Thursday 21 August 2014

በድንግል ማርያም ላይ የአይሁድ አሽሙር (የመጨረሻ ክፍል)



     አረጋዊው ቅዱስ ስምዖን የናዝሬቱን ህጻን ኢየሱስን ለግዝረት ወደቤተ መቅደስ በእናቱ ክንድ ታቅፎ በወጣ ጊዜ፤  ህጻኑን  ከእናቱ ክንድ ተቀብሎ የደስታና የሚያስጨንቅ ትንቢት ለህጻኑና ለእናቲቱ ተናገረ፡፡ እንዲህም አለ፦   “እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት።”(ሉቃ.2፥35) እመቤታችን ጥልቅ የመከራ ሥቃይ እንደምትቀበል የሚያመለክትና፤ ኢየሱስ ገና በስምንተኛ ቀኑ ሊሞት እንዳለው ለመጀመርያ ጊዜ ተነገረለት፡፡
     በራስ የሚደርስን መከራንና ስቃይን ገና በልጅነት መስማት ከማስደንገጥ አልፎ ያሰቅቃል፡፡ ድንግል ማርያም በነፍሷ ሰይፍ ማለፍ የጀመረው ጌታን መጽነሷ ከታወቀባት ከሦስት ወር ቆይታ በኋላ ከኤልሳቤጥ ዘንድ ወደናዝሬት ከመጣች በኋላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አይሁድ የጌታ በመንፈስ ቅዱስ አሠራር ከድንግል ማርያም መወለድ ሲያስተምር በነበረበት ዘመኑ እንኳ አልተቀበሉትምና፡፡
      ጌታ “አባታችን አብርሃም ነው” ብለው በባዶ ትምክህት የሚመኩትን አይሁድ “የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር፡፡ … እናንተ የምታደርጉት አባታችሁ ዲያብሎስ የሚያደደርገውን ነው” (ዮሐ.8፥38፤44) ባላቸው ጊዜ የመለሱት መልስ የአሽሙር ስድብ ነበር፡፡

    “አንተ የተወልድከው በዝሙት ነው” የሚለውን የአሽሙር ስድብ ድንግል ማርያም በነበረችበት ዘመኗ ሁሉ በጆሮዋ እየሰማች ኖራለች፡፡ የሰይፍ በነፍስ ማለፍ ወይም የነፍስ በሰይፍ መወጋት እንደትኩስ ቁስል ህመሙና ቁስሉ በየቀኑ የሚታደስ ነው፡፡ ድንግል ማርያም አይሁዳዊ እንደመሆኗ  ይህን የአሽሙር ስድብ ከወገኖቿ አይሁድ በተለይም ከፈሪሳውያን በየጊዜው ትሰማዋለች፡፡ ይህ ደግሞ የነፍሷን ቁስል በየቀኑ ያድሰዋል፡፡ የሥጋ ቁስል የሚታይ፤ የሚፈወስም ነው፤ የነፍስ ቁስል ከታመመው በቀር መረዳት ይከብዳል፡፡
    ድንግል ማርያም በጠባይዋ ብዙ የማትናገር እጅግ በጣም ዝምተኛና ነገርን በልቧ የምታሰላስል እናት ናት፡፡ አይሁድ ባለመታከት በአሽሙር ስድብ እየወጉ ሲያደሟት እርሷ ምንም መልስ መመለሷን መጽሐፍ አልዘገበልንም፡፡ ዝምታዋ ግን ዛሬም ለተሳዳቢዎችና አሽሙረኞች የሚናገረው ተግሳጽ አለው፡፡ ዛሬ ላይ ቁጭ ብዬ ስለድንግል ማርያም የዚያኔ በጌታ ዘመን የነበራትን ህይወትና አገልግሎት ሳስብ፤ “የእመቤታችን የድንግል ማርያም ልጆች ነን” የሚሉ አመጸኛ “የለየላቸው ተሳዳቢዎች” ከፊቴ ይደቀናሉ፡፡
    ወደፌስ ቡክና የተለያዩ ድህረ ገጾች ስገባ ስለድንግል ማርያም ሁለት ተቃራኒ ወገኖችን አስተውላለሁ፡፡ ስለድንግል ማርያም ጨርሰው መስማት የማይፈልጉና ሌሎች ደግሞ ባለመናገራቸው በጣም የሚቆጡ ወገኖችን፡፡ ከሁለቱም ወገኖች፤ አንዳንዴ ሌሎችም እየታከሉበት አስነዋሪ ስድቦች ሲንጸባረቁ አያለሁ፡፡ ሰይጣን በሁለቱም በኩል የተሳካለት ይመስላል፡፡ የአዲስ ኪዳንዋን የመጀመርያ አማኝ እናት በሌላው አንደበት አስጠልቶ፤ ሌላውን ደግሞ በአላስፈላጊ ጥብቅና በስድብ አሰልፎ፡፡
    የድንግል ማርያምን ቅድስና ከሚያጐሉና ከሚያደምቁ ነገሮች አንዱ በነፍሷ ስለት እያለፈ፤ ሳያቋርጥ ነፍሷ በአሉባልታ እየደማ፤ ባለመሰልቸት አይሁድ በአሽሙር እየሰደቧት እርሷ ግን የጌታን ፈቃድ በልቧ የምታሰላስል እናት በመሆኗ ነው፡፡ ትልቁ ትዕግስት ሥጋ ቆስሎ ሳይሆን ነፍስ እየደማ መታገስ ነው፡፡ የሥጋ ቁስል ያመረቅዛል፤ የነፍስ ቁስል ግን ያቅበዘብዛል፤ ያንቀዠቅዣል፣ ብዙ ያስለፈልፋል፡፡ የነፍስን ቁስል መታገስ ማለት መልካሙን ገድል የመጋደል ያህል ነው፡፡
    በእውነት የእመቤታችን የድንግል ማርያም ልጆች ከሆንን “የበዛ የታላቁ መጽሐፍ የምስጋና ቃል” እንጂ  “የሰላ የስድብና የአሽሙር አፍ” ሊኖረን አይገባም፡፡ ድንግል ማርያም የተማረችው ከእግዚአብሔር ነው፤ ልጆቿ የሆንም ከራሱ ከእግዚአብሔር ልንማር ይገባናል፡፡ ከጌታ የተማረች እናት ህይወቷ መጽሐፍ ነው፡፡ ተሰድባ ለመብቷ አትሟገትም፡፡ በአሽሙር ቢያደሟት መልስ አትሰጥም፡፡ ነፍሷ በብዙ እንባ ብትከበብም እርሷግን በጌታ ያመነች ናትና አንደበቷን አታረክስም፡፡
   ልጆቿ የሆንን በመከራ መታገስን ከህይወትዋ ታስተምረናለችና የህይወቷን ገጽ እናንብበው፡፡

    የጌታ ብርሃን ያግኘን፤ ይብራልን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment