Wednesday 13 August 2014

ድንግል ማርያምና የአይሁድ አሽሙር(ክፍል ሁለት)



ፈጣን ጉዞ ወደ ተራራማው የኤፍሬም አገር
   
    ድንግል ማርያም “እንደቃልህ ይሁንልኝ” ባለች ጊዜ እንደመንፈስ ቅዱስ አሠራር ህጻኑ በማህፀኗ ተፀንሷል፡፡ ይህ ነገር ከሆነ በኋላ ሳትቆይ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ወደዘካርያስ ቤት ተጓዘች፡፡ ከመልአኩ አንደበት የሠማችው የኤልሳቤጥ መፅነስ ሳያስደምማት አይቀርም፡፡ በእርግጥም ዝጉ ማህፀን ሲከፈት፤ አይቻልም የተባለው ሲቻል፤ አይሆንም ተብሎ የተደመደመው ሆኖ ሲታይ በእርግጥ ያስደምማል፡፡ ደስታ የበዛላቸው በአንድ ተገናኙ፡፡ “አንዱ ለአንዱ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው” እያሉ ሊያወሩ፡፡ አዎ! ሠላምታቸው እንኳ ለእግዚአብሔርን ክብርና አምልኮን በመስጠት የደመቀና የሚማርክም ነው፡፡

   ኤልሳቤጥ የድንግል ማርያምን እምነት “በጌታ ያመነች ብጽዕት ናት” ብላ ፈጽማ አደነቀች፡፡ ምንም እንኳ የኤልሳቤጥ ዕድሜ ከሰባ አመት በኋላ ቢሆንም አስራ ስምንት ዓመት ያልሞላትን የድንግል ማርያምን እምነት በግልጥ ተናገረች፡፡ ዛሬ ላይ ከሚታዩ የአብያተ ክርስቲያናት “ልክፍት” አንዱ “ታላላቆቹ” ሁሌ ስለእነርሱ እንጂ እነርሱ ከእነርሱ ለሚያንሱቱ መመስከር እንዳለባቸው በረሳ ማንነት ተይዘዋል፡፡ ኤልሳቤጥ ግን ስለድንግል ማርያም ጮኻ አሰማች፡፡ እምነቷን፤ በጌታ ላይ ያላትን መደገፍ አብዝታ ተናገረች፡፡ በዚህም ከሴቶች መካከል የተባረከች መሆኗንም ሳትሸሽግ መሰከረች፡፡ በእርግጥም የድንግል ማርያም እምነት ሊደነቅ የሚገባ እምነት ነው!!!
    ድንግል ማርያም፥ ኤልሳቤጥ የእርሷን ታላቅነት ብትመሰክርም እርሷ ግን በምስጋናዋ በመንፈስ ድኻ ሆና፥ ወራዳነቷንና አገልጋይነቷን ነበር የገለጠችውና የተናገረችው፡፡ በእርሷ ትልቁን ሥራ የሠራው እግዚአብሔር ራሱ ነው ስለሆነና ክብር ሁሉ ለእርሱ እንዲጠቀልል “ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።”(ሉቃ.1፥55) ብላ በምስጋና ቃል ተናገረች፡፡
  ድንግል ማርያም ከዚህ በኋላ በተራራማው አገር ለሦስት ወራት ያህል ተቀመጠች፡፡(ሉቃ.1፥56)


ከሦስት ወር በኋላ በአይሁድ መካከል
    ድንግል ማርያም ከሦስት ወር በኋላ ወደቤቷ ተመልሳ ስትመጣ ፅንሷ አድጎ፤ ማርገዟም ያስታውቅ ነበር፡፡ ባል ያላገባች ሴት የሚለውን፤ ከሦስት ወር መሸሸግ ጋር አንድ ላይ አጋጥመው በራሳቸው “እንድምታ” አይሁድ በክፉ ተረጐሙት፡፡ ብዙ ጊዜ የሰዎችን ንግግር ከሰማነው ሰው ከመረዳት ይልቅ በራሳችን ተርጉመን ድምዳሜ የመስጠት አባዜ አለብን፡፡ ዘመናችንን የመካሰስና የመነካከስ ያደረገብን  አንዱ ነገር ከተሰማበት ሳይሆን ከተወራበት ቀጥለን እኛም ስለምናወራውና የነገሩን የት መጣ ከመመርመር ስለምንሰንፍ ነው፡፡ ነገርን ታግሰን ከማጣራት ይልቅ የሰማነውን ወሬ ቸኩለን አምነን ከምንወዳቸው ወዳጆቻችን የተቆራረጥንና የማይገባ ነገር የተናገርን፤ ዛሬም እንኳ የምንናገር ጥቂት አይደለንም፡፡ ጌታ ይድረስልን፡፡ አሜን፡፡
     የድንግል ማርያምን የፅንስ ነገር ማጋለጥና በህጉ እርምጃ ማስወሰድ ትክክለኛ መንገድ ሊመስል ይችላል፡፡(ዘሌዋ.20፥10፤ዘዳግ.22፥24) ፀንሳ መገኘቷ ለማመንዘሯ በቂ ምክንያት ነው ብለው እርምጃ መውሰድ እንዲችሉ ህጉ ያዛልና፡፡ ጠባቂዋ ዮሴፍ ግን እየሆነ ያለው ነገር ግር ቢለውም፤ ግራም ቢገባውም ያደረገው ነገር የሐዲስ ኪዳን አማኝ የሆነበትን በጎ ሥራ ነው የሠራው፡፡  “እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ።”(ማቴ.1፥18)
     ያልተረዱትን በጥርጣሬ መናገር ጥሩ ለፖሊስ መረጃ መርጃ ይሆን ይሆናል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ግን አጸያፊ፤ ነውርም ነው፡፡ ያልገባን እስኪገባን የሚታገስ እምነትና ዝምታ ትልቅ ድል አለው፡፡ ፍጹም ጻድቅነትም ነው፡፡ ያልሆነውን እንደሆነ፤ የሆነውንም ደግሞ እንዳልሆነ አድርጎ ማቅረብና መናገር የዚህ ዘመን ያልታፈረ ርኩሰት ሆኗል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከተከሰሰባቸው ክሶች አንዱ “ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና፤ መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፥ እንደ ሕጋችንም እንፈርድበት ዘንድ ወደድን።”(ሐዋ.24፥5) የሚል ነው፡፡ በክሱ ውስጥ እውነት አለበት፡፡ እውነቱ ቅዱስ ጳውሎስ የናዝራውያን ወገን (የናዝሬቱ ኢየሱስን አማኝ) ነበር፡፡ በዚህ እውነት ውስጥ የተመረዘ ሐሰት አለበት፤ ህዝብን አነሣሣ ማለታቸው በቄሳር ላይ በጠላትነት ሰዎችን እያደራጀ ነው ለማለትና ይህንን በመሪነት እየመራ ነው ለማለት ነው፡፡ ይህ ሐሳብ በሌላም ሥፍራ ተንጸባርቋል፡፡(ሐዋ.21፥38)
    በእርግጥ የከሳሽነት መንፈስ የያዘው ሰው ስለሚናገረው ነገር እውነታነት አንዳች አይጨነቅም፤ በሐሰትም ቢሆን ማሸነፍን እንጂ፡፡ ታላላቅ ያልናቸው ሰዎች ያነሱብን፣ ያከበርናቸው የተዋረዱብን፣ ለምድር የከበዱቱ የተባሉት ከገለባ ይልቅ የቀለሉብን፣ አንቱ ብለን በመሰከርንላቸው አፍረን አንገት የደፋነው … ለሐሰት ቃል ሸንጎ ፊት በመቆማቸው፣ በሐሰት ምለው በሐሰት በመመስከራቸው፣ ባስቀመጥናቸውና በሰጠናቸው የአክብሮት ሥፍራ ባለመገኘታቸው ነው፡፡ በእርግጥም በዚህ ዘመን አገልጋዮች ጭምር በዚህ ነውር መያዛቸው እጅጉን ይመራል፡፡ ጻድቁ ዮሴፍ ግን “ማጋለጥና መርታት” የሚችልበት በቂ ምክንያት ቢኖረውም ነገርን በስውር መተው አሰበ፡፡
  ለእኛም ይህች የልብ ቅንነት ከጌታ ዘንድ ትሁንልን፡፡ አሜን፡፡
       ይቀጥላል …



   


No comments:

Post a Comment