ ልብስ ለብሳ በመንገድ ላይ ጠበቀችው፡፡ እርሷንም ለምኗት ወደእርሷ ገባ፡፡ እርሷም መያዣ ይዛ ተገናኘችው፡፡ ከሦስት ወር በኋላ መጽነስዋን ሲሰማ፥ “አውጡአትና በእሳት ትቃጠል” ብሎ ግብዝ ፍርድን ፈረደ፡፡ (ዘፍጥ.38፥24)
     ይሁዳ ወደቀ ፤ ከመውደቅም ዘቀጠ፡፡ ግብዝ ሆኖም በራሱ ፈረደ፡፡ እንዲህ ያለ ታሪክ በዳዊትም ሆኖ ነበር፡፡ (2ሳሙ.12፥5) በፈረደበት ፍርድ ተያዘ ፤ ፍርድን በአንደበቱ ተናገረ፡፡ ሴቲቱ ከእርሱ የተሻለች ጻድቅት መሆኗን አምኖ ተቀበለ፡፡ ከትልቅ ውድቀት በኋላ ወደልቡ የተመለሰ ይመስላል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች የሰዎች የተገለጠን ነውር በቅን ልብና ለንስሐና ሌሎች እንዲማሩበት ሲገለጥ እጅግ በጣም ይቆጣሉ፡፡ አምናለሁ ፤ ሁላችንም ንጹሐን አይደለንም፡፡ ንጹሐን አይደለንም ማለት ግን ከኃጢአት ጋር ተመቻምቸንና ተደላድለን ፤ ተስማምተንም እንቀመጣለን ማለት አይደለም፡፡ እንደቅዱስ ቃሉ በአገባቡና በግልጥ መነቀፍና መገለጥ አለበት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የይሁዳን የውድቀት ታሪክ በዮሴፍ ታሪክ መካከል ለምን አመጣው? ይህንን መመርመር ለያዝነው የመማማርያ ርዕስ ትልቅና ድንቅ ነጥብ ይሰጠናል፡፡
     እግዚአብሔር የነገር መጨረሻን ያያልና በንስሐ ብዙ ይታገሰናል፡፡ ሰው የሰው መጀመርያ እንጂ ፍጻሜን አያይምና ስንፍናን ያወራል፡፡ በእርግጥም፥ “የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል” (መክ.7፥8) ተብሏልና ለእግዚአብሔር ቅድስና ስንተጋ ፤ ኃጢአትን በአገባብ መግለጥንም አንዘንጋ፡፡ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡





       [1] ቅዱስ ያዕቆብ ዮሴፍን እጅግ ማቅረቡን ከሚያሳየን ድርጊት አንዱ “በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት።” የሚለውን ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህም ለእርሱ ልዩ ፍቅር እንዳለውና እጅግ እንደሚወደው ያሳያል፡፡ በእርግጥም እንዲህ ያለውን ልብስ ይለብሱ የነበሩት “ብዙ ኅብር ያለውንም ልብስ ለብሳ ነበር፥ እንዲህ ያለውን ልብስ የንጉሡ ልጆች ደናግሉ ይለብሱ ነበርና” እንዲል የንጉሥ ደናግላን ልጆች ናቸው፡፡ (2ሳሙ.13፥18) በዚህም ሌሎቹ ልብስ እንዮሴፍ ያይደለና እጅግ የሚበልጥ ልብስ ማልበሱን ያሳያል ፤ የዚህ ልዩ ሞገስ ውጤቱ በክፉ መጥላትና በክፉ ቅንአት እንዲጠሉት ሆነ፡፡
     [2] ይህ የይሁዳ ውድቀት ፍጹም አጸያፊ ነው፡፡ ከዮሴፍ ጋር ሲነጻጸር ዮሴፍ ጻድቅ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሌላው ደግሞ ማንም፥ የእግዚአብሔር ወገንና ሕዝብ ቢሆን እንኳ ኃጢአቱ መገለጡ እንደማይቀርም እናስተውለለን፡፡

No comments:

Post a Comment