Monday 18 August 2014

“ … እርሱን ስሙት” (ማቴ.17፥5)



እንኳን ለደብረ ታቦር መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ!!!



    ቃሉን የተናገረው አብ ነው፤ የተነገረለት ደግሞ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ … የሰው ልጅ “ምን እንደሚሰማ እዝነ ልቡናውን አለመጠበቁ” (ማር.4፥24) የህይወት ዘመኑን በጭንቅ እንዲጓዝ፤ ፈቃዱም ከፈጣሪው ይልቅ ወደፍጡር እንዲያዘነብል፤ ሊሰማ የሚገባውን የበላዩን ጌታ ትቶ ከጎን ያለችውን “ወዳጅ ሚስቱን” መስማቱም ማንነቱን ድካም፤ እሾህና አሜኬላ ደግሞ ዙርያውን ለመከበቡ ምክንያት ሆኗል፡፡(ዘፍ.3፥10-21)
     አዳም ሁሉን አዋቂውንና ሰምቶ ከመመለስ ቸል የማይለውን ጌታ አለመስማቱ፥ ለማይሰማውና በጭካኔ ለተሞላው ለሰይጣን አገዛዝ ማንነቱንና ነጻነቱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ የእስራኤል ልጆች ወደእግዚአብሔር እረፍት ያልገቡት ጌታ እግዚአብሔር በድምፁና በሙሴ አማካይነት እየተናገራቸው ከመስማት ይልቅ “እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን ወይስ አይደለም?”(ዘጸ.17፥7)፤ “ … ወደዚህ ክፉ ስፍራ ታመጡን ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? ዘርና በለስ ወይንም ሮማንም የሌለበት ስፍራ ነው የሚጠጣም ውኃ የለበትም።”(ዘኅ.20፥5-6) ብለው ፍጹም ድምጹን እየሰሙ እግዚአብሔርን በአመጻ ቃል በማስመረራቸውና አልታዘዝ በሚል ልብ በመከራከራቸው ነው፡፡(ዕብ.3፥7)

       ይህን እውነት፥ የዕብራውያን መልዕክት ፀሐፊ የምክር ቃሉን ሲጽፍ “ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ ልባችሁን እልኸኛ አታድርጉት” የሚለውን ቃል በሁለት ምዕራፍ ሦስት ጊዜ አጽንቶ ይጽፈዋል፡፡(ዕብ.3፥7፤15፤4፥70) እልኸኛነት አለመስማትን ያለፈ አለመታዘዝን በውስጡ ያዘለ የአመጽ ድርጊት ነው፡፡ እስራኤል ቃሉን እየሰሙ ነገር ግን እልኸኞች ስለሆኑ በቁጣው ነደዱ፤ ሬሳቸው በምድረ በዳ ወደቀ፡፡ ጸሐፊው ለተደራስያኑ ወገኖችም “እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ።”(ዕብ.4፥11) እያለ ወደፍጹሙ እረፍትና ሰንበት ወደክርስቶስ መግባትን ይመክራቸዋል፡፡
    አስተውሉ! ቃሉን መስማት ማለት ለቃሉ መታዘዝ ማለት ነው፡፡ ለቃሉ በመታዘዝ የማይኖር ሰው እርሱ ቃሉን ያልሰማ፤ ቃሉም የሌለው ነው፡፡ ብዙዎቻችን ቃሉን መስማትንና ለቃሉ መታዘዝን ለያይተን ነው የምናየው፡፡ ነገር ግን ቃሉን የሚሰማ እርሱ ለቃሉ የታዘዘው ብቻ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በምሳሌው እንዳስተማረን(ማቴ.21፥28) አባታቸው ያዘዛቸው ሁለቱ ልጆች አንደኛው እሺ እሄዳለሁ ብሎ የቀረ፤ ታናሹ ግን አልሄድም ብሎ በኋላ ተጸጽቶ የሄደ ነው፡፡ እሺ ብሎ ቃሉን ሰምቶ ከቀረው ይልቅ እምቢ ብሎ በኋላ ተጸጽቶ የሄደው የአባቱን ፈቃድ የፈጸመ እርሱ የታዘዘ ሰሚ ነው፡፡
    በተለያዩ ጉባኤያት ቃሉ ሲሰበክ እምቢ የሚሉ ሰዎች የሉም፡፡ ከንፈርን እየመጠጡ፥ እሺ የሚሉ እንጂ፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ብዙዎች ቃሉን አያደርጉትምና ሰሚዎች ናቸው ማለት ይቸግራል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የሚሰማውን ቃልና ራዕይ ቢቃወም የሚብስ ነገር እንደሚያገኘው ማስጠንቀቂያ ተሰጠው(ሐዋ.9፥5)፤ ልድያ ቃሉን እንደሰማች ታዘዘች(ሐዋ.16፥15)፤ ጌታ ቃሉን ሰምተው የማይታዘዙትን ብርቱ ወቀሳና ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው፡፡(ማር.4፥9፤23)
   አብ በደብረ ታቦር ስለኢየሱስ ከመሰከረው ምስክርነት አንዱ “ … እርሱን ስሙት” የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሔር በገነት ያኖረውን ቃሉን፣ የእስራኤል ልጆች እየተከተላቸው ያጠጣቸውን መንፈሳዊ ዐለት ባለመስማታቸው ፍጹም ተቀጥተዋል፡፡ ከጥንት የሰው ልጅ የኃጢአት ምንጭ እርሱን ፈጣሪ ቃል፤ አስገኚ ቃል ክርስቶስን አለመስማታቸው ነው፡፡ በደብረ ታቦር የባህርይ አባት አብ፥ የባህርይ ልጁ ክርስቶስን “እርሱን ስሙት” አለ፡፡ ነቢያት፣ አበው ቅዱሳን፣ መላዕክት ሁሉ እርሱን እንሰማ ዘንድ አዘዙን፡፡ ነገሩን፡፡ መሰከሩልን፡፡ ከሁሉ ይልቅ አብ በስሙ ያመንነውን ሁላችንን እንሰማ ዘንድ በፍቅር ተናገረን፡፡
    እግዚአብሔር በራዕይና በህልም የተናገራቸውን ሰምተው ስላልታዘዙ በከባድ ቅጣት ቀጥቷቸዋል፡፡ እንኪያስ ሥጋ ለብሶ የመጣውንና እንሰማው ዘንድ የመሰከረለትን ጌታ አለመስማትና ቃሉን በማቃለል አለመታዘዛችን እንዴት ላለ ቅጣት ይጥለን ይሆን? በብሉይ ሰምተው ካልታዘዙት በቀር ሁሉም ወደእረፍቱ ገብተዋል፡፡ በሐዲስም ቢሆን ባለማመን ጠንቅና ሰምተው የማይታዘዙቱ ወደእውነተኛው እረፍት ወደ ክርስቶስ ክብር እንዳይገቡ ግልጥ ነው፡፡ (ዕብ.3፥18)
     በደብረ ታቦር እንድንሰማ የተነገረንና የሰማነው “ያ ድምፅ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ከእውነተኛው የወንጌል ትምህርት የምንለይበትና የምንቆርጥበት” ስለት ነው፡፡ የምንሰማውና የምንሰብከው አብ የመሰከረውን “የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና ግርማ አይተን እንጂ ብልሃታዊውን ተረት ተከትለን አይደለም፡፡” (2ጴጥ.1፥16-19) የብሉይና የአዲስ ኪዳን ህልሞች፣ ራዕዮች፣ ምሳሌዎች፣ ትምህርቶች፣ ምክርና ተግሳጾች ሁሉ እንደቀስት የሚጠቁሙት ወደክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ የታዘዝነው ክርስቶስን ብቻ እንሰማ ዘንድ ነው፡፡ እርሱን አለመስማታችን ጆሮ ጭው ለሚያደርግና በወንጌል ፊት ለቀለለ ተረትና የአሮጌት ወሬ አሳልፎ ሰጥቶናል፤ ፓለቲካችንን አጠንዝቶታል፤ በጌታ ላይ ያለንን መደገፍ አጠውልጐታል፤ የምንበላውን የእህሉን ጉልበት ሰብሮታል፤ ትውልድ መቅኖ አጥቷል፤ መፍትሔ አምጪዋ ቤተ ክርስቲያን ግራ ተጋብታ ትውልዱም ፊቱን ወደዓለም ካዞረ ሰነባበተ … ፡፡
       ነገር ግን እርሱን መስማት የማይወሰድ መልካም ዕድል(ሉቃ.10፥42)፤ ደስ የሚያሰኝ የሙሽራ ድምጽ (ዮሐ.3፥29)፤ በእርጋታ የሚያስቀምጥና ከመከራ ሥጋት የሚያሳርፍ(ምሳ.1፥33)፤ ሰላማችንን እንደ ወንዝ ጽድቃንንም እንደ ባሕር ሞገድ የሚያበዛ(ኢሳ.48፥18)፤ እውነተኛና የሚቀድስ (ዮሐ.17፥17) ነውና፤  የደብረ ታቦሩን አማናዊ ብርሃን እርሱን አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስን መስማት ብቻ በሕይወት ያኖራል፡፡

 ብርሃነ መለኰቱ ሰምቶ መታዘዝን ለሁላችን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡

1 comment:

  1. tebarek betam des yemil tsihuf new!!! berta tsegawun yabzalih!!!

    ReplyDelete