Friday 13 March 2015

“የምርጫ 97 ቀይ ስህተት እንዳይደገም ”ቤተክርስቲያን ድርሻዋን ብትወጣስ?!


                        Please read in PDF

   
     ቤተ ክርስቲያን አግባብነት ላላቸው የመንግሥት ሕጎችና ሥርዓት ሁሉ ልትገዛ እንደሚገባት ታላቁ መጽሐፍ “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና … ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ከሁሉ በላይ ነውና … ” (ሮሜ.13፥1 ፤ 1ጴጥ.2፥13) በማለት ያስቀምጣል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ሆነ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህንን ቃል የተናገሩት በዚያ ዘመን ምድርን ይገዙ ለነበሩት ሮማውያን ቄሳሮች ፥ ደቀ መዛሙርት እንዲገዙና እንዲታዘዙ በማሳሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ባዕለ ሥልጣናት “ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ (ከእግዚአብሔር) ተልከዋልና … በጎ እያደረጋችሁ፥ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና፡፡” (1ጴጥ.2፥14-15)

   በእርግጥም ክርስቲያኖችን በጠላትነት አይተው ይገድሉና ያሰቃዩ ለነበሩ ሮማውያን ቄሳሮች የዚያ ዘመን ደቀ መዛሙርት በመታዘዝ ተገዝተዋል፡፡ በቄሳሮች ዘመን የክርስቲያኖች መታረድና የመሰደዳቸው ምክንያቱ የእነርሱ “እግዚአብሔርን ለማያውቅ ለአህዛብ ንጉሥ አንገዛም” ባይነት ሳይሆን ቄሳራውያን ነገሥታት ሥልጣናቸውን በልጥጠው ራሳቸውን በጌታ ቦታ አስቀምጠው “ከኢየሱስና ከቄሳር ጌታ ማነው?” ለሚለው ቄሳራዊ አምልኮን ለሚሻ ጥያቄ “ኢየሱስ ጌታ ነው” የሚል የተቃውሞ እውነተኛ ትምህርት በማስተማሯ ምክንያት ነው፡፡
   እናም የጌታን ስሙን ፤ ሞቱንና ትንሳኤውን ከመስበክ ውጪም በሌላ በምንም ሰበብና ችግር የተከሰሰ አንድም ሐዋርያ ከመካከላቸው አልተገኘም፡፡ የዛሬዎቹን አገልጋዮችና አማኞችን በዚህ መንፈስ ስንቃኛቸው ፥ የሚበዙቱ ካለመገዛትና ካለመታዘዝ አልፈው ከኣለሙ በባሰ ክፋትና ግልጥ በሆነ የህግ ድንጋጌዎችን በመጣስ ፊት አውራሪዎች ናቸው፡፡
   ቤተ ክርስቲያን እንደቀደመው ዘመን ከተልዕኮዋ በመዘለል ከመሪዎች ተርታ በመቀመጥ ለመኖር ዛሬ ዕድሉም ፤ ጊዜውም አይሰጣትም ፤ የላትምም፡፡ ነገር ግን መገዛት ባለባት ነገር እየተገዛች መሪዎችን መምከር ፣ ለመሪዎች መጸለይ (1ጢሞ.2፥1-2) ፣ ሲያጠፉ መውቀስና መገሰጽ የሚያስችል አቅምን ማጎልበት ግን እንዳለባት መታለፍና መዘንጋት የሌለበት ትልቅ ሥራ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህም መሪዎች ዙፋናቸው በጉበኞች እንዳይወረርና ድኻው እንዳይበደል ፣ አጋንንት በዙፋናቸው ዙርያ ረብበው ደምን እንዳያፈሱ ቤተ ክርስቲያን የድርሻዋን ልትወጣ ይገባታል፡፡
    ስለዚህም ስለሰላማዊ መሪና መንግሥት ከማሰባችን በፊት ወደበትረ ሥልጣን አመጣጣቸውም ሰላማዊና ያለደም መፍሰስ እንዲሆን ለሥልጣን ባለቤት ለእግዚአብሔር ተግተን በመጸለይ ልንነግረው ይገባናል፡፡ ብዙዎቻችን አገራችን መሪዎችን “በዲሞክራሲያዊ ምርጫ” ወደዙፋን እያመጣች ስለመሆኑ መስማት ከጀመርን አመታትን አስቆጥረናል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ምርጫ 1997 ዓ.ም የብዙዎች ንጹሐንንና የሌሎች ደም በመፍሰሱ በሁላችን ዕዝነ ልቡና የማይረሱ ብዙ አስቀያሚ ትዝታዎች ጥሎብን አልፏል፡፡ ማንም ቢሆን እንዲህ ባለ ሁኔታ የዚያን ያህል ብዙ ቁጥር ያለው አይደለም ፥ የአንደም ሰው ደም መፍሰስ የለበትም ብሎ ለማሰብ ሰው መሆን ብቻ እንደሚበቃው አምናለሁ፡፡
     በሌላ ዕይታ እጅግ አሳዛኙ ነገር በምርጫ 1997 ዓ.ም ያ ሁሉ ሰው በሞተና ደሙ ፈሶ ፤ አካሉ በጎደለበት ወቅት ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በስተቀር የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የተከሰተውን ድርጊት እያዩ እንዳላዩ ሆነው ዝምታን መርጠዋል፡፡ ምናልባትም “የገዛ ወገን ይቅርና” ሰው የሞተ ያህል እንኳ የተሰማው የለም ወይ? ያስብላል የየዚያኔውን ዝምታ ላስተዋለ፡፡ በኋላ ላይ በዚህ ጉዳይ የሞቱትንና የተጎዱትን እንዲጣራ  በመላው ሀገሪቱ የተሸመው ኮሚቴም አጣርቶ  የሞቱ ፤ የቆሰሉና ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች ባቀረበም ጊዜ ይህንንም አይተው እንኳ አለመቃወማቸውና አለመገሰጻቸው ምነው በግ በጨካኝ ተኩላ ሲነጠቅ ግድ የማሰተው እረኛ ምን አይነት ምንደኛ እረኛ ነው ያስብላል? (የታሪክ ጥቁር ነጥብ!!!)
  ይህን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ አደራ ነበረባት ፤ አለባትም፡፡ ቃሉ እንደሚለው ማንም ይመረጥ፥ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ጭካኔና ቀይ ስህተት እንዳይደገም ብሔራዊና አገራዊ በሆነው በዚህ ጉዳይ ላይ በዚህ በጸሎትና በጾም ዘመኗ ከፊታችን ያለውን ምርጫ በማሰብ “ርዕስ” አድርጋ ልትጸልይበት ፣ ልትጾምበትም ይገባታል፡፡
  ከዚህ ባሻገር ምናልባት ድርጊቱ ዳግም ቢከሰትና ደም ቢፈስ፥ ቤተ ክርስቲያን ነገሥታትን መገሰጽ የሚያስችል አቅም (ማቴ.10፥19-20) ከመንፈስ ቅዱስ በመቀበል፥ ከመጸለይና ከመጾም አልፋ በልክ የመገሰጽ ድርሻዋን ልትወጣም ይገባታል፡፡ የመንግሥት ባዕለ ሥልጣናት በእብሪትና በማን አለብኝነት መንፈስ ደም የሚያፈሱ ከሆነ “ለባዕለ ሥልጣናት ተገዙ ፤ ታዘዙ” የሚለው መርሕ አይሰራም፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን የሰው መገደልና ደም መፍሰስን እንዳላየ ሆና በማለፍ ራስዋን ከፍርድ ማስመለጥ አትችልምና ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለባዕለ ሥልጣናትና ለመንግሥት ስትገዛ ፥ መንግሥትም ደም ከማፍሰስ ፣ በሥልጣን ጉልበት ሌሎችን ከመጫንና ሃሳብን በጉልበት ከመጠምዘዝ … ሊቆጠብ ይገባዋል፡፡
    ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን “እገሌን ምረጡ ፤ እገሊትን አትምረጡ” የሚል ፖለቲካዊ ሃሳብን ከማራመድ አፏንና ህሊናዋን ሰብስባ በመከልከል ፤ የሚመጣውና ያለው መንግስት ደም የማፍሰስና ሌላውን የመግደል ሃሳብ እንዳይጣባው አጥብቃ በመትጋት ርዕስ አድርጋ ልትጾም ፤ ልትጸልይም ይገባታል፡፡ ምናልባት አሁን ባለንበት በዚሁ በዓቢይ ጾም ውስጥ ይህንን እንደርዕስ አድርጋ ቤተ ክርስቲያን ድርሻዋን ብትወጣስ??? አይገባምን?!
   ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ልበ ብርሃን መሆንን ያድለን፡፡ አሜን፡፡    

1 comment:

  1. Zendro qnjit slemaynor yeman dem yifesal bleh new bro? Xenkara xenkara yetebalut partiwoch rasu be eprdf kechewata wuch honewal so mnm ayasegam woyane zendrom ashenefku yilal:: ke mrchaw befit wuxetu yemitaweqbet bchegnawa hager ETHIOPIA lol

    ReplyDelete