እግዚአብሔር ጉልበትና ማስተዋል ሆኖኝ ፥ ይኸው ይህን አገልግሎት
ከጀመርኩ ሁለት አመት ሞላኝ፡፡ የዘላለም መዳን ፈቃድን ሲጠይቅ
(ማር.2፥5 ፤ ዮሐ.5፥6 ፤ ሐዋ.8፥37 ፤ 13፥46) አገልግሎት ደግሞ ጥሪና መለየትን ይሻል፡፡ (ዘፍጥ.12፥1-9 ፤ ሐዋ.9፥15)
በየትኛውም ዘመን የተገለገለ የወንጌል አገልግሎት ያለመከራና ነቀፋ ተገልግሎ አያውቅም፡፡ የሐዋርያትን ዘመን ትተን ክርስትና በነጻነት
ተገለገለ የተባለበትን ዘመን ብናይ እንኳ እነቅዱስ አትናቴዎስ ከአርባ አመታት በላይ በከባድ ስደትና ህመም ፤ በስም ማጥፋት ፣
እነቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በእስርና በስም ማጥፋት ክስ የወደዱትን ጌታ አገልግለውታል፡፡
ለዚህም ነው ክርስትና ከዓለማዊነት ጠባይና ምኞት ጋር ተካክዶ (ቲቶ.2፥13)
እንጂ ተመቻምቾ (ተስማምቶ) የኖረበት ዘመን የለምና በየትኛውም ዘመን ያለመከራ የማይገለግለው፡፡ በዚህ ዘመንም ሰዎች አለማዊነትን
ተለማምደው ወደ እግዚአብሔር መንጋ ሲያመጡ ፥ ለእውነት የጨከኑና ለእግዚአብሔር የወገኑ አጥብቀው ከማስተማርና ከመምከር አልፈው
የጌታን ወንጌል በማንሳት ሊገስጹ ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያለው የአገልግሎት በር ሊከፈት ሲገባ ዛሬ ግን አለማዊነት በቤተ
ክርስቲያን አብቦ በየመድረኩና በየአውደ ምህረቱ ሁከትና ክርክር ፣ ክስና ሽንገላ ፣ የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ጉድለት ጭቅጭቅ በመብዛቱ
“የተከፈተው በር ሲዘጋ” እያየን ነው፡፡
በተቃራኒው ይህ ይስተካከል! የሚሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በተለያየ መንገድ
“ከመንገድ እየተወገዱ” የበግ ለምድ የለበሱ አለማውያንና መናፍቃን ፣ ግብረ ሰዶማውያንና ጠንቋይ … ነጣቂ ተኩላ የሐሰት መምህራን
(ማቴ.7፥15) መድረኩን መውረር ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ በእርግጥ በዚህ ዙርያ ገና ከእግዚአብሔር ጋር ልንሠራው የሚገባን ትልቅ
የቤት ሥራ እንዳለብን ልንዘነጋ አይገባንም፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት ያየናቸውን ነውሮች በግልጥ አንስተን ምንም ሳናቅማማ በእግዚአብሔር
ጉልበት “ጽድቁን ጽድቅ ፤ ኃጢአቱንም ኃጠኢት ነው!” ለማለት ደፍረናል፡፡ይህን እንድንል ጉልበት የሆነን የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር
ስሙ ይባረክ፡፡ ክብርም ሁሉ ለጌታችንና ማስተዋልን ለሠጠን ጥበባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን፡፡ አሜን፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ይህ
አገልግሎት ለሁሉ እንዲዳረስ ፥ የተከፈተው የአገልግሎት በር እንዳይዘጋ በብዙ የረዳችሁንን ፤ በጸሎት ያሰባችሁንን ወገኖች ጌታ
በማታልፈው መንግሥቱ ዋጋችሁን ያብዛ እላለሁ፡፡
ጌታ ኢየሱስ ቀሪ የአገልግሎት ዘመናችንን ይባርክልን፡፡ አሜን፡፡
be blessed
ReplyDelete