Sunday 15 March 2015

ጌታ ሆይ ፤ ና! (1ቆሮ.16፥22)


                                                 Please read in PDF
 

     
 የጥንት ክርስቲያኖች ጌታ ወደሰማያት ከማረጉ ምንም ሳይቆይ በመናፈቅ ለሁልጊዜ ይጮኹ የነበሩት የዳግመኛ መምጣቱን ነገር እንደሆነ ታላቁ መጽሐፍ አስረግጦ ይነግረናል፡፡ የአዲስ ኪዳን የትንቢት መጽሐፍ የሆነው የራዕይ መጽሐፍ የመጽሐፉን መግቢያ ሲጀምር በተደጋጋሚ “ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር… ” እንደሆነና ጌታ ባረገ ገና አንድ ምዕት ሳይሞላው “ዘመኑ ቀርቦአልና …” (ራዕ.1፥1 ፤ 3) በማለት ዘመኑ በደጅ የቀረበ መሆኑን በግልጥ ተናግሮ ሳያበቃ መጽሐፉን የዘጋው “ዘመኑ ቀርቦአልና … እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ … መንፈሱና ሙሽራይቱም ፦ ና ይላሉ ፦ የሚሰማም ፦ ና ይበል። … አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና።“ (ራዕ.22፥10 ፤ 12 ፤ 17 ፤ 20) በማለት በተደጋጋመ ናፍቆታዊ መቃተት ነው፡፡


    የክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት በዚህ አሁን እኛ ባለንበት ዘመን ከፊት ይልቅ ይበልጥ በደጅ ቀርቧል፡፡ (ማቴ.24፥32-33) እንዲህ ቀርቦ ሳለ ግን ይህን የቤተ ክርስቲያንን ፍጹም ተስፋና መጽናናት የሆነውን የክርስቶስን መምጣት (1ቆሮ.15፥19 ፤ 1ተሰ.4፥18 ፤ ቲቶ.2፥12-13) የሚቃወሙና ከፊት ይልቅ እጅግ የሚክዱ አለማውያንና መናፍቃን የበዙበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቆመችበት አንዱና ትልቁ መሠረት ትንሳኤ ሙታን እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ “ስለክርስቶስ የተሰጠው የመጀመርያ ትምህርት …  ስለ ሙታንም ትንሣኤ ስለ ዘላለም ፍርድም ትምህርት” (ዕብ.6፥1-2) እንደሆነ ይናገራል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በጉባኤ ኤፌሶን በወሰነችው አንቀጸ ሃይማኖቷ “በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ዳግመኛ ይመጣል” በማለት ትመሰክራለች፡፡ ስለሁሉ የተቀጠረ ቀን እንዳለ ፤ (2ጴጥ.2፥9) ይህ ምስክርነት መጽሐፍ ቅዱሳዊና የታመነ እውነት እንደሆነ ቃሉ ይናገራል፡፡ (ሐዋ.10፥42 ፤ ሮሜ.14፥9 ፤ 2ጢሞ.4፥1 ፤ 1ጴጥ.4፥5 ፤ ራዕ.19፥11)
  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል ፤ የሚመጣው፦
1.    ቤተ ክርስቲያንን ከመከራ ሊያሳርፍ ነው፡፡

    ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን በማመኗ እንደእርሱ በከባድ መከራ ታልፍ ዘንድ ግድ ነው፡፡ (ማቴ.5፥11 ፤ 24፥9-10 ፤ ዮሐ.15፥18 ፤ 16፥33 ፤ሐዋ.14፥22 ፤ ሮሜ.5፥3 ፤ 2ጢሞ.3፥12 ፤ ራዕ.7፥14) በተለይም ደግሞ በዘመኑ መጨረሻ ፤ መጨረሻ ላይ ልትቀበልና ሊገጥማት ያለው መከራ “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።” (ዳን.12፥1-2 ፤ ማቴ.24፥21) በማለት የተገለጠ ነው፡፡ ከሰው ፍጥረት ማንም የሚድን እስከማይመስል ድረስ መከራውን ፦ ከባድ የሚያደርገው መከራው በምድር በሚኖሩ ፥ ነገር ግን  ጌታ ኢየሱስን በሚያምኑ ሁሉ ላይ መሆኑ (ራዕ.3፥10) ፣ ምድር ሙሉ ለመሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ሐሰተኛውን ክርስቶስ “ … አውሬውን እየተከተለ በመደነቅ መውደቁ” እና (ራዕ.13፥3 ፤ 12) ሰዎችም በእርሱ መንፈስ የሚመሩ በመሆናቸው ምክንያት መከራውን ከባድና አስጨናቂ ያደርገዋል፡፡
   ነገር ግን ይህ ሁሉ ቢሆንም እንኳ በአውሎና በወጀብ መካከል መንገድ ያለው ጌታ (ናሆ.1፥3) “ሁል ጊዜ በጸሎት የተጉ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንደሚቻላቸው” (ሉቃ.21፥31) ፣ በእርሱ የሚያምኑ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ ፤ እግዚአብሔር ለቍጣ ስላልመረጠን (1ተሰ.5፥8) ቤተ ክርስቲያን ከመከራው ትድናለች ፤ ሙሽራይቱን ሙሽራው ጌታም ይታደጋታል፡፡

2.   ፍጥረትንም ሊያሳርፍ

    ፍጥረት ከኃጢአትና ከበደል የተነሳ ለመፍረስና ለጉስቁልና ተሰጥቷልና በክርስቶስ ኢየሱስ በሚሆነው ዳግም መምጣት ለማረፍ ይቃትታሉ፡፡ ፍጥረት በእርግጥ አሁን እጅግ በምጥ ነው የሚኖረው፡፡ የዚህ ዋናው ምንጭ ደግሞ የሰዎች ልጆች ኃጢአት ከልኩ ማለፍ ነው፡፡ ስለዚህም የሚመጣው ጌታ ሁሉን አዲስ በማድረግ ከዚህ ዓለም ያይደለ ፤ ትመጣ ያለችና በማንም ልብ ያልታሰበችውን አዲስና ድንቅ ፥ አዲስ ሰማይና ምድርን ለልጆቹ ሲያዘጋጅ ( 2ቆሮ.5፥17 ፤ ዕብ.13፥14 ፤ ራዕ.21፥1) ፍጥረት አሁን ከሚሆንበት መከራ ፤ ሰቆቃ ላይደርስበት በትኩሳት ያልፋል፡፡ (2ጴጥ.3፥9) ነገር ግን ፍጥረትም የሰውን ልጅ ማረፍን በፍጹም መቃተት ይቃትታል፡፡

3.  የዘላለም ፍርድ የተጠበቀላቸውን ሊቀጣ

     የሐሰት መምህራን ምድርን ሁሉ በክፋታቸው እግዚአብሔርን ከመፍራት ውጪ አድርገው ስለበከሉና ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ፈጽማ ስለረከሰች ፥ ሁሉንም የሚያጠፋም ቢሆንም ፥ ጌታ ዳግም የመምጣቱ ነገር የሚዘገየው ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ ነው፡፡ (2ጴጥ.3፥7-9) እርሱ በመስቀል የሞተው ጌታ ፍጥረት ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ እንዲጠፋ አይፈልግም፡፡ (ሕዝ.33፥11 ፤ 1ጢሞ.2፥4)
    መዳንን በተመለከተ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ነጻነትን የሰጠ ነው፡፡ (ዘፍጥ.2፥16 ፤ ዘዳግ.30፥15 ፤ 19 ፤ ሕዝ.3፥18) የሰው ልጅ ደግሞ ነጻነቱን በመጠቀም ሞትን ወይም ሕይወትን መምረጥ የእርሱ ድርሻ ነው፡፡ በኃጢአታቸው የሚጸኑትንና ንስሐ ፈጽመው የማይገቡትንና ያልገቡትን በአንድነት  “ሰማያትን በታላቅ ድምፅ ያሳልፋል፥ የሰማይም ፍጥረትን በትልቅ ትኵሳት ያቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ያቃጥላል።” (ማቴ.24፥35 ፤ 25፥46 ፤ 2ጴጥ.3፥10 ፤ ራዕ.21፥1) የኃጢአት የመጨረሻ ዕጣና ደመወዝም ሞት ነውና ኃጢአተኞች ለዘለዓለም ይሞታሉ ፤ ከእግዚአብሔርም ህልውና ውጪ ይሆናሉ፡፡(ሮሜ.6፥23 ፤ ያዕ.1፥15)

4.  ሰይጣንን ለዘላለም ሊፈርድበት

     እግዚአብሔር የሰዶምንና የጎሞራን ሰዎች በኃጢአታቸው ሳይራራላቸው የሚቃጠል ድኝ በማፍሰስ ሙሉ ለሙሉ ያጠፋቸው (ዘፍጥ.19፥24) “በዘላለም እሳት እየተቀጡ ለሚኖሩት ምሳሌ” ነው፡፡ (ይሁ.7) ልክ እንዲሁ የሰውን ልጅ የሚያስቱና ለራሳቸውም የሳቱ  “ … የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል።” (ይሁ.6)
    “ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥  … ።” (ራዕ.19፥20 ፤ 20፥10) ጌታችን ሲመጣ ከሚሆኑት ነገሮች አንዱ፥ ጽኑና ማንም የማይሽረው ፍርድ ሲሆን ኃጢአንንም ሰይጣን ወደተጣለበት የእሳት ባህር “እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ።”(ማቴ.25፥41) በማለት የሚፈርደው የዘላለም ፍርድ ነው፡፡
5.  የዘላለም ሕይወትና ዕረፍትን ለልጆቹ ሊሰጥ

“ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና።” (2ተሰ.1፥6-7)

       ቅዱስ ጳውሎስም ሆነ ስለክርስቶስ በሆነው ነገር ሁሉ መከራን የተቀበሉ የተሰሎንቄ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም አብረው መከራን እንደተቀበሉ እንዲሁ ዕረፍቱንና ደስታውንም እንደሚካፈሉ ይጽፍላቸዋል፡፡ ጌታ ክርስቶስ ቃሉን በመጠበቅ የተጉትንና ለፈቃዱ የታዘዙትን ጻድቃንን፥ ነጻ የዘላለም ሕይወትን በስጦታ ከቸርነቱ የተነሳ ያድላቸዋል፡፡ (ምሳ.10፥16፤ ማቴ.25፥46) ይህም “እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ፡፡” የሚል ነው፡፡ (ማቴ.25፥34)
  ቤተ ክርስቲያን ታላቁን መከራ በሙሽራዋ ጉልበት በማለፍ ፤ በዓለም ላይ ስለስሙ የሚገጥማትን ሁሉ ተግዳሮትም ፊት ለፊት በመቃወም የምትጓዘው ታላቁ ጌታ ዳግመኛ እንደሚመጣ በማመን ነው፡፡ አዎ! ጌታችን ይመጣል፡፡ እርሱ ባይመጣ ከፍጥረት ወገን ከመከራውና ከኃጢአቱ ብዛት የተነሳ የሚድን የለምና (ማቴ.24፥22) የጌታችን መምጣት ለሁሉ ነገር ማማርና መትረፍ ዋስትና ነው፡፡ አሜን ፤ ጌታችን ሆይ ና!!! ማራናታ!!! አሜን፡፡ 
“መንፈሱና ሙሽራይቱም። ና ይላሉ።” (ራዕ.22፥17) አሜን፡፡

3 comments: