Thursday 28 August 2014

የመቶ አለቆቹ (የመጨረሻ ክፍል)





4. የመቶ አለቃው ዩልዮስ (ሐዋ.27፥43)

“የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ያድነው ዘንድ አስቦ ምክራቸውን ከለከለ … ”
      ቅዱስ ጳውሎስ ለቁጥር በሚታክቱና ምላሳቸው በሳለ ከሳሾች መካከል “እየተብጠለጠለ” ቅንጣት ታህል አለመፍራቱን ሳስብ የጌታ ኢየሱስ “ … አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና፡፡” የሚለው የትንቢት ቃል መፈጸሙን ትዝ ይለኝና ልቤ ይረካል፡፡(ማቴ.10፥19-21) የእስያ አይሁድ፣ የኢየሩሳሌም አይሁድ፣ ጠርጠሉስ፣ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ … ስለእርሱ በጎነት የላቸውም፡፡ ፊስጦስም እንደቀደሙት ባዕለ ሥልጣናት ክፉ ልማድ አይሁድን ደስ ለማሰኘት ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ተመልሶ እንዲዳኝ ይጐተጉተዋል፡፡(ሐዋ.25፥9፤21)
        ቅዱስ ጳውሎስ ነገሩ እንዳላማረ፤ ፊስጦስ ራሱ ወደአይሁድ እንዳደላ ያወቀ ይመስላል፡፡ አሁን በቆመበት የሮማ የፍርድ ችሎት ፊት መዳኘት እንደሚፈልግ በጽናት ተናገረ፡፡ ምክንያቱም በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቢዳኝ የልባቸውን ክፋት ያውቀዋል፡፡ ይገድሉታልና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ለሌለው ሞት ራሱን አሳልፎ አልሰጠም፡፡(ዮሐ.8፥59) ጳውሎስ “ሰማዕትነት አያምልጠኝ” ብሎ ለስንፍና ሞት ሳይሸነፍ ወደቄሳር ይግባኝ በማለት በሮማዊ ዜግነቱ የተሰጠው መብቱን ተጠቀመበት፡፡(ሐዋ.25፥11)

       ፊስጦስ የጳውሎስ ይግባኝ የማለት ነገር ጨንቆታል፡፡ ለቄሳር ይግባኝ ያለው ጳውሎስን ወደ ቄሳር ለመላክ ለቄሳር ተጨባጩን የጳውሎስን ክስ በማስረጃ አጠናቅሮ መላክ አለበት፡፡ ጳውሎስንም መርምሮት “እኔ ግን ሞት የሚገባውን ነገር እንዳላደረገ አስተዋልሁ … ”(ሐዋ.25፥25) በማለት ምንም ሊያገኝበት አልቻለምና፤ ንጉስ አግሪጳ የክሱን ምክንያት ለማጣራት እንዲረዳው ይማጸናል፡፡ ከዚህም የተነሳ ንጉስ አግሪጳና ሌሎችም መርምረው “ይህ ሰው እኮ ወደ ቄሣር ይግባኝ ባይል ይፈታ ዘንድ ይቻል ነበር …” ብለው ስለንጽዕናው ተነጋገሩ፡፡(ሐዋ.26፥32)
      ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስና ሌሎችም እስረኞች ወደ ሮም እንዲሄዱ ነገር ተቆረጠ፡፡ ያደርሳቸውም ዘንድ ለመቶ አለቃ ዩልዮስ ተላልፈው ተሠጡ፡፡ ጉዟቸውን ባደረጉ በማግስቱ በሲዶና ሳሉ የመቶ አለቃ ዩልዮስ፦
1.    ለቅዱስ ጳውሎስ ደግነትን አደረገ (ሐዋ.27፥3)
     የወንጌል እግር እንዳይታሰርና አገልጋዮቿ እየተቻኮሉ ያደርሱ ዘንድ የመጀመርያይቱ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ሌሎች ድሆች አማኞችንና  አገልጋዮችን በመርዳት በጣም ይታወቃሉ፡፡ (ሐዋ.4፥34-37፤ 11፥19፤ ሮሜ.15፥26፤ 2ቆሮ.8፥2፤ ፊሊ.4፥16) ይህን የእርዳታ መዋጮ ደግሞ የታመኑቱ የጌታ ደቀ መዛሙርት ከቦታ ወደቦታ ያዘዋውሩ፤ ያደርሱም ነበር፡፡ በአንዱ ቤተ ክርስቲያን ያሉ ምእመናን በረሃብ፣ በእርዛት፣ በቤተሰብ መፈናቀል … ሲጎዱ፥ የሌላው ቤተክርስቲያን ዝምታ የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን አንዱ በሽታ ነው፡፡ በተለይ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ብር በባንክ አከማችተው በገጠር ያሉትን ምዕመናንና አገልጋዮች ሲቸገሩና ሲጎሳቆሉ ከመርዳት ይልቅ “በምን አገባን መንፈስ” ቁልቁል ማየት ያልታፈረ ነውር ሆኗል፡፡
    ቅዱስ ጳውሎስ ወዳጆቹን እንዲጎበኝና ለጉዞው የሚያስፈልገውን ዕቃዎች፤ እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ የተዋጣውን መዋጮ ከወዳጆቹ ሊወስድ ባለ ጊዜ የመቶ አለቃው በደግነት መንፈስ ፍጹም ተባበረው፡፡ በጐነታችን እንደነዚህ ካሉ አህዛብ ካልበለጠ የክርስቶስ ነን ያልንበትን የቀደመው ዘመናችንን ንስሐ በመግባት ልናድሰው ያስፈልገናል፡፡(ማቴ.5፥46) አህዛባዊው የመቶ አለቃ ለማያውቀው ወገኑ(ያውም በህጉ ለተከሰሰ) ይህን ካደረገ እኛ ምነው ለምናውቀው ወገናችን ክፋትና ስም ማጥፋት እንጂ በበጐነት መራራት አልታይ አለን?!
2.   እንዳይገደል ተጠነቀቀለት (ሐዋ.27፥43)
    ወደሮም የተደረገው “ጉዞ በጥፋትና በብዙ ጉዳት እንዲሆን፤ ጉዳቱም በህይወት እንጂ በመርከቡና በጭነቱ እንዳልሆነ” ቅዱስ ጳውሎስ ቢናገርም የመቶ አለቃው ዩልዮስ ግን ከቅዱስ ጳውሎስ ቃል ይልቅ የብዙሃኑን ቃል አምኖ ተቀበለ፡፡ የመቶ አለቃው ከጳውሎስ ይልቅ የመርከቡን መሪና ባለቤት ያመነው ምናልባት የተሻለ፤ የበዛ ድምጽ ስላገኘ ወይም የተሻለ ሙያዊ ብቃት እንዳላቸው ስላሰበ ይሆናል፡፡ ዛሬ ላይ ጥቂቶች ያመኑት እውነት የመረረን አዕላፋት ክፋትን እንደውኃ ሲጠጡና ሲጨልጡ ስላየን እንጂ እግዚአብሔር እንዳለበት እርግጠኞች ሆነን አይደለም፡፡ የአለም ምሁራን ጣፋጭ ብለው ከመከሩት ምክር ይልቅ እግዚአብሔር ያለበትና የመከረው መራራ ምክር ዕረፍት አለበት፡፡
    እንደ መርከቡ መሪና እንደባለቤቱ ሳይሆን አውራቂስ የተባለው አውሎ በመጣ ጊዜ ጳውሎስ የተናገረው ሆነ፡፡ ጉዳትና ጥፋቱ ለአስራ አራት ቀናት ፀሐይና ኰከብ ሳያዩ፣ ምግብን አጥተው … እንድናለን የሚል ተስፋቸው እስኪቆረጥ ድረስ ተጓዙ፡፡ የሆነው ነገር ይጨንቃል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ጥፋቱን ቀድሞ በጌታ አይን ያየና የደረሰውንም ከባድ ኪሳራ የተረዳ ቢሆንም፤ ከጉዳቱ በኋላ ሳያዝን እስረኛነቱን ረስቶ በመርከቡ ውስጥ የነበሩትን ነፍሳት እንደአባት ማጽናናት ጀመረ፡፡
   ጌታ ራሱ በዚህ ሰንሰለት ሠርቶ በከበበው መከራና እጅግ በጨለመበት ሰዓት ከቅዱስ ጳውሎስ አጠገብ ቆሞ አበርትቶታል፡፡ እስረኛው ለተሳፋሪዎቹ ከጌታ የተቀበለውን የማጽናናት ቃል ሁሉንም ነገራቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ወደምድር ቀርበው ወደባህሩ ዳርቻ ነጂው ሊያቀርብ የሚችለውን ጥረት ባደረገ ጊዜ መርከቡ ከመሬት ተጣብቆ ስለነበር ማዕበሉ መርከቡን ሊሰብረው ሆነ፡፡ ስለዚህም ተጓዦቹ ሁሉ ውኃ ውስጥ ዘለው በመግባት በዋና እንዲድኑ ተወሰነ፡፡ አንዳንዶች ግን ጳውሎስ የነገራቸውን የመጽናናት ቃል ዘንግተው ሊያመልጡ አስበው ነበር፡፡ ጌታ ፊት ለፊት እየተናገራቸው እነርሱ ግን ደንዝዘው ቃሉን ረስተው እንደዚህ ባለ ክፋት መጠመዳቸው አግባብ አልነበረም፡፡
    ይህ በሆነ ጊዜ ወታደሮቹ እስረኛ እንዳያመልጥ ፈርተው የሚያመልጥ ካለ ለመግደል መከሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የመቶ አለቃው ዩልዮስ ምናልባት ቅዱስ ጳውሎስ በመካከል ሊገደል ይችላል ብሎ ስላሰበ “የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ያድነው ዘንድ አስቦ ምክራቸውን ከለከለ … ”(ሐዋ.27፥43) ይለናል፡፡ የመቶ አለቃው እስረኞች እንዲገደሉ የታቀደውን ዕቅድ ከማክሸፉም በላይ ለጳውሎስ እጅግ ተጠንቅቆለታል፡፡ እስረኞቹን በተለይም ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ያህል እንዲያምን ያደረገው ነገር ግን ምን ይሆን?! ጳውሎስ የሰበካት የጌታ የመንግስት ወንጌል ትሆንን?! በእርግጥም የመቶ አለቆቹ የሚደነቅ ነገር ተገኝቶባቸዋል፡፡ እኛስ ምን አስተውለን ይሆን?!
    ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን፡፡ አሜን፡፡

ተፈጸመ፡፡ 

No comments:

Post a Comment