Friday, 4 December 2015

ድንግል ማርያም በድንግል ማርያም አንደበት (የመጨረሻ ክፍል)


6.  የእግዚአብሔርን መጋቢነት

           “የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል ፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል።” (ሉቃ.1፥53)

      እግዚአብሔር የተራቡትን ከመራባቸው በፊት አዝኖ ሲያስብላቸው (ዘፍጥ.41፥25 ፤ ሐዋ.11፥28) ፤ በተራቡና በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሲያጠግባቸው አይተናል፡፡ (ዘፍጥ.41፥54-56 ፤ ዘጸ.16፥6-18 ፤ ማቴ.6፥26 ፤ 31-32) ድንግል ማርያም በምድር ላይ ትኖር በነበረችበት ወራት ድኃ እንደነበረች የሚያሳየን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አለ፡፡ (ሉቃ.2፥22-24) በእርሱ መጥገብንም በሚገባ ታውቀዋለች፡፡ እንዲህ ያለውን ምስክርነት “ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ፥ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል” በማለት ቅድስት ሐናም ምስክርነት ስትሰጥ እናያለን፡፡ (1ሳሙ.2፥6)

     ከቃሉ እንደምንረዳው ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር መጋቢነቱ ማለትም መራብና መጠማት ፣ መደኅየትና መበልጠግ ፣ መታረዝና መልበስ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት የሚመራ መሆኑን ትመሰክራለች፡፡ የተራቡትን የሚያጠግብ ፤ ባለጠጎችንም ባዶአቸውን የሚሰድ በችሎታው ክንድ ኃይልን አድራጊ እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ይህንንም በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክሮች ማስረገጥ ይቻላል፡፡ (ዘዳግ.32፥19 ፤ 2ነገ.4፥32-35 ፤ ኢዮ.1፥21 ፤ 42፥2 ፤ 12)
     እግዚአብሔር ቦታ ሲያደላድል “እንዴትና ለምን?” ብሎ የሚጠይቀው የለምና ፤ ታላቁ መጽሐፍ  ባዕለጠጎችን መጽሐፍ እንዲህ እያለ ያስጠነቅቃል፦ “ቅሚያንም አትተማመኑት ባለጠግነት ቢበዛ ልባችሁ አይኵራ።” (መዝ.62፥10)
5.  ተስፋ
     በምድር የምንኖርበት ትልቁ ጉልበት ተስፋ ነው፡፡ ያለተስፋ በምድር ላይ የአይን ጥቅሻ ያህል እንኳ መኖር አይቻለንም፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ያቆየበትና ሕዝቡም በመታመን ታግሰው የጠበቁበት ጉልበት ተስፋ ነው፡፡ (ዘዳግ.15፥6 ፤ 26፥18 ፤ 27፥3 ፤ 1ነገ.8፥20 ፤ 24 ፤ 25 ፤ 56 ፤ 2ነገ.8፥19 ፤ 1ዜና.1፥9 ፤ 6፥10-15 ፤ 21፥7 ፤ መዝ.33፥20) በእርግጥም እግዚአብሔርንና ስሙን ተስፋ ማድረግ ይገባል፡፡ (መዝ.25፥11 ፤ 52፥9 ፤ 71፥14 ፤ ) ፍጥረትም ሁሉ የእግዚአብሔርን አይንና እጅ ተስፋ ያደርጋል፡፡ (መዝ.124፥7 ፤ 145፥15)
     ቅድስት ድንግል፥ “ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ” ስትል ፥ ለአባቶቻችን የተነገረውን ተስፋ ቃል ፍጹም ይጠብቁ የነበሩ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ድንግል ማርያም በነበረችበት ዘመን ለአባቶቻችን የተነገረውን የተስፋ ቃል ይጠብቁ የነበሩ ድንቅ ቅሪት ቅዱሳን መኖራቸውን ወንጌላዊው እግዚአብሔር ለምድሪቱ ምስክር ማኖሩን እንዳሳየ ዘግቦልናል፡፡ አረጋዊ ስምዖንንና ቅድስት ነቢይት ሐና፡፡ ስለእርሱም ሲናገር፦ “እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፥ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበር፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ።” (ሉቃ.2፥25) ስለእርሷም ፦ “ … በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች ፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር።” (ሉቃ.2፥37-38) እኒህ ሁለት ቅሪት ቅዱሳን ተስፋቸው እጅግ የሚደንቅና በትንሹ ተስፋ ለምንቆርጥ እግዚአብሔርን ብዙ መጠበቅ ዋጋ እንዳለው በሕይወት ያስተምሩናል፡፡
    በምናምነው ነገር ላይ ያለን የእምነት ጉልበት ልል በሆነው ልክ ተስፋችንም እጅግ ይላላል፡፡ በተስፋ አይኖች ትክ ብለን በትኩረት የምናምነውን ነገር ሳንታክት ለማየት፥ የእምነት ብርሃናችን ሳያቋርጥ መብራት አለበት፡፡ የተስፋ አይኖቻችን በመፍዘዝ የሚደበዝዙት የእምነት ጉልበታችን ከቃሉ አቅም በመራቅ ሲጣምን ነው፡፡

7.  እግዚአብሔር ኪዳኑን ይጠብቃል
ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።”

     እግዚአብሔር ለአብርሃም የምድርን ነገዶች ሁሉ በእርሱ ዘር ሊባርክ ፤ እንዲሁም ለሙሴ ደግሞ በሕጉ አማካይነት ለሁልጊዜ ከእነርሱ ላይለይ ኪዳን ሰጥቷቸው ነበር፡፡ የኪዳኑም ምልክት ለአብርሃም ወንድ ሁሉ እንዲገረዝ የሚል ሲሆን፥ ለሙሴና ለእስራኤል ሕዝብ ደግሞ የሰንበትን ቀን ማክበር ነበር፡፡ (ዘፍጥ.12፥2 ፤ 17፥11 ፤ ሕዝ.20፥10-20) በዚህ ኪዳንና ምልክት ግን ነቀፋ ስለተገኘበት (ዕብ.8፥7) እግዚአብሔር ይህን ኪዳን እንደጥላና ምሳሌ እንዲያገለግል አድርጎ በፍጻሜው አዲስ ኪዳንን ሊሰጥ ፍጹም የሆነ ኪዳን ለሕዝቡ ሰጠ፡፡ (ኤር.31፥31)
     ይህን የተሰጠውን ኪዳን ድንግል ማርያም በሚገባ ታውቀዋለች፡፡ አውቃም በጸሎቷ ውስጥ አንስታዋለች ወይም በጸሎቷ ለዘወትር በመማለድ ለትውልድ እንዲሆን ተግታ ጸልያለች፡፡ የእግዚአብሔር ልብ ያለው ቅዱስ የዘወትር ጥማቱ ትውልድ በመባረኩና ከጥፋት በማምለጡ እንጂ የራሱ መልካምነት ፤ ቅንጦትና ምቾት አይደለም፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም የዘወትር ጥማትና ናፍቆቷ እግዚአብሔር በኪዳኑ የአብርሃምን ቤት እንዲያስብ ነበር ፤ እኛስ የዛሬው ጥማትና ናፍቆታችን ምን ይሆን!? በእውኑ የቤተ ክርስቲያን ማደግና መለምለም ፤ የወደቁት እንዲነሱና እንዲተጉ ፤ በኪዳኑም እነንዲታቀፉ ይሆንን!?
    ጌታ እግዚአብሔር አብ በነገር ሁሉ ስለረዳን ስሙ ቡሩክ ይሁን፡፡ አሜን፡፡



No comments:

Post a Comment