Monday 25 August 2014

የመቶ አለቆቹ (ክፍል አራት)



የሮማ መቶ አለቆች
3.2. በሰፈሩ ውስጥ(ሐዋ.23፥10)

       ቅዱስ ጳውሎስ ከመገረፍና ጭካኔ ከተመላበት ድብደባ በኢየሱስ መንፈስና ብርታት፤ በየመቶ አለቃውም ቅንነት ተርፏል፡፡ በማግስቱ ሻለቃው አይሁድ እርሱን የከሰሱበትን እርግጡን ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ አስቦ ከፈታው በኋላ፤ ሸንጎውንና የካህናት አለቆችን እንዲሰበስቡ አዞ፤ ጳውሎስን በፊታቸው አቆመው፡፡ የአይሁድ ሸንጎ እንዲሰበሰቡ የተፈለገበት ምክንያት ሻለቃው የጳውሎስን ጥፋት ማወቅ ስለተሳነው የእርሱ ወገኖች እንዲያጣሩ ነበር፡፡ ግን ዳኝነቱ ቀድሞ በአድሎአዊነት አጋድሏል፡፡
   ቅዱስ ጳውሎስ በሸንጎው ፊት በቆመ ጊዜ ሁለት የማይስማሙ ወገኖች ጳውሎስን ለመክሰስ ግን ተስማምተው ቆሙ፡፡ ሁል ጊዜ ይደንቀኛል፡፡ የጌታ የሆኑ ክርስቲያኖችን ለመግደል፤ ለማሳደድ፤ ለመክሰስ ሁለት ፈጽሞ የማይስማሙ አካላት ይፋቀራሉ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ በሁለት ፍጹም ተቃራኒ የእምነት አካላት የተከሰሱ አማኞችን የአለማዊ ፍርድ ቤት ችሎት እየደነቀው የማየት ዕድል አጋጥሞታል፡፡ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን አብረው ለመኖር አይስማሙም፣ ይበላላሉ፤ ክርስቶስ ኢየሱስንና እንደጳውሎስ ያሉ አማኞችን ግን ለመክሰስ ከባልና ሚስት ይልቅ ይዋሃዳሉ፡፡

   ሁለት ተቃራኒ አካላት ሊከሱት እንዳለ የተረዳው ሐዋርያው፥ የጥበብን መንገድ ተጠቀመ፡፡ “ጳውሎስ ግን እኵሌቶቹ ሰዱቃውያን እኵሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል ብሎ በሸንጎው ጮኸ። ይህንም ባለ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጥል ሆነ፤ ሸንጎውም ተለያየ።”(ሐዋ.23፥6-7) በእርግጥም ኃጥአን ክፋትን የተሞሉ ናቸውና ሰላም የላቸውም፡፡(ምሳ.12፥21፤ኢሳ.48፥22፤57፥21) ከሁሉ ይልቅ ደግሞ በእግዚአብሔርና የእግዚአብሔር በሆኑት ላይ የሚያምጹና የሚያደቡ አድማቸው የሠላም ቢመስልም ግና ፍጹም ሠላም የላቸውም፡፡
       ጠባቸው ገደቡን በጣሰ ጊዜ “የሻለቃው ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ጭፍሮቹ ወርደው ከመካከላቸው እንዲነጥቁት ወደ ሰፈሩም እንዲያገቡት አዘዘ።”(23፥10)
    በሠፈሩ ሳለ ቅዱስ ጳውሎስ አጽናኙ ጌታ በጸናው ሌሊት፤ በመከራ ተከቦ ሳለ በአጠገቡ ቆሞ “አይዞህ” በሚል ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ተናገረው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ጌታ የተናገረው ስሙን እየመሰከረና በሚጠሉትም መካከል ተከቦ ሳለ ነበር፡፡(ሐዋ.18፥9) ዛሬ ደግሞ በከሳሾቹ ፊት ሰው ሁሉ ርቆት ብቻውን እያለ አጽናኙ ጌታ በቀኙ ቆሞ አጽናናው፡፡ እውነተኛ የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምንም መከራ ቢገጥማቸው፣ ምድር ሁሉ የእነርሱ ከሳሽ ሆኖ ቢገኝ፣ አንዳች ከጎናቸው የሚቆም ባያገኙ … ትልቁ ጌታ ሁሉ ነገራቸው ሆኖ በአጠገባቸው ይቆማልና፤ ሁልጊዜም በፊታቸው ይታያልና በልባቸው አይታወኩም፡፡ (መዝ.15፥8) በስሙ የተጠላን ፣ ስለእርሱም የተገፋን፣ የአለሙን ርኩሰት ስለመጠየፍ በብዙ የተሰበርን … ቀኑን ሁሉ ደስ ሊለን ይገባናል፤ ጳውሎስን ያገኘች ማጽናናቱ ታገኘናለችና፡፡
   ብዙዎቻችን በጎ ምስክርነታችን በመንፈሳዊ ቤተሠቦቻችን መካከልና በህንጻ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን በሠፈር ውስጥም አለ፡፡ ጌታ ጳውሎስን ያጽናናው በሠፈሩ ውስጥ ነው፡፡(ሐዋ.23፥10) ሰው ለሠራው ህንጻ ተጠንቅቀን ክርስቶስ ለሞተለትና በሰው ላልታነጸው ድንቅ ህንጻ ሰውነታችን ግን አለመጠንቀቅ እንዴት ያለ የልብ ዝገት ነው?!
    ቅዱስ ጳውሎስ በሠፈር ውስጥ ሳለ ከአርባ የሚበልጡ አይሁድ ጽኑ መሐላ ተማምለው፤ ጾምን ጾሙ፡፡ መሐላውና ጾሙ ስለክፋት ይኸውም ጳውሎስን ስለመግደል እንጂ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት በማሰብ አልነበረም፡፡ በመልካምነት ካባ የኃጢአትን ነውር መፈጸም ፈሪሳውያን አይሁድ እጅግ የተካኑበት ነው፡፡(ማቴ.23፥5፤14፤27) ናቡቴን የአይሁድ ሽማግሌዎች ሲያስገድሉት የጾምን አዋጅ አስነግረው ነበር፡፡(1ነገ.20፥12) መንፈሳዊ ፍትፍት በሚመስል ገበታ ላይ የኃጢአትን ምርቅ መሰነግ በይሁዳ ህይወት ሲነበብም እናያለን፡፡ የወዳጅ በሚመስል መሳም ለጠላት ስለት አሳልፎ መስጠት፡፡(ሉቃ.22፥48) እንዲሁ ጳውሎስንም ለመግደል በጾም ላይ ናቸው ፡፡
     የሚያሳዝነው ያልተለወጠ ነገር ዛሬም ማየታችን ነው፡፡ “በቅድስናው ሥፍራ” የሚሠራውን የምዝበራና የሙስና ሥራ በአለሙ ውስጥ ያለ አይመስልም፣ በጥቂት ያይደለ መነኰሳት መካከል የሚወራው ግብረ ሰዶምና ዝሙት የተፈቀደ ያህል ምድሪቱን ማካለል ይዟል፤ ኃጢአትን ለመፈጸም ፍቃድ ማግኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የሚሸራርፍና እጅ ጠምዝዞ የሚተረጉም ትውልድ ከፊት ይልቅ በቅሎና በዝቶ ታይቷል … ፡፡ ጌታ ይቅደመን፡፡ አሜን፡፡
  ጳውሎስን ለመግደል መማማላቸውንና ጾምን መያዛቸውን የሰማው የጳውሎስ የእህቱ ልጅ ወደሰፈሩ ገብቶ ለጳውሎስ በነገረው ጊዜ፥ ጳውሎስ አንዱን የመቶ አለቃ ጠርቶ ወደሻለቃው ይህን ልጅ እንዲያስገባው ለመነው፡፡ የመቶ አለቃው በቅንነት እሽታውን ገለጸ፡፡ ልጁም የሆነውን ሁሉና ምክራቸውንም ለሻለቃው ነገረው፡፡ ሻለቃውም፦
1.     አለህግ እንዳይሞት ወደደ፡፡ ሻለቃው የህጻኑን ልጅ ቃል ማመኑ ይደንቃል!! የአገሬን ታሪክ ሳጠና በህግ ከሞተው አለህግ የሞተው ይበዛብኛል፡፡ በዚህ ሁሉ ባፈሰስነው ደም ንስሐ ሳንገባ ማደግና መለወጥን፤ ስለአገር አንድነት መጠበባችንና መጨነቃችን ምን ያህል ከመንፈሳዊነት አለም እንደጐደልን ያሳያል፡፡
2.    ፈጣን እርምጃ ወሰደ፡፡ በዚያው ሌሊት ሁለት የመቶ አለቆች “ወደቂሣርያ ይወስዱት” ዘንድ አዘዘ፡፡ “የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል” የሚለው የእውነተኛ የህግ ባለሙያዎች ንግግር ይህን እውነት ያጸናዋል፡፡ ለአገር ልማት መሻሻል ጠር ከሆኑት አንዱና ዋናው “የኮሚቴው ውሳኔ” መዘግየት ነው፡፡ ይህ በሽታ ዛሬ ቀጥታ ቤተ ክርስቲያንን ወሯታል፡፡ ማን ነበር “ሥላሴ በኰሚቴ ቢሰሩ የእስራኤል ልጆች ዛሬም ከግብጽ አይወጡም ነበር” ያለው?! ሻለቃው ወዲያው እርምጃ ባይወስድ ብዙ ችግር ይፈጠር ነበር፡፡
የመቶ አለቆቹ፦
1.     በሠፈሩ ውሰጥ የጳውሎስን የእህት ልጅ ያደመጠውና የተወጠነውን ሴራ ለሻለቃው እንዲናገር በበጎ ህሊና የፈቀደው የመቶ አለቃ ቅንነቱ ይደንቃል! የመቶ አለቃው መታዘዝ ጳውሎስን በእውነት ታድጎታል፡፡(ሐዋ.23፥30) በተለያየ በጥበቃ ሥራ የሚሰማሩ ወገኖች እንዲህ ያለ ቅንነትን ከዚህ የመቶ አለቃ ሊማሩ ይገባቸዋል፡፡ ለትልቁ “አለቃ” ብቻ ሳይሆን እንደጳውሎስ እህት ልጅም ላሉ ሰዎች የመታዘዝ የልብ ዝንባሌ ሊኖራቸው ይገባል፡፡
2.    ከሠፈሩ ውጭ ይዘውት ሲወጡ በእርሱ ላይ ምንም ጉዳት አላደረሱበትም፡፡ ወዳጅና ወገን በመራራ ጥላቻ ተይዞ ሊገድል ሲያደባ፥ ጌታ ወዳጅ ያልሆኑትን እንደእናት ልጅ ያቀርባቸዋል፡፡ በእርግጥም የመቶ አለቆቹ ለጳውሎስ እጅግ ቅኖች ነበሩ፡፡
ጌታ እንዲህ ያሉትን ያብዛልን፡፡ አሜን ፡፡


ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment