ይህን ጽሁፍ
ከመጻፌ በፊት ለብዙ ሰዓታት ውስጤ ከገለባ ይልቅ እስኪቀልብኝ ድረስ “አስቀድሞ ነገር፥ እኔ ራሴ ለሌላው በተለይም ለሃይማኖት ቤተ
ሰዎቼ ወንድም መሆን እችላለሁኝ?” ብዬ ከራሴ ጋር ተሟግቻለሁኝ፡፡ ምናልባት ጥያቄው ያን ያህል ከባድ ላይመስል ይችላል ፤ ይህን
ጥያቄ ይዘን ወደታላቁ መጽሐፍ ሚዛንነት የተጠጋንና ራሳችንንም በታላቁ መጽሐፍ ሚዛንነት ያየን እንደሆን ግን እጅግ የሚስቡና እይታችንን
የሚያጠሩ እውነቶችን እናስተውላለን፡፡
“ወንድም” የሚለውን
ቃል ታላቁ መጽሐፍ ሲፈታው፥ ከአንድ እናትና አባት የሚወለዱትን ብቻ ሳይሆን የአንድ አገር ተወላጆችን (ዘጸ.2፥11 ፤ ሐዋ.7፥23-26)
፤ ከጥብቅ ወዳጅነት የተነሳ እጅግ የተቀራረቡትን (2ሳሙ.1፥26-27) ፤ ከቅርብ ዘመድ የተነሳ የተወዳጁትን (ዘፍ.36፥10 ፤ ዘኊል.20፥14 ፤ ሮሜ.9፥3) ፤ በቃል ኪዳንም (1ነገ.5፥1 ፤ 12) ወንድማማችነት
እንዳለ ይነግረናል፡፡ ወንድማማችነት ምንም እንኳ መሠረቱ በደም መወለድ ቢሆንም፥ ከዚሁ ጋር ሊተካከል በሚችል መልኩ ደግሞ ታላቁ
መጽሐፍ በአላማ የተሳሰሩትን እኩል አስተካክሎ ያስቀምጣል፡፡
ወንድማማች ያልሆኑ - የ“አንድ
እናት” ልጆች
በፍጥረት ታሪክ
የመጀመርያዎቹ ወንድማማቾች ቃየልና አቤል ነበሩ፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች ከእናትም ከአባትም ከአንድ ምንጨ ማህጸን ተቀዱ፡፡ ታላቁ
መጽሐፍ ሁለቱን ወንድማማቾች ከጅማሬው በእኩልነት አስተካክሎ “አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ ፤ ቃየንም
ምድርን የሚያርስ ነበረ።” (ዘፍጥ.4፥2) በማለት ያስቀምጣቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረትን በፈጠረበት ሃሳቡ አንዳች አድሎ አልነበረበትም፡፡
ሁለቱም የተደነቀና ውብ ፤ የተለያየ ሙያ ነበራቸው፡፡ የሙያ ሥራ በኃጢአት
በመውደቃችን ያገኘነው ሳይሆን ቀድሞም ከውድቀት በፊት የነበረ ታላቅ የእግዚአብሔር በረከት ነው፡፡ (ዘፍጥ.2፥15) አዳም ከመውደቁ
በፊት፥ እንደፈጠረው አባቱ እግዚአብሔር ሠራተኛ ነበር፡፡ (ዮሐ.5፥17) ገነትን በመንከባከብና በመጠበቅ፡፡ ልጆቹም ይህንን ገንዘብ
አድርገው ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡ “ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ።” ሲለን የሁለቱም ሥራ እኩልና የማይበላለጥ መሆኑን ያሳየናል፡፡
ከኃጢአት በቀር የትኛውም ሥራ በእግዚአብሔር ፊት ቅቡል ነው፡፡ ምድሪቱን
ማጐሳቆል ማራቆት አልተባለልንም ፤ በተመሰገነው ሥራ እንጠብቃትና እንከባከባትና ዘንድ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ሁለቱን ወንድማማች
ከጅማሬው ፈጽሞ አላበላለጠም፡፡ ለልዩነቱ ምክንያት የሆነው ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕትን ሲያቀርቡ ልዩና እንደወንድማማችነታቸው
አንድ ያይደለ ነው፡፡ መጽሐፍ፦ “ … ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ ፤ አቤልም ደግሞ
ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም።”
(ዘፍጥ.4፥3-5) እንዲል ሲፈጠሩና ሲኖሩ አንዳች አድሎ ያልነበረባቸው ፤ እኩል ፈቃድ ፣ እኩል ስሜት ፣ እኩል እውቀት ግን የነበራቸው
መሥዋዕት ያቀረቡት አንዱ የሰባውንና የተመረጠውን ፤ ካለው በጐች መካከል እጅግ የተወደደውን ሲሆን ቃየን ግን ካመረተው በግድ የለሽነት
ዘግኖ ያልተመረጠውንና ያልሰባውን አቀረበ፡፡
የጸሎት ፣ የስብከት ፣ የዝማሬ ፣ የትምህርት ፣ የስጦታና ሌሎችንም መሥዋዕቶቻችን
በእግዚአብሔር ፊት ኃይል ያጣው ምርጡን ለራሳችን እያቀረብን መናኛውን ግን ለእግዚአብሔር ስለምንል ነው፡፡ የምንጸልየው ፣ ቃሉን
የምናጠናው ከሥራ በተረፈን መናኛ ሰዓትና ጉልበት ነው እንጂ እጅግ ከምንወደውና ከምንሳሳለት ነገራችን ላይ በመቀነስ አይደለም፡፡
የተወደዱ ቅዱሳን ግን የሕይወታቸው አንዱ ፣ የበላዩ ፣ ምርጡ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
እግዚአብሔር ሁሉን እንደመንገዱ የሚከፍል አምላክ ነውና (መዝ.94፥23
፤ ማቴ.25፥28 ፤ ራእ.2፥23) የሁለቱን ወንድማማቾች መሥዋዕት እንደየአቀራረባቸው ተመለከተ፡፡ ሲመለከትም ፦ ወደአቤልና በልቡ
ቅንነት ወዳቀረበው መሥዋዕት ሲመለከት፥ የቃየንን ግን አልተመለከተውም፡፡ አቤል እግዚአብሔር የሚወደውንና ትክ ብሎ የሚያየውን መሥዋዕት
ሊያቀርብ በልቡ ማስተዋል አሰበ ፤ “አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ” (ዕብ.11፥4)
እንዲል፥ አቤል ለጽድቅ በሚሆን እውነተኛ እምነትና መሰጠት አቀረበ ፤ ቃየን ግን ከመታዘዝ ፍጹም ዝንጉ ሆነ፥ ስለዚህም ልቡ በኃጢአት ተጠምዶ ደስታ ርቆት ፊቱ
በሃዘን ተዋጠ፡፡ (ምሳ.15፥13) ፊቱን ያጠቆረው በእግዚአብሔርና በአቤል ላይ ነው፡፡ እግዚአብሔር መሥዋዕቱን ባይቀበልለት በእግዚአብሔር
ተቀየመ ፤ የአቤልን መሥዋዕቱ ደግሞ ቅድመ እግዚአብሔር ቅቡል ስለሆነ በወንድሙ ፊቱን አጠቆረ፡፡
ለንጽጽር የቀረበው ፥ የቀረበው የእንሰሳቱና የዕጽዋቱ መሥዋዕቱ ሳይሆን
ሁለቱ ያቀረቡበት ልብ ነው ፤ ለቃየን ምክንያት ያልሆነው ነገር ምክንያት ሆኖለት በወንድሙ ላይ በንዴት ፊቱን አጠቆረ፡፡ ከቃየን
ከዚህ የተሻለ መጠበቅ አይቻልም ፤ ቀድሞም እይታው የተበላሸ ነውና ፤ ቃየን ፊቱን ያጠቆረው ልቡን የተቆጣጠረው የክፋት ኃይል በእርሱ
እንዲሰለጥን በር ስለከፈተ ነው፡፡ ልባችን በክፋት ኃይል ሥር ሲወድቅ የምንጣላው ከራሳችን ጀምረን፥ በዙርያችን ካሉ ነገሮች ሁሉ
ጭምር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የግድያ ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎችን የማየትና የማግኘት እድሉን አለኝ ፤ በተለይም የአገራችን የመንደር አሰፋፈር
“ቤተሰባዊ መልክ” ያለው ስለሆነ፥ ግድያዎች የሚፈጸሙት በአብዛኛው ከቤተሰብ በአንዱ አካል በሆነው በወንድም ላይ ነው፡፡ እኒህ
ሰዎች ወንድሞቻቸውን ለምን እንደሚገድሉ ብዙ ጊዜ ስጠይቅ፦ “ድርጊቱን በሚፈጽሙበት ሰዓት የሚያደርጉትን ‘እንደማያስተውሉ’ አምርረው”
ይናገራሉ ፤ ጥቂት ልመክርና ልወቅሳቸው ሳስብ የማያባራ እንባቸውን ይዘረግፉታል ፤ ባስታወሱት ቁጥር ቁጭታቸው ድንበር የለውም!!!
በመንፈስ ቅዱስ የምንታመን ከሆንን መንፈስ ቅዱስ በፍሬው ራስን የመግዛት
መንፈስ ሰጥቶናል (ገላ.5፥23 ፤ 2ጢሞ.1፥7) ፤ ራስን አለመግዛት በገዛ ማንነትና ወገን ላይ በአመጽ ያነሳሳል፡፡ የኃጢአት
መንገድ ቶሎ ካልተቋጨ ፤ ግንዱ ከሥሩ ተመንግሎ ካልተቆረጠ ቀጣይ ሌላ ፍሬ ፤ ልላ ቅርንጫፍ ማፍራቱ አይቀርም፡፡ ዳዊት ከሌላ ሰው
ሚስት ጋር አመነዘረ ፤ ማመንዘሩን ለመደበቅ የሴቲቱን ባል አስክሮ ማጭበርበር ፈለገ ፤በስካር አጭበርብሮ መደበቅ ባይቻለው ኦርዮን
አስገደለ … (1ሳሙ.11፥) አንዱ የኃጢአት ዘለላ ፈጥኖ አለመቆረጡ ሌላ ፍሮ እንዲያፈራ ለዲያብሎስ ፈንታ ይሰጣል፡፡ ቃየን በዚህ
አላበቃም ፤ ሃሳባዊ ኃጢአቱን ድርጊታዊ ማድረግ ፈለገ፡፡
ወዳጆች ሆይ! የእንደገና አምላክ ፊቱን እንዲመልስላችሁ የጀመራችሁትን የኃጢአት
መንገድ ፈጥናችሁ አቋርጡና ፊታችሁን በንስሐ ወደእርሱ አቅኑ፡፡ ጌታ ይርዳን፡፡ አሜን፡፡ ይቆየን…
ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment