ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባቱና ለእኛ
የታዘዘበትን የገዛ ዘመኑን (1ጢሞ.2፥7) በመፈጸም ወደአባቱ ለመሄድ በመወሰኑ ምክንያት ለመጨረሻ ጊዜ ከኢያሪኮ
(ማቴ.20፥29 ፤ ማር.10፥46 ፤ ሉቃ.19፥1) “ወደ ኢየሩሳሌምም ከደብረ ዘይት
አጠገብ ወዳሉቱ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ” ሄደ፡፡ ጌታችን ወደኢየሩሳሌም የወጣው አይሁድ እንደሚገድሉት ፤ በእርሱም ላይ እንደተነሳሱ
እያወቀ ነው፡፡ (ማቴ.20፥17-19 ፤ ማር.10፥32 ፤ ሉቃ.9፥22 ፤ 44 ፤ 18፥31) ነፍሱን በፈቃዱ ስለበጎቹ ያኖረው ጌታችን
(ዮሐ.10፥16) ከታላቅ ፍቅሩ የተነሳ ነው ስለእኛ የሞተው፡፡
ራሱን
መሥዋዕት ሊያደርግ ፥ ሞትን አላማ አድርጎ ወደዚህ ምድር የመጣ ከጌታችን በቀር ማንም የለም፡፡ የሕማማቱ ሳምንት ሊጀምር ጌታችን
በክብር ወደኢየሩሳሌም ሊሄድ ተነሳ፡፡ ጌታችን ወደኢየሩሳሌም መሄድን ሲያስብ ፥ አይሁድ እንደሚገድሉት ቢያውቅም መሢህነቱን ይሸሽግ
ዘንድ አልወደደም፡፡ የክርስቶስ ሞት ለክርስትና ትምህርት ዋናና እጅግ አስፈላጊው ነው፡፡ ገና በተወለደበት ወራት አረጋዊው ቅዱስ
ስምዖን የሕጻኑን እናት “በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት።” (ሉቃ.2፥35)በማለት ከሕጻኑ የተነሳ እናቱ የሚደርስባትን
ነገር በግልጥ ተናገረ ፤ በሕጻኑ እናት ነፍስ ላይ ሰይፍ ካለፈ በሕጻኑ የደረሰው እንዴት ከአዕምሮ ያልፍ ይሆን?!
ጌታችን
ኢየሱስ ቀድሞም ሊሞትልን እንዳለ የተቆረጠ እውነት ነው፡፡ (ሉቃ.22፥22 ፤ ዮሐ.2፥19-21 ፤ 3፥16 ፤ ራዕ.13፥8) በሐሙስ
ማታ ጸሎቱ “አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን” (ማቴ.26፥39)
በማለት ቢጸልይም ነገር ግን “አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣትምን?” (ዮሐ.18፥11) በማለት ጽዋውን ይጠጣ ዘንድ አባቱ እንደወደደ
በግልጥ ተናግሯል፡፡ አባቱ የፈቀደውንና ክርስቶስ ስለሁላችን ሲል ሊጠጣ የወደደውን ጽዋ፥ ጴጥሮስ፦ “ጌታ ሆይ፥ አሁን ልከተልህ
አለመቻሌ ስለ ምንድር ነው? ነፍሴን ስንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ አለው።” (ዮሐ.13፥37) በማለት በሞቱ የሚገኘውን የፍጥረት ሁሉ
መዳን ሳያውቅ ተቃወመ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን የአባቱን ፈቃድ የሚቃወመውን ክፉ ሰይጣን ፍጹም ገሰጸው፡፡
“በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥
ወዲያውም ወደ እርስዋ ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም፦ ስለ ምን
እንዲህ ታደርጋላችሁ? ቢላችሁ፦ ለጌታ ያስፈልገዋል በሉት፥ ወዲያውም ደግሞ ወደዚህ ይሰደዋል አላቸው።” (ማር.11፥2-3) ሊቃውንት
አህዮቹን የሰረቀውና በመንገድ አስሮ የሄደው ሌባ ነው ይላሉ ፤ በምሳሌነትም አህዮቹ የአዳምና የልጆቹ ምሳሌ ፣ ሌባው ደግሞ ሰይጣን
እንደሆነ ይተረጉማሉ፡፡
ሌባው
ዲያብሎስ (ዮሐ.10፥10) በኃጢአት ያሰራቸው የሰው ልጆች ፥ አርነት ሳያገኙ ለዘመናት ኖረዋል፡፡ “ለታሰሩት መፈታትን ሊሰብክ
… የተጠቁትንም ነጻ ሊያወጣ” (ሉቃ.4፥19) የመጣው ጌታ፥ የታሰሩትን አህዮች ፈትተው እንዲያመጡ ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ፡፡ የሆሳዕናው
ጌታ መፈታት ለሚያስፈልጋቸው እስረኞች ነጻ እንዲወጡ ፈረደ፡፡ መድኃኒት ለታመሙ ፤ መፈታት ለታሰሩ ይገባቸዋል፡፡ ዛሬ የተዘነጋው
ትልቁና ዋናው የቤተ ክርስቲያን ሥራ ይህ ይመስለኛል!!! የታሠሩት ሳይፈቱ ፣ የወደቁት ሳይነሱ ፣ የተበተኑ ሳይሰበሰቡ ፣ የቆሰሉ
ሳያገግሙ ፣ የታመሙ ሳይድኑ … እነሆ አገልግሎት የሚመስል አገልግሎት እያገለገልን አለን!!! አቤቱ አገልግሎታችንን ባርክ!!!
ኃጢአት የመንፈስና የነፍስ ቁስል ፣ በደል ደግሞ ጽኑ እስራት ነው ፤ ኃጢአት ያላደረገው ጌታ (1ጴጥ.2፥22) በኃጢአት
ለታመምነው የሕይወት መድኃኒት ፣ ፍጹም ለታሰርነው ደግሞ አርነትና ነጻነት ሊሆነን ጌታ መጣ፡፡ (ማቴ.9፥12 ፤ ገላ.5፥1) ነቢያት
በእስራኤል ታሪክ፥ ዘመነ ሰላም ከሆነ በአህያ ተቀምጠው፣ መነሳንስ ይዘው ይታዩ ነበር። ጌታም በአህያዋና በውርንጫዋ አንፃር እኛን እንደሚፈልገን እየነገረን ነበር። የክብር ዙፋኑን በእኛ ዘርግቶ በመቅደስ ሰውነታችን
ሊያድር ጌታችን መፈታታችንን ወደደ፡፡ በእርግጥም
፦ የእኛን ማደርያነትን የወደደ ጌታ እንደምን ያለ ድንቅ ነው!!!
ለጌታ የምናስፈልግ ውድ ማደርያዎች እኛ መሆናችንንና ማደርያችንንም
ለቅዱስ መሥዋዕት እንደሚገባ ባለ ቅድስና መጠበቅና ማቅረብ እንዳለብን “ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት
አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ” (ሮሜ.12፥1) በማለት በመስቀሉ ፍቅር ተለምነናል፡፡ አህዮቹ ጌታ
እንዲቀመጥባቸው ሙሉ ፈቃዳቸውን ሰጥተዋል (አቅርበዋል)፤ አማኞች እግዘአብሔርን ለማገልገል ራሳችንን ማቅረብ ያለብን “ብልቶቻችንን
የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርገን ለኃጢአት ባለማቅረብ ፤ … የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርገን ለእግዚአብሔር ማቅረብ” አለብን፡፡ (ሮሜ.6፥13)
የታሰሩትን
አህዮች በተመለከተ በዙርያቸው የነበሩት ሰዎች ብዙ ቢሉም፥ ጌታ ግን ለላካቸው ደቀ መዛሙርቱ “ለጌታ ያስፈጉታል በሉ።” አላቸው፡፡ እርሱ ከጠራን ከልካይ (ማር.10፥49) ፣ ያስፈልጉኛል ካለ ማንም ምንም ማለት አይቻለውም፡፡
በእርግጥ ሁላችን ለጌታ እናስፈልገዋለን ፤ ስለምናስፈልገውም ነው፥ እርሱ እኛን ፍለጋ ከሰማይ አድራሻው ወደምድር የመጣው፡፡
ስለዚህም “ጌታ እኔን ትቶኛል ፣ ረስቶኛልም” ማለት
አይቻለንም፡፡
ፍለጋውን በተመለከተም ከጌታ በቀር በእኛ ላይ
ማንም ሥልጣን የለውም ፤ ለዚህም ነው ደቀ መዛሙርቱን “የተዉአቸው” (ማር.11፥6)፡፡ እርሱ ፍለጋውን ከገነት(ዘፍጥ.3፥10)
(ከቤተ ልሄም) እስከ ቀራንዮ በማድረግ ፤ በዘላለም ፍቅርና በደም አትሞ በትልቅ ዋጋ በመግዛት አጊኝቶናል፡፡ (ሉቃ.19፥10
፤ 1ቆሮ.6፥20 ፤ 1ኛ ጴጥ.1፥19)
ከአህያይቱና ውርንጫይቱ መገኘት በኋላ ጌታችን በመሢህነት ማዕረጉ
ወደኢየሩሳሌም በታላቅ ዕልልታና ደስታ ሲገባ “ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ እያነጠፉ (ማቴ.21፥8) ፣ ልብሳቸውን በመንገድ
ላይ አንጥፈው ፥ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቈረጡ በማንጠፍ (ማር.11፥8) ፣ የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው (ዮሐ.12፥13) በንጉሥነት ማዕረግ (2ነገ.9፥13) ሊቀበሉት ወጡና ፦ ሆሣዕና ፤ በጌታ
ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው እያሉ ጮኹ። ጌታችን ሆሳዕና ሊባል ይገባዋል ፤ የሚያድነውን ጌታ ሆሳዕና (አሁን አድን)
መባሉ የሚገባም ነው፡፡ እርሱ መድኃኒትና አዳኝ መሆኑን በገሊላ እንዳዩት መሲህነቱን መሰከሩለት፥ ስለዚህም ሆሳዕና በማለት ዘመሩለት፡፡
የጌታችንን
መድኃኒትነት መመሥከራቸው ሞቱን መመኘታቸው ነው ፥ መድኃኒት ሊሆን ሞት ይገባዋልና፡፡ ጴጥሮስ ጌታን እንዳይሞት ሲመኝና ሲከላከል፥
ሆሳዕና እያሉ የዘመሩለት ብዙ ሕዝቦች ደግሞ መድኃኒትነቱን ሽተው እንዲሞትላቸው ወደዋል፡፡ በእርግጥም ጌታችን የተዘመረለት ለሞቱ
ነውና ክብር በአርያም ላንተ ይገባሃል ልንለው ፤ የሞተልንና በሞቱም የገዛን ጌታ ሆሳዕና መባል ይገባዋል፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment