Friday, 18 December 2015

ግጭትና ጦርነት የማያስተምራት አገር



ስለራሳችን እንዲህ እንናገራለን ፦
-      እንግዳ ተቀባይ ሕዝቦች ነን ፤
-      ብዙ ብሔር ብሔረሶችና ሕዝቦች ተዋደው የሚኖሩባት አገር አለን ፤
-      ለቁጥር የሚታክት “ክርስቲያን” ፣ እልፍ አዕላፍ ገዳም ፣ መድረክ የሚያጨናንቁ አገልጋይ ጳጳሳት ፣ ካህናት ፣ ዲያቆናትና ዘማርያን አሉን ፤
-      ከእኛ ወዲህ ማን አለ አማኝ? ከእኛ በላይ ጸዳቂ ፤ ታማኝ አገር ወዳድ ወዴት አለ?! …
ስንታይ ግን፦
-      “ባዕድ እንግዳ” ለመቀበል ሆዳችንን እንደአገር ስናሰፋ ፥ ከጎረቤትና ከወገናችን ጋር ግን “ጠብ ያለሽ በዳቦ” በሚል መንፈስ የተያዝን ፤
-      አገልጋዮቻችን ጸንሰው ወልደው ፣ አሳድገው የሰጡን አንዱ መልክ ዘረኝነትና ልዩነት ነው ፤
-      ከእኛ በላይ ሁሌም ሰው የለም ብንልም ዘወትር ግን እየኖርን ያለነው ከሰው በታች ጅራት ሆነን ነው …
     ሰሞኑን በከፊል የአገራችን ክፍል ብጥብጥና ሁከት ፤ ደም ማፍሰስና ግድያ ነግሶ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ አድራጊው ሌላ ወራሪ ወይም እንግዳ አሸባሪ መጥቶብን አይደለም ፤ ሟችም እኛው፥ ገዳይም ያው እኛው ኢትዮጲያውያን ፤ ንብረት አውዳሚም፥ ንብረት የሚወድምበትም ያው የአንድ አገር ዜጎች ፤ የአንድ ርስት ወሰንተኞች ፤ የአንድ ወንዝ ጠጪዎች እኛው ነን፡፡
      እስኪ አስተውሉ፥ አንድ መቶ ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በእኛና እኛ መካከል የተደረጉ ጦርነቶችን ብናነሳ፦ በ1909 ዓ.ም በራስ ተፈሪና በንጉሥ ሚካኤል መካከል በሰገሌ ፣ በ1922 ዓ.ም በራስ ተፈሪና በራስ ጕግሳ በአንቺም ወይም በበጌምድር ፣ ከ1966-1983 ዓ.ም ወታደራዊው መንግሥት ደርግና ኢሕአዴግ በተለያየ ቦታ ያደረጉት አስቀያሚ ጦርነት ፣ በ1994 ዓ.ም ሁለቱ “ወንድማማች” ኢትዮጲያና ኤርትራ ያደረጉትን ጦርነት (ወታደራዊው መንግሥት በአንድ ጉድጓድ የፈጃቸው የንጉሡ ዘመን መሪዎችና ሌሎችም ሳይካተቱ) ይህን ሁሉ ስናነሳ ምን ይታወሰናል?!

     በእውኑ እኛ ነን ተቻችሎ አዳሪ? እኛ ነን ለእግዚአብሔር ቀናተኞች? ከእኛ በላይ አማኝ ፤ ከእኛም ወዲያ ክርስቲያን የሚባልልን በእውነት እኛ ነን?! እኔ የፖለቲካ ተንታኝ አይደለሁም፥ ዳሩ ይህን አምናለሁ ፤ ማርቲን ሉተር ኪንግ ፣ ማኅተመ ጋንዲ ፣ ታዋቂው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ጦር ሳይመዙ ፣ የጥይት ባሩድ ሳያጤሱ ለሕዝቦቻቸው ነጻነትን ያጎናጸፉ ምርጥ የነጻነት ታጋይ ተምሳሌቶች ናቸው፡፡ እኒህ መሪዎች ከሕዝባቸው እኩል መከራ ተቀብለዋል ፣ ተርበዋል ተጠምተዋል ፣ በእስር በግርፋት ተሰቃይተዋል ፤ በፍጻሜው ግን ዘረኞችን ድል አድርገዋል፡፡
      እኒህ የነጻነት ሰዎች ከንግግራቸው ይልቅ ከሕዝባቸው ጋር ያሳለፉት መከራና ሰቆቃ ረጅም ነው፡፡ ለወሬ የግል ተከታይና ደጋፊ የግል ቻናል አልከፈቱም ፤ ሕዝብ በአመጽ ለመቀስቀስ በስውር አልተመሳጠሩም ፣ ከሕዝቦቻቸው ርቀው በዲያስፖራነት እየተቀማጠሉ ኖረው፥ በየሚዲያው ተውበው አልቀረቡም ፣ እኩል የሕዝባቸውን መከራ በመቀበል ኖሩ እንጂ፡፡
     ወደአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ በአንድ መቶ ያሳለፍነው ጦርነት ምን አስተምሮናል? እርስ በእርስ ያን ያህል ተጋጭተን የት ደረስን? የገዛ ወንድማችንን ገድለን እርካታችን ምንድር ነው? … ገድለን ካልተማርንበት አሁንስ ለመግደል መነሳሳት ምን የሚሉት ድንዛዜ ነው? ነጻነት እፈልጋለሁ የሚል አካል ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ምን ያጣባዋል? አንድ ብሔር ወይም የተወሰኑ ብሔሮች ላች ላይ ችክ ማለትስ? የነጻነት ታጋይ ነን ካሉ ብዙ ሃይማኖትና ብዙ ብሔር ባለበት አገር ላይ ታች አንሶ አንድ ሃይማኖትና አንድ ብሔር ላይ ማቀንቀን በእውኑ የማስተዋል ውጤት ነውን?
      መጯጯህ ፣ አለመደማመጥ ፣ አለመከባበር ፣ ተቀራርቦ ከመወያየት ይልቅ መናናቅና መገፋፋት ፣ የትላንት ትውልድ የሠራውን ነውርና ዘረኛነት በግድና በብልሃት የዛሬው ትውልድ ላይ ቆልሎ በቂምና በበቀል ስሜት መነሳት ፣ ሰውን በሰውነቱ ሳይሆን በብሔርና በሃይማኖት ከፍሎ ማየትና ማቅረብ ከትላንቱ ያልተማርንበት ከባዱ ስህተታችን ነው፡፡ ይህን የምለው መንግሥት ጉያ ውስጥ ሆነው ጠብ የሚጭሩና በሕዝብ መታመስ የሚረኩ ባለሥልጣናት ያሉትን ያህል፥ አንዲት የደም ጠብታ ምድርን እንዳይነካ የሚተጉ አገር ወዳድ ባለሥልጣናት መኖራቸውን ባለመዘንጋት ነው፡፡ ከዚህ እጅግ በሚልቅ ቁጥር ደግሞ “አገራችን ተበድላለች ፤ ብሔራችን ተጨቁኗል” በሚል ሽፋን የአንድን ሃይማኖት ዶግማና ቀኖና በትውልድ ላይ ለመጫንና ዘረኝነት ፣ ግብረ ሰዶማዊነትንና ስድነትን በምድሪቱ ሊያመጡ የሚሠሩትን እጅግ እንቃወማለን፡፡
    በእርግጥ ከገበሬው አንስቶ ተምሬያለሁ እስከሚለው ተማሪና አስተማሪ ይህን እውነት ምን ያህል እንዳስተዋለው አላውቅም፡፡ ልብንና ኩላሊትን ፤ ሃሳብንና የውስጥ ስውር ዕውቀትን የሚፈትነው አምላክና እውነተኛ ልጆቹ ይህ እውነት ግን አይጠፋቸውም፡፡ እግዚአብሔር ደም የሚያፈሱትን የእነርሱን ደማቸውን ያፈሳል፡፡ ኢትዮጲያ ትላንት ደም ላፈሰሰችበት ፤ በገዛ ልጆቿ ላይ ለፈጸመችው ግፍና እልቂት ፤ ምድሪቱን ላረከሰችበት የደም እንባና ጎርፍ ከልብ በሆነ እውነተኛ ንስሐ አላጸዳችውም፡፡ ከዚያ አንዳች ነገር ሳንማር ዛሬም የአገርን ልጅ ደም ለማፍሰስ ካራ ስለን ተነስተናል፡፡ እንኳን ከእግዚአብሔር፥ ከህሊና በታች ስለወረድን ፤ ስለተሸነፍንም ስለት አንስተን የሰው ደም እናፈሳለን ፤ ንብረት እናወድማለን እንጂ ሰብዐውያን ብንሆን ተወያይተን ፣ ተወቃቅሰን ፣ ተገሳስጸን ፣ አንዳችን ሌላችንን (ሌላውን) ተቆጥተን ወደመንገዳችን በተመለስን ፤ በመለስንም ነበር፡፡
     ቃየን ደም በማፍሰሱ ምክንያት ምድር ለእርሱ ትሰጥ የነበረ ኃይሏን ነፍጋዋለች ፤ እርሱ ደም በማፍሰሱም የእርሱን ደም ሌሎች አፍስሰውታል (ዘፍጥ.4፥23-24) ምድር የሰማይ ዝናም እንጂ የሰው ደም የተገባት አይደለም ፤ ቃየን የወንድሙን ደም በማፍሰሱ በምድር ሁሉ ፊት ኮብላይና ተቅበዝባዥ ሆነ፡፡ ወንድሙ አምላክን በፍቅርና በመታዘዝ ደስ እናዳሰኘ ቃየን ግን ስለተሳነው በጥላቻ ወንድሙን በድንጋይ መትቶ ገደለው፡፡
     ሰውን መሳደብ ፣ በጥላቻ መጥላት ፣ ደሙን ለማፍሰስ መቸኮልና ለመግደል መጣደፍ የመሸነፍና ከማስተዋል የመጉደል ትልቅ ምልክት ነው፡፡ አዎን! በሕይወት መስበክ ስላልቻልን በኃይልና በጥላቻ እንነሳሳለን፡፡  የመንግሥት ባለሥልጣናትም ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶችም ፣ የመሃል ቤት ሰፋሪዎችም ትልቁ ችግራችን፦
1.     ከትላንቱ ታሪክ የተማርን አልመሰለኝም፡፡ የትላንቱን ነፍሰ ገዳነትና ዘረንነት በአፋችን ረገምነው እንጂ ከሃሳባችንና ከልባችን አልወጣም፡፡ ቀን ቢቀናልን ጎረቤታችንን ፣ ወዳጃችንን ለሞት የማንሰጥ እንኖር ይሆንን?
2.    ዛሬም የይቅርታ ጉልበት አልበዛልንም፡፡ አንዱ ብሔር ሌላውን ሊያፈቅር ፣ ሊቀበል ፣ በጋብቻ ሊዛመድ ፣ አቅርቦ ሊጎራበተው ... አቅም አጥቶ የትላንቱን ቂም በማሰብ የይቅርታ ጉልበታችንን አመናምነነዋል፡፡
3.    ልበ ሰፊዎች አይደለንም፡፡ ልበ ሰፊነት ሁሉን የመቀበል ደግሞም ሁሉን እንደቅዱስ ቃሉ የመመርመር ሃብት ነው፡፡ ጽንፈኝነትና ግትርነት ይህን ሃብት አስጥሎናል፡፡
     ኢትዮጲያ ዛሬም ከትላንቱ አልተማረችምና የልጆቿን ደም በማፍሰስ ተጠምዳለች ፤ የፍጡር ደም ደግሞ ጯኺና ከሳሽ ነው፡፡ (ዘፍጥ.4፥10 ፤ ዕብ.12፥24) ደም ደግሞ በደም እንዲጠራ እግዚአብሔር በልጁ ሞት ፤ በደሙ ሥርየትን ሰጥቶናል፡፡ (ዕብ.9፥22) የፈሰሰውን ደም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ማጥራት ((ዕብ.9፥14) ፤ በንስሐ መቋጨት የዛሬውን ቀን ሰላማዊ፥ የነገውን ደግሞ ብሩህ ፤ በተስፋ የተሞላም ያደርገዋል፡፡
      እንኪያስ “የሃይማኖት መሪዎች ወዴት ናችሁ? ፣ ቲዎሎጂያንስ ምነው ድምጻችሁ አይሰማም? የአገር ሽማግሌዎችስ የሰው መርገፍ አያሳስባችሁምን? በእውኑ አንድ ሰው ሲሞት አይገዳችሁምን? ስንት ሰው ሲሞት  ፤ አካሉ ሲጎድል ትነሱ ይሆን? … “የባሰ አታምጣ” ብለን የምናልፈው ነገር አይደለም ፤ ከዚህ የባሰ የለምና፡፡ በረሃብ የሚቆላውና አንጀቱ የተጣበቀው ወገን አሮ ፣ ከስሎ ፣ ደብኖ ፣ አንጀቱ ታጥፎ መሞቱ ሳያንስ የሌላውስ መጨመር በእውኑ ለምን አልገድ አለን?!  የምትጸልዩ ትጉ ፤ መፍትሔ ከፍጡር የምትፈልጉ ደግሞ ፍጹም የሆነ መፍትሔ ከአምላክ እንጂ ከፍጡር የለምና ንስሐ በመግባት  እጆቻችሁን ወደአዳኙና ታዳጊው ጌታ ዘርጉ፡፡

     አቤቱ ሕዝብህን አድን ፤ ርስትህንም ባርክ፡፡ ጌታ ሆይ! ሕዝባችንንና ምድራችንን ፈውስልን፡፡ አሜን፡፡

4 comments:

  1. tebarek wendeme

    ReplyDelete
  2. ABENZEER EBAKHN ESKI BEGIL ENAWERA SILKEHN ENDET MAGEGET ECHILALHU YEMTSEFEW POSTIVE NEW DES YELAL ENE CATHOLIC NEG BEHONEM ORTHDOXN EWEDALHU

    ReplyDelete